የእስያው አደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ በአምስተርዳም በቁጥጥር ስር ዋለ

የአምስተርዳም አየር ማረፊያ

በአለም ትልቁ የአደንዛዥ ዕፅ ቡድን መሪ የሆነው እስያዊው የዕፅ ከበርቴ በአምስተርዳም በቁጥጥር ስር ውሏል።

የእስር ትዕዛዙ የወጣበት በአውስትራሊያ መንግሥት ነው ተብሏል።

ትሲ ቺ ሎፕ የተባለው የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ ትውልዱ ቻይና ቢሆንም ዜግነቱ ካናዳዊ ነው።

በእስያ ውስጥ 70 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን የሚያካሂድ ኩባንያ አለው።

በአለም ላይ ተፈላጊ ሰዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴው በአምስተርዳሙ ሺፖል አየር ማረፊያ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።

አውስትራሊያ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጣትና የፍርድ ሂደቱም በአውስትራሊያ እንዲካሄድ ትፈልጋለች።

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ሳም ጎር ሲንዲኬት ተብሎ የሚታወቀው የትሲ ቺ ኩባንያ በአውስትራሊያ ውስጥ ከሚገቡ ህገወጥ አደንዛዥ ዕፆች መካከል 70 በመቶውን እንደሚሸፍን አስታውቋል።

የ56 አመቱ የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ በዘረጋው የንግድ ስርአትና ሃብት ምክንያት ምክንያት ከሜክሲኳዊው "ኤል ቻፖ'' ጉዝማን ጋርም የሚያመሳስሉት አልታጡም።

የአውስትራሊያ ፖሊስ ግለሰቡን ከአስር አመት በላይ ሲያድነው የነበረ ሲሆን ወደ ካናዳ ለመብረር ሲል ነው በዚህ ሳምንት አርብ በቁጥጥር ስር የዋለው።

የፖሊስ መግለጫ እንደሚያሳው በኔዘርላንድስ የእስር ትዕዛዙ የወጣበት ከሁለት አመት በፊት በኢንተርፖል አማካኝነት ነው።

"በአለም ላይ እየታደኑ ካሉ ቁንጮ ሰዎች መካከል አንደኛው ነው። በቁጥጥር ስር የዋለው ባገኘነው ጥቆማ መሰረት ነው" በማለት የኔዘርላንድስ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

ሮይተርስ ከሁለት አመታት በፊት በሰራው ልዩ የምርምር ዘገባ "በእስያ አንደኛው ተፈላጊ ሰው" በሚል ትሲ ቺን የጠራው።

በዚህ ዘገባ ላይ ግለሰቡ ሜታፌታሚን ተብሎ ከሚጠራው አደንዛዥ እፅ ሽያጭ ብቻ 17 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በአውሮፖውያኑ 2018 ማስገባት እንደቻለ የተባበሩትን መንግሥታት ግምት አስቀምጧል።

የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴውን ለመያዝ በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ 20 የደህንነት ኤጀንሲዎች የተሳተፉበት ኩንጉር የሚባል ዘመቻ መካሄዱን ሮይተርስ አስነብቧል።

ግለሰቡ በቅርብ አመታት በማካው፣ ሆንግ ኮንግና ታይዋን እየኖረ ነበር ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክስ በአሜሪካ ለዘጠኝ አመታት ታስሮ ነበር።

የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴውን እስር ተከትሎ የአውስትራሊያ ሚዲያዎች የአገሪቱ ፌደራል ፖሊስ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ የታየ ትልቁ ስኬት ሲሉ አሞካሽተውታል።