ኮሮናቫይረስ ፡ ባንነካካ፣ ባንተቃቀፍ፣ ባንሳሳም በጤናችን ላይ የሚጎድል ነገር ይኖር ይሆን?

ጓደኛሞች በአንድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ያለፈው የፈረንጆች ዓመት በጥቅሉ ካየነው መልካም ዓመት አልነበረም።

አራራቀን እንጂ አላቀራረበንም። ለመሆኑ ባንተቃቀፍ ምን ይቀርብናል?

ትዝ ብሎንስ ያውቃል? ለምን አልተጨባበጥኩም ብሎ የከፋውስ አለ?

ለነገሩ ልጆችንን አቅፎ መሳም፣ ፍቅረኛችንን መሳም፣ ባሎቻንን ማቀፍ. . . እንዴት አንናፍቅም?

በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች የፈረንጆቹን 2020 የማኅበራዊ መራራቅ ዓመት ብቻ ሳይሆን ቤት ተከርችሞብን የታሸግንበት ዝጋታም ዓመት ሆኖ ነው እያበቃ ያለው።

ከኮቪድ-19 መከሰት በፊት ማንም ሰው መቼስ ወደፊት መጨባበጥ ይከለከላል፣ መተቃቀፍ ያስቀስፋል ብሎ ያሰበ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።

ለመሆኑ አለመተቃቀፋችን አለመጨባበጣችን የራሱን ችግር ይዞ ብቅ ይል ይሆን?

ተመራማሪዎች አዎ ይላሉ።

መነካካት ተራ ነገር አይደለም።

በፍቅር መነካት ወይም መታቀፍ ሕጻን ሳለን የመጀመርያ ቋንቋችን ነው። ፍቅርን የምንማርበት ቋንቋ። መግቢያቢያችን። ደግነትን፣ ሰው መውደድን፣ ለሆነ ፍጡር እምነታችንን መስጠትን የምንሰለጥነው በእቅፍ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው።

በጊዜ ሂደት ረስተነው ይሆናል እንጂ ድሮ ድሮ ካልታቀፍን ብለን አልቅሰናል። ካላመናችሁ እናታችሁ ጋር ደውሉ።

ለዕድገታችንም እንደ እናት ጡት ወተት ሁሉ መታቀፍ አስተዋጽኦ ነበረው። በጊዜ ሂደት ክደውን ነው እንጂ. . . ።

"የሰዎች ተቀራርቦ መነካካት የዋዛ ነገር አይደለም። ማኅበራዊ ሙጫ ማለት ነው። አስተሳስሮናል። ከምንወደው ሰው ጋር ገምዶናል። እንደ ሰው የሚያቀራርበን አንድ ነገር ቢኖር ይኸው ነው" ይላሉ ዴቪድ ሊንደን።

ዴቪድ 'ዘ ኒው ሳይንስ ሂዩማን ኢንዲቪጁዋሊቲ' ደራሲ ናቸው። በዚህ የንክክኪ ሳይንስ ውስጥ ብዙ አጥንተዋል።

"የመነካካት ነገር እና ፋይዳው እምብዛምም አልተጠናም። ቸል ያልነው፤ ገሸሽ ያደረግነው ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም" ይላሉ ደራሲ ዴቪድ።

በአበባ ተሸፍንው የሚሳሳሙ ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለመሆኑ ሌሎችን ሰዎችን ስንነካ አእምሯችን ውስጥ ምንድነው የሚፈጠረው?

አንዳንድ ጥናቶች መነካት፣ መታቀፍ፣ ልክ ሕመም ማስታገሻን የመውሰድ ያህል ፈውስ ይሰጣል ይላሉ።

ይህ የተጋነነ አረፍተ ነገር ከመሰላችሁ፣ አንድ ሕጻን ልጅ ሲነካ እንዴት እንደሚሆን ለማየት ሞክሩ።

አንድ ሕጻን ልጅ በእናቱ ጭንቅላቱ ቢዳበስ የልብ ምቱ መረጋጋት ይጀምራል። ይህን ያሉት በሕጻናት አንጎል [ኒውሮሳይንስ] ላይ ተመራማሪ የሆኑት ሬቤካ ስላተር ናቸው።

አንዳንድ ጥናቶች ይህንን ነገር ከዚህም በላይ ገፋ ያደርጉታል።

ለምሳሌ ክብደታቸው ከአማካይ በታች ሆነው የተወለዱ ልጆች በእናቶቻቸው ሲነካኩና ሲታቀፉ መጠናቸው እየተስተካከለ እንደሚመጣ ተደርሶበታል።

የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪ ሮቢን ደንበር እንደሚሉት የሰው ልጅ ከእንሰሳት ጋር ከሚያመሳስሉት ነገሮች አንዱ ንክኪና ለዚያ የሚሰጠው ትርጉም ነው።

የሰው ልጅ ያለበት የነ ዝንጀሮና ዝርያቸው ጨምሮ አጥቢዎች በሕይወት ዘመናቸው 20 ከመቶውን የሚያሳልፉት እርስ በርሳቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በመነካካት ነው።

ከዝርያቸው ጋር ወዳጅነታቸውን የሚገልጹትም በብዛት በንክኪ ነው።

ለምሳሌ አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስንነካ በመዳፋችን ያለው የነርቭ ብልጭታ ለጭንቅላታችን 'ከአዲስ ሰው ጋር አዲስ ግንኙነት እየፈጠርክ ነው' የሚል መልዕክት ያደርስለታል። ያ ስሜት ደግሞ ብዙ እጢዎች መልካም የሰውነት ፈሳሾችን እንዲያመነጩ ያደርጋል።

በንክኪ ውስጥ አእምሯችን ዘና ይላል፤ በተለይም ደግሞ አብረነው በንክኪ እየተግባባነው ያለውን ሰው የምናምነው ሲሆን እፎይታን ይመግበናል ይላሉ እኚሁ ተመራማሪ።

ከመነካካት ጋር የነበረን የመጀመሪያ ቁርኝት ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝ ነው። መጀመሪያ የሳምናትን ኮረዳ፣ መጀመሪያ የዳበስነውን መልከ መልካም ልጅ፣ የመጀመሪያ የፍቅር ግንኑነቶች ሁሌም በአእምሯችን የማይጠፉት ከንክኪ በሚያገኙት ኃያል የተነሳ ነው።

ለመሆኑ መነካካት ይህን ያህል ትርጉም ካለው አለመነካካት ምን ሊያደርገን ይችላል?

መነካት፣ መታቀፍ ይህን ያህል አእምሯችን ላይ በጎ ተጽእኖ አለው ብለናል። ያረጋጋናል፣ ያስደስተናል፣ ሕይወታችንን እንድንወዳት ያደርገናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕመማችንን ያስወግድልናል። አልተጋነነም።

በንክኪ ደዌ ይፈወሳል። የንክኪ ሕክምና ያለውም ለዚህ ሳይሆን ይቀራል?

አሁን እንዳትነካኩ፣ እንዳትጨባበጡ፣ እንዳትስሙ ስንባል ሳናውቀው የሆነ ነገራችን እየተጎዳ ነው።

"እርግጥ ነው አትነካኩ በተባልን ማግስት ሕመም አልጀመረንም። ራሳችንን አልሳትንም፣ መፈጠራችንን አልጠናል ይሆናል. . ." ይላሉ ደራሲው ሊንደን። . . . ነገር ግን ከሰው ጋር የነበረን የቁርኝት ገመድ ለእኛ ባይታየንም ተበጥሷል፤ በስሜት ተለያይተናል። ቀስ በቀስ መጎዳታችንን ሳናውቀው ተጎድተናል።"

ለምሳሌ አንዳንድ እንሰሳትን በፍጹም እንዳይነካኩ ብንከለክላቸው ወዲያውኑ ሊታመሙ ይችላሉ።

ታመሙ የምንለው በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአካልም ጭምር ነው። በጭንቀት ይወጠራሉ፤ አዳዲስ የአውሬነት ባህሪን እያሳዩ ሊመጡ ይችላሉ።

በጊዜ ሂደት ደግሞ ጤናቸው እየተቃወሰ ሊመጣ ይችላል። እስከመሞትም ሊያደርሳቸው ይችላል።

ወረርሽኙ የገባ ሰሞን፣ በተለይ ደግሞ ብዙ አገሮች ማኅበራዊ መራራቅን ግዴታ ባላደረጉበት ወቅት እንኳ ብዙ ሰዎች ከሰዎች ጋር መቀራረብን፣ መነካካትን እንደናፈቁ ይናገሩ ነበር።

አሁን ዓለም እንዲህ በተራራቀበት ጊዜ ይህ ሁኔታ ሲብስበት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ነው።

ምናልባት ነገሩን ትተነዋል። ቅርርቦሽንና ፋይዳውን የምናስብበት ጊዜ እንኳን አጥተን ይሆናል። ሕይወት እያራወጠን ዘንግተነው ይሆናል። ያ ማለት ግን ውስጣችን አልተጎዳም ማለት አይደለም።

ጎልድስሚዝ ዩኒቨርስቲ በቢቢሲ ራዲዮ ፎር በኩል አንድ ጥናት አድርጎ ነበር። በጥናቱ በ110 አገሮች የሚኖሩ 40ሺህ ሰዎች ተጠይቀው ነበር።

20ሺህ የሚሆኑት መተቃቀፍን እጅግ አድርገው መናፈቃቸውን አምነዋል። መነካትን መናፈቅ ከባድ ናፍቆት ነው።

እጃቸውን ያጋጠሙ ልጆች እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዲያ ምን ተሻለ?

ፕሮፌሰር ስሌተር እንደሚሉት ከሆነ ከዚህ በኋላ በሰዎች መካከል ተህዋሲው ቢጠፋ እንኳን ከተህዋሲው በፊት እንደነበረው ጊዜ ንክኪዎች አይኖሩም ይላሉ። ሰዎች በመጨባበጥ ውስጥ የሚለዋወጡት ወዳጅነት እንደነበረው አይዘልቅም ነው የሚሉት።

ነገር ግን የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪና ሳይኮሎጂስት ሮቢን ደንበር ይህ ነገር አያሳምናቸውም።

እሳቸው የሚያምኑት ወዳጅነትና መነካካት ሰዋዊ ነው። ሰዋዊ ባህሪ ደግሞ እንዴትም ቢሆን ካቆመበት ይቀጥላል።

መዳፋችን የውስጠኛው አካሉ ሲፈጠር ራሱ እንዲነካ፣ እንዲዳስስ ተደርጎ ነው። የነርቮቹ ብዛት የሚያመላክቱትም ያንኑ ነው።

እኛ ባናውቀውም ሰውነታችን ልክ እንደ ጥልፍልፍ የኤሌክትሪክ ገመድ ያለ ነው። ንክኪ ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮ መልዕክት ይልካል። ስለዚህ ያለ መነካካት ጤናችን ልክ አይመጣም።

በሚወዱት ሰው መነካትን የመሰለ የአእምሮ ፈውስ የለም።

ለረዥም ጊዜ በናፈቅነው ሰው እቅፍ ውስጥ የመግባትን ያህል ደስታ የለም። በናፈቅነውና በምንወደው ሰው እቅፍ ውስጥ ለሰከንዶች መቆየት ትንሽዬ የገነት ጎጆ ውስጥ ገብቶ የመውጣት ያህል ነው።

"አንድ ሰው ስለእናንተ የሚሰማውን በትክክል ለማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ . . . የሚነግሯችሁን ከመስማት ይልቅ እንዴት እንደሚነካችሁ ስሜቱን ለመረዳት ሞክሩ" ያላሉ ባለሙያው።

ብዙ ሰዎች ከልጅነታቸው ጋር በነበራቸው የእናት ፍቅር ውስጥ ምን ትዝ ይላችኋል ሲባሉ፤ እናታቸው ፀጉራቸውን ስትነካካቸው የነበራቸው ስሜትን በይበልጥ ያስታውሳሉ። ለምን?

የፈረጆቹ 2021 ዳግም የምንተቃቀፍበት ዘመን ይሆን ይሆን?