ዩኔስኮ፡ የመስቀል በዓልን ጨምሮ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስመዘገበቻቸው 13 ቅርሶች

ኢትዮጵያ ውስጥ የመስቀል በዓል በሚከበርበት መስከረም 17 በየዓመቱ የዓለም የቱሪዝም ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
በዚህ ዕለት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው የሚንቀሳቀስበትን 'ጭስ አልባው' የሚባለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጎልበት አገራት ጥት ያደርጋሉ።
በተለያዩ ዝግጅቶችም ሁሉም እንደየ አቅሙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊ ተፈጥሯዊና ሌሎችንም ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ የቱሪዝም ሀብታቸውን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማጉላት ጥረት ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በተለያዩ ዘርፎች የታደለች ከመሆኗ ባሻገር በርካታ የቱሪስት መሰህቦችን በዓለም ደረጃ ለማስመዝገብ ችላለች።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የተካተቱ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት።
ቅርሶቹ ከአክሱም ሐውልቶች እስከ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ናት።
1. የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስትያናት
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ከአንድ ወጥ ድንጋይ በመፈልፈል የተሰሩ ሲሆን እኤአ በ1978 በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ከአዲስ አበባ በ645 ኪሜትር ላይ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደተደቀኑበት በባለሙያዎች ሲነገር ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
2. የሠሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
የሠሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እ.ኤ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በ2009 ዓ.ም በዩኔስኮ የአደጋ ተጋላጭ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ነበር።
በወቅቱ ፓርኩ በጥበቃ መጓደል፣ በደን መጨፍጨፍና በአካባቢው ሕዝብ እየታረሰ እንስሳትም እየተሰደዱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የተመለከተው ዩኔስኮ፤ በአደጋ ላይ ነው በሚል መዝግቦት እንደነበረና ሁኔታዎች በአስቸኳይ ካልተስተካከሉ ሊሰርዘው እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።
ፓርኩ ከመጠን በላይ በግጦሽ በመጎዳቱ እንዲሁም ዋሊያ አይቤክስ፣ የሠሜን ቀይ ቀበሮ እና ሌሎች ግዙፍ አጥቢ እንስሳት ቁጥራቸው በመመናመኑ ነበር ለአደጋ የተጋለጡ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ ሰፍሮ የቆየው።
ፓርኩ በ1960ዎቹ በሕዝብ ተከልሎ ሲጠበቅ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ መሆኑና በተለይ በአገሪቱ ውስጥ በሠሜን ተራሮች ላይ ብቻ የሚገኘው ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀበሮና ጉሬዛ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ፓርኩ በርካታ አዕዋፋትን የያዘው እንደ ውጬ፣ ዝግባ፣ ወይራና ዋንዛ የመሳሰሉ ዛፎችና ሌሎች ቁጥራቸው የበዛ የተለያዩ እፅዋት የሚገኝበት ሲሆን 138 ስኩዬር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
3. የፋሲል ግቢና ሌሎች የጎንደር ሐውልቶች
የፋሲል ግቢ እና ሌሎች ግብረ ህንጻዎች እና አብያተ መንግሥታት እኤአ በ1979 በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል።
ይህ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ከአዲስ አበባ በ748 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ታሪካዊ ቅርስ የአገሪቱ ጥንታዊ ስልጣኔ ሕይወት ያለው ምስክር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
በጎንደር ከተማ የሚገኘው የንጉሥ ፋሲል ግቢ የንጉሣውያን ዋነኛ ማዕከል የነበረ ሲሆን ዙሪያው 900 ሜትር ርዝመት ያለው ግንብና በ12 በሮች የተከበበውን መንገድ የሚዞር ድልድይ አለው።
በ1632 በንጉሥ ፋሲለደስ ዘመን ጎንደር የኢትዮጵያ የአስተዳደር ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን በ16ኛውና በ12ኛው ክፍለ ዘመን የታጠረው የፋሲል ግቢ የንጉሥ ፋሲልና የተከታዮቻቸው መኖሪያ ነበር።

4. አክሱም
አክሱም ሰው ሰራሽ አርኪዮሎጂ ስፍራ ሲሆን እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ይህ በትግራይ ክልል ከአዲስ አበባ በ1080 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ ከፍተኛ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት፣ እንዲሁም ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍን የሚወክል በመሆኑ መመዝገቡን የዩኔስኮ ሰነዶች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዲናና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ ተመራማሪዎች እንደሚገልጿት የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ ቀጥሎም የሐይማኖት ማዕከል ብሎም የጥንታዊ ሐይማኖታዊ መንግሥት በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች፣ አሁንም በርካታ ምዕመናን የምታስተናግድ ከተማ ነች።
5. የታችኛው አዋሽ ሸለቆ
የታችኛው አዋሽ ሸለቆ የተፈጥሮ (የፖሊዮአንትሮፖሎጂ) ግንቶች ስፍራ ነው። ሸለቆው የሰው ዘርና የአትክልት ቅሪት በዙሪያው የተገኘበት ሲሆን ተከታታይ የጥናትና ምርምር ሥራ በቦታው ተሰርቷል።
እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ይህ ስፍራ በአፋር ክልል ከአዲስ አበባ በ577 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።
ይህ ስፍራ ኢትዮጵያ ሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያሳወቀ ስፍራ ነው። በዚህ ስፍራ በ1974 ዓ.ም 3.2 ሚሊዮን እድሜ ያስቆጠረችው ሉሲ ስትገኝ፣ 4.4 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችው አርዲም የተገኘችው በዚሁ ስፍራ ነው።
3.6 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችው የሦስት ዓመት ህፃኗ 'ሰላም'ም በዚሁ ቦታ ተገኝታለች።
6. የጢያ ትክል ድንጋይ
ጢያ ትክል ድንጋዮች ባህላዊ (የአርኪዮሎጂ) ግኝት ስፍራ ነው። እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው እና ከአዲስ አበባ በ86 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ክልል ይገኛል።
የእነዚህ ትክል ድንጋዮች ብዛት ወደ 36 የሚጠጋ ሲሆን የተለያየ ስፋት፣ ርዝመት (ከ1 እስከ 5 ሜትር) እና ውፍረት አላቸው።
32ቱ ትክል ድንጋዮች ላይ የተለያዩ ምስሎች (የጎራዴ፣ የጦር፣ የጨረቃ፣ ፀሐይ መሰል፣ የእጅ እና ምንነቱን መለየት ያልተቻለ ቅርጽ) ተቀርጾባቸዋል።
7. የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪኦሎጂ ስፍራ
ይህ የፖሊዮአንትሮፖሎጂ ግኝቶች ስፍራ የሆነው ሸለቆ እኤአ በ1980 ነው በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው። በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ በ1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም የተመዘገበው ይህ ስፍራ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከኛንጋቶም እስከ ዳሰነች አካባቢ የሚገኘውን ክፍል ይሸፍናል።
የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ስለሰው ልጅ አመጣጥና ቅድመ ታሪክ ጥናት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ከ2.4 ሚሊዮን ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶችና የሰው ዘር ቅሪተ አካላት የተገኙበት ይህ አካባቢ በርካታ የተለያዩ ጥንታዊ ባህላቸውንና አኗኗሯቸውን የሚከተሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይኖሩበታል።

8. የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ
የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ በጥንታዊ በሮችና ታሪካዊ ግብረ - ህንጻዎች ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዝግቧል።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም እኤአ በ2006 የተመዘገበው ይህ ቅርስ በሐረሪ ክልል ውስጥ ከአዲስ አበባ በ525 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል።
ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ የሆነችው ሐረር በ7ኛው ክፍለ ዘመን መቆርቆሯ ይነገራል። በጀጎል ግንብ የተከበበችው ሐረር ከተማ አምስት በሮች አሏት።
ሐረር ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና ከመሃል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ አገራት ጋር በንግድ መንገዶች ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባሕር ወደቦች አማካኝነት ትገናኝ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
9. ኮንሶ
የኮንሶ መልክዓ ምድር በእርከን የታጠሩ መንደሮች ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እኤአ በ2011 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ይህ በደቡብ ክልል የሚገኘው እና ከአዲስ አበባ 595 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ በውስጡ በርካታ ባህላዊ ሀብቶችን ይዟል።
በኢትዮጵያ የ400 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚነገው የኮንሶ ሕዝብ ባህላዊ መኖሪያ በውስጡ በካብ የታጠሩ መንደሮች፣ ባህላዊ ጎጆዎች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ሐውልቶች እና ኩሬዎችን የያዘ ነው።

10. መስቀል
የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ተቋም መዝገብ ውስጥ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ታዳሽ ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ የመስቀል ባህላዊ ክብረ በዓል አስረኛውና የመጀመሪያው የማይዳሰስና የማይጨበጥ (ህሊናዊ) ባህላዊ ቅርስ በመሆን ነበር የተመዘገበዉ።
11. ፍቼ ጫምባላላ
የሲዳማ ብሔር አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ የሆነው ፍቼ ጫምባላላ በዓል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበው በኅዳር 2008 ዓ.ም ነበር።
ፍቼ ጫምባላላ በዓል በውስጡ በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎችን የያዘ ነው።

12. የገዳ ሥርዓት
የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) መስፈሩ ይፋ የተደረገው ኅዳር 2009 ዓ.ም. ነበር።
የኦሮሞ ሕዝብ በረጅም ዘመናት ውስጥ ካዳበራቸው የአኗኗር ብልሃቶች እና ሥርዓቶች መካከል አንዱ የገዳ ሥርዓት ነው።
የገዳ ሥርዓት በዋናነት የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመምራት የሚረዱ ዕሴቶችን አካትቷል።
ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ዋና ምሰሶ የሆነ ሥርዓት ሐይማኖታዊ እና የሕግ ሥርዓቶችን በውስጡ አካቶ ይዟል።
በተጨማሪም የገዳ ሥርዓት ከውልደት እስከ ሽምግልና ድረስ በእድሜ በመከፋፈል የተለያዩ የማኅበረሰብ ኃላፊነቶችን፣ እና የስልጣን ድርሻዎችን ይሰጣል።
በገዳ ሥርዓት ውስጥ ዋቄፈና እና ኢሬቻ የተሰኙ የዕምነትና ባሕላዊ ሥርዓቶች ይገኙበታል።
13. ጥምቀት
የጥምቀት በዓል የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል አንዱ ነው።
ቦጎታ ኮሎምቢያ ውስጥ ድርጅቱ ስለ ቅርስ ጥበቃ በተነጋገረበት ስብሰባ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት በዓሉ በዩኔስኮ የተመዘገበ 4ተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኗል።
ጥምቀት በወርሃ ጥር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ሐይማኖታዊ በዓል ነው።
የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 11 ተጀምሮ በማግስቱ ጥር 12 ቃና ዘገሊላም በድምቀት ይከበራል።
ጥምቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባና ጎንደር ተጠቃሾቹ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, J. Countess
















