ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአምስተርዳም፣ ፓሪስ እና ሊዝበን ማራቶኖችን አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
እሁድ ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም በአውሮፓ ከተሞች በተካሄዱት የፓሪስ፣ የአምስተርዳም እና የሊዝበን የማራቶን ውድድሮችን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል አድርገዋል።
ሆላንድ ውስጥ በአምስተርዳም ከተማ በተካሄደ የወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ ርቀቱን በ2 ሰዓት 03 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመሮጥ አሸንፏል።
ሌላው ኢትዮጵያዊ ልዑል ገብረ ሥላሴ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል።
በዚህ ውድድር ላይ ኬንያዊው በርናንድ ኮዬች ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
እሁድ በተካሄደው የአምስተርዳም የማራቶን ውድድር የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ከአንድ እስከ አስር ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በሴቶች ውድድር ደግሞ ኬንያዊቷ አንጌላ ታኑዪ ማሸነፍ ችላለች። የገባችበት ሰዓት 2፡17፡57 የቦታው ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
ማርዊን ቼፕኬሞይ ሁለተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች። ኢትዮጵያዊቷ ሄቨን ኃይሉ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ገበያነሽ ኃይሉ እና ወርቅነሽ ዓለሙ አራተኛ እና ምስተኛ ሆነዋል።
የፓሪስ ማራቶን
በፈረንሳይ ፓሪስ የሴቶች ማራቶን የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነትን ይዘው አጠናቀዋል። ውድድሩን ትዕግስት ማሙዬ አሸንፋለች። ትዕግስት ርቀቱን የሮጠችበት ሰዓት 2፡26፡12 ነው።
የኔነሽ ድንቄሳ፣ ፋንቱ ጂማ እና ዋጋነሽ መካሻ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ተከታትለው በመግባት ይዘዋል።
ጃኔት ሩጉሩ ከኬንያ አምስተኛ ስትሆን ኢትዮጵያዊቷ የሺ ቸኮለ ስድስተኛ ሆናለች።
በፓሪስ የወንዶች ማራቶን ደግሞ ኬንያዊው ኤሊሻ ሮቲች ቀዳሚ ሆኖ በመግባት አሸንፏል። ሮቲች 2 ሰዓት 04 ደቂቃ 21 ሰከንድ ውድድሩን አጠናቋል።
ኃይለማርያም ኪሮስ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል። ሌላኛው ኬንያዊ ሂላሪ ኪሳምቡ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
የሊዝበን ማራቶን
ፖርቱጋል ሊዝበን ማራቶንም የኢትዮጵያውያን የበላይነት ታይቷል። በወንዶች አንዷለም በላይ 2 ሰዓት 05 ደቂቃ 52 ሰዓት በመግባት አሸንፏል።
ይሁንልኝ አዳነ እና ባለው ይሁኔ ሦስተኛ እና አራተኛ በመሆን ኬንያዊውን ሆሴ ኪፕሊሞ ተከትለው ውድድራቸውን አጠናቅዋል።
በሴቶቹ ዘርፍ ደግሞ አሳየች አያሌው አሸንፋለች። አሳየች 02 ሰዓት25 ደቂቃ 07 ሰከንድ ውድድሩን አጠናቃለች። አልማዝ ነገደ ሁለተኛ ስትሆን ጄን ጄላጋት ሦስተኛ ሆናለች።
















