ቀነኒሳ ያሰብኩን ያላሳካሁት በጤና እክልና በአየር ንብረት ምክንያት ነው አለ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ቀነኒሳ ያሳበውን ያላሳከው በጤና እና በአየር ንብረት ምክንያት ነው አለ

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን ቀድሞ ያሰበውን ሳያሳካ የቀረው በጤና እክል እና በአየር ንብረት ምክንያት መሆኑን ተናገረ።

አትሌት ቀነኒሳ ትናንት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር አቅዶ የነበረ ቢሆንም ውድድሩን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በወንዶች ውድድሩን ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ በ2፡05፡45 አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኬኒያዊው ቤትዌል ዬጎን ቀነኒሳ በቀለን አስክትሎ በመግባት ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል።

ቀነኒሳ ከሁለት ዓመት በፊት እአአ 2019 በተካሄደው የበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን ለመሻሻል ሁለት ሰኮንዶች ብቻ ቀርተውት ውድድሩን ማሸነፉ ይታወሳል።

ከውድድሩ በኋላ ቀነኒሳ ለቢቢሲ እንደተናገረው በበርሊን ከተማ የነበረው የአየር ሁኔታ ሞቃት በመሆኑ በውድድሩ ላይ በፈለገው ፍጥነት መሄድ እንዳልቻለ ገልጿል።

"ከስምንት ወር በፊት በኮቪድ ታምሜ ነበር" ያለው አትሌት ቀነኒሳ፤ በሕመሙ ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ልምምድ ሳያደርግ መቆየቱ ያሰበውን እንዳያሳካ እንዳደረገው ተናግሯል።

"ከዚያ ሕመም አገግሜ ተመልሼ ይሄን ውጤት ማስመዝገቤ ለእኔ ጥሩ ነው። ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በኋላ ነው ማራቶን ላይ የተወዳደርኩት" በማለት በበርሊኑ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥሩ ውጤት ማስመዝገባቸውን በጥሩ ጎኑ አንስቷል።

ቀነኒሳ "ውድድር እስከሆነ ድረስ ያጋጥማል። ለቀጣይ ደግሞ በደንብ ተዘጋችቼ ጥሩ ውጤት አስመዘግባለሁ ብዬ ገምታለሁ" ብሏል።

አትሌት ቀነኒሳ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በሚካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን ተሳታፊ እንደሚሆን ቀደም ሲል ይፋ ተደርጓል።