አንጋፋው የቴሌቪዥን አቅራቢ ላሪ ኪንግ በ87 አመቱ አረፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስመ ጥር ፖለቲከኞችንና ዝነኛ ሰዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ በአለም ላይ ከፍተኛ ስፍራ መጎናፀፍ የቻለው አንጋፋው አሜሪካዊ የቴሌቪዥን አቅራቢ ላሪ ኪንግ በ87 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
ጋዜጠኛው በስድስት አስርት አመታት የሞያ ቆይታው ከ50 ሺህ በላይ ቃለ መጠይቆችን ማድረግ የቻለ ነው። ለ 25 አመታት ያህል በሰራበት ሲኤኤን ታዋቂነትን ያተረፈ ላሪ ኪንግ ላይቭ የሚባል ፕሮግራም ነበረው።
ላሪ ኪንግ ከጄራልድ ፎርድ እስከ ባራክ ኦባማ ድረስ ሁሉንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ከአሜሪካ መሪዎች በተጨማሪ የተለያዩ የአለም መሪዎችን በተለያዩ ጉዳዮች ማናገር የቻለ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ታሪካዊ የሚባሉ እንደ የጥቁር መብት ነፃነት ታጋዩ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ፣ ዳላይ ላማን ጋር ቆይታ ማድረግ ችሏል።
ጋዜጠኛው ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ሴዳርስ ሲናይ የህክምና ማዕከል ህይወቱ እንዳለፈ ኩባንያው ኦራ ሚዲያ አስታውቋል።
ባለፈው ወር በኮሮናቫይረስ ህመም ሆስፒታል ገብቶ እንደነበርና አገግሞ እንደወጣ የአሜሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በሚያጥፋት ሸሚዙ፣ በመነፅሩና በሱሪው ማንገቻው የራሱን የሆነ የፋሽን መለያ መፍጠር የቻለው ጋዜጠኛው በቅርብ አመታት ውስጥ በተደራራቢ ህመሞች ሲሰቃይ ነበር ተብሏል። በቅርቡም እንዲሁም ተደጋጋሚ የልብ ድካም አጋጥሞታል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ላሪ ኪንግ ስምንት ጊዜ ከሰባት ሴቶች ጋር ተጋብቷል።
ከነዚህም ትዳሩ አምስት ልጆችን አትርፏል። ከነዚህም መከካከል ሁለቱ ልጆቹ ባለፈው አመት በአንድ ሳምንት ልዩነት ህይወታቸው አልፏል።
ሴቱ ልጁ ቻያ በሳንባ ካንሰር የሞተች ሲሆን ልጁ አንዲ ደግሞ በልብ ድካም እንደሞተ ተዘግቧል።












