ቱሪዝም፡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት እግራቸውን የሰበሰቡ ጎብኚዎች የሚመለሱት መቼ ይሆን?

በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ከተካተቱት ቁልፍ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ አከባበርን ተከትሎ በርካታ ጎብኚዎች ወደ አገር መጥተው ነበር።
ከሐምሌ 2011 እስከ ታኅሳስ 2012 ባሉት ወራት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይናገራሉ።
ተስፋ አይቶ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኗል ከሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህንንም በተመለከተ ቢቢሲ በዘርፉ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው ሥራና ኑሯቸው ከተስተጓጎለባቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑት አናግሯል።
"ፈረንጅ ካየን 7 ወር አለፈን"
በቅሎዎችን ለጎብኚዎች በማከራየት የሚተዳደሩት ቀሲስ አሰፋ ለጋስ ነዋሪነታቸው በጥንታዊቷ የላሊበላ ከተማ ሲሆን የላሊበላ የበቅሎ አከራዮች ማኅበርንም 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሊቀመንበርነት መርተዋል።
አሁንም በማኅበሩ የስምሪት ክፍል ውስጥ እያገለገሉ ሁለት በቅሎዎችን በማከራየት ኑሯቸውን ይደጉማሉ። በዚሁ ሥራ ታግዘው የስድስት ልጆቻቸውን የትምህርት ደረጃ ከ8ኛ ክፍል እስከ መጀመሪያ ዲግሪ አድርሰዋል።
በዚህም የቱሪዝም እንቅስቃሴው በሚደራበት ወቅት በቅሎዎቹን ከላሊበላ ወደ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ገነተ ማርያም፣ አሽተን እና አቡነ ዮሴፍ ተራራዎች ለሚሄዱ ጎብኚዎች በማከራየት በአማካይ በወር እስከ 3 ሺህ ብር ያገኙ እንደነበር ቀሲስ አሰፋ ያስታውሳሉ።
ከሰባት ወር በፊት ግን ይህንን እንቅስቃሴ ማስቀጠል አልተቻለም። ቀሲስ አሰፋ እድሜ ልካቸውን በዚሁ ሥራ ሲሰማሩ አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የጎብኚዎች ቁጥር ከፍና ዝቅ ማለት ካልሆነ በስተቀር ሥራውን አደጋ ላይ የጣለ ክስተት ገጥሟቸው አያውቅም።
"ማኅበሩን ከአባቶቻችን ነው የተረከብነው" የሚሉት ቀሲስ አሰፋ፤ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የመኪና መንገድ ባልተሰራበት ወቅት እንግዶችን ከአውሮፕላን ማረፊያ በመቀበል ወደ ላሊበላ በመውሰድም የበቅሎ ማኅበሩ የማይረሳ እንዳለው ይናገራሉ።
የኮሮናቫይረስ መከሰት ግን በዚህ የዕድሜ ጠገብ የሥራ ዘርፍ ላይ በእርሳቸውም በአባቶቻቸውም ዘመን አይተውት የማያውቁትን ጫና አሳድሯል። "ከተማችን ከፍተኛውን ገቢ የምታገኘው ከጎብኚዎች ነው፤ አሁን ግን ፈረንጅ ካየን ሰባት ወር አለፈን" በማለት ሥራው ሙሉ በሙሉ ቀሟል ይላሉ።
ወትሮውንም አንዳንድ የአስተዳደር ችግሮችና የጥቅም ተጋሪዎች በየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ማለት ለማኅበሩ ስጋት የነበረ ቢሆኑም በመላው ዓለም የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግን ችግሩን አባብሶታል።
ወደ ላሊበላ ለሚመጡ ጎብኚዎች በቅሎዎቹን በማከራየት የምትመራ ህይወት ከሰባት ወራት ወዲህ ፈተና ገጥሟታል። አሁን በቅሎዎቹን አከራይቶ ከሚገኘው ገቢ ይልቅ ለበቅሎዎቹ የሚሆን መኖ ለመግዛት የሚወጣው ወጪ አይሏል።
ይህም በኪሳራ እንደመኖር ማለት ነው ይላሉ። እናም የማኅበሩ አባላት መፍትሔ ያሉትን ርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፤ በቅሎዎቻቸውን ሸጠው ህይወታቸውን መምራት።
እንደ ቀሲስ አሰፋ ገለጻ በማኅበሩ ውስጥ የነበሩት የበቅሎዎች ብዛት 600 ደርሶ ነበር። አሁን ግን አብዛኛው የማኅበሩ አባላት በቅሎዎቻቸውን በመሸጣቸው ቁጥሩ ወደ 106 አሽቆልቁሏል። ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አሁን የያሉት በቅሎዎችም ተሸጠው ማኅበሩ ሊፈርስ ይችላል ብለው አሰፋ ይሰጋሉ።
ጎንደርና ቱሪዝም
አዝማሪ ወረታው ማለደ የእርሱን እና የቤተሰቡን ሕይወት የሚመራባት ብቸኛ መሳሪያው ማሲንቆው ነች። ሙሽሮችን ሠርጋቸውን ያደምቅላቸዋል፣ እንግዶችን በማሲንቆው ይቀበላል፣ በባሕላዊ ምሽት ቤቶች በመዘዋወር አዝናኝ ጨዋታውን ያቀርባል፣ ጎብኚዎችን በማሲንቆው ያስደምማቸዋል።
ይህ ለበርካታ ዓመታት የኖረበት የሥራ ዘርፉ ነው። ከሞያ አጋሩ ጋር በትዳር ተሳስረው ያፈሯቸውን አራት ልጆች የሚያሳድጉትም ከዚሁ ሥራ ከሚያገኙት ገቢ ነው። ነገ ሙያዬን አሳድጌ የተሻለ ደረጃ እገኛለሁ እንጂ የተለመደውን ሥራዬን ማንም ይነጥቀኛል ብሎ አያስብም።
"ባሕላችንን በመሸጥ የምንተዳደር በመሆናችን የባሕል አምባሳደሮች ነን" የሚለው ወረታው፤ "ቋሚ ደመወዝ ባይኖረንም ጎብኚዎችንና ሌሎች የሙዚቃ መድረኮችን በመጠቀም ብቻ ህይወታችንን ያለ ችግር እንመራ ነበር" ይላል።
በዚህም ሥራ እንደየወቅቱ ሁኔታ በወር በአማካይ እስከ 10 ሺህ ብር ያገኙ እንደነበር ያስታውሳል።
ጎብኚዎችን በማስተናገድ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ከጎርጎራ እስከ ባሕር ዳር በመርከብ ወይም በጀልባ ሲሄዱ በማጀብ "ዳጎስ ያለ ገንዘብ እናገኝ ነበር" የሚለው ወረታው፤ ከጎንደር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ቤተ እስራኤላዊያን ሲመጡ ምርጫቸው አዝማሪ በመሆኑ እነሱን በማዝናነት ጥሩ ሥራ ይስሩ እንደነበርም ይናገራል።
በተለይ ከቤተ እስራኤላዊያን ጋር የተለየ ቁርኝት እንደነበረው እና እነርሱ ሲመጡ እንደ አዝማሪ ብቻም ሳይሆን እንደ አስጎብኚም በመሆን ገቢ ያገኝ እንደነበር ይገልጻል።
ከዕለት ደራሽ ሥራዎች ባሻገርም ከባለቤቱና በተመሳሳይ ሙያ ከሚገኙ ሌሎች 11 አዝማሪዎች ጋር በመሆን "ኮራሁ በባህሌ" የሚል የምሽት መዝናኛ ቤት ከፍተው እየሰሩ በነበረበት ጊዜ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ቤታቸውን ቆላልፈው ያለ ምንም ሥራ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።
"ያለፉት ሰባት ወራት ምንም ያላገኘንባቸውና በህይወታችን ገጥሞን የማያውቅ አደጋ ላይ የወደቅንበት ነው" በማለት የችግሩን ክብደት ይገልጻል።
"መንግሥት በሚያሰናዳቸው ፕሮግራሞች እንዳንሳተፍም በወረርሽኙ ምክንያት መንግሥት ሰው የሚሰባሰብባቸውን ዝግጅቶች ሰርዟል። የራሳችንን ቤት እንዳንከፍትም የሚመጣ ሰው ስለማይኖር ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዘነብን፤ እንዲሁ ተጨንቀናል" ይላል።
ወረታው እንደሚለው ይህን ክስተት አንዳንዴ ለማመን ሁሉ እንደሚቸገር ሲናገር "ይህ በተለይ በእኛ ሥራ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ስለሆነ ለ7 እና ለ8 ወራት ያለሥራ መቆየታችን በጣም አሳሳቢ ነው።"
አክሱም፣ መቀለ፣ አድዋና ገረዓልታ ይዞር የነበረው ጉዕሽ
ወጣት ጉዕሽ ከልጅነቱ ጀምሮ ተወልዶ ወደ አደገባት አክሱም ከተማ የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች እያየ ሲያድግ 'ምን ፈልገው ነው?' የሚል ጥያቄ ይመላለስበት እንደነበር ይናገራል።
ቀስ በቀስ በታሪክ ዙርያ ያለውን ግንዛቤና እውቀት አሳድጎ በዚያው ወደ አስጎብኚነት ገባ። ጉዕሽ፣ ከአክሱም እስከ መቀለ፣ አድዋና ገረዓልታ ጎብኚዎችን ይዞ ይዞር ነበር። ኑሮውንም የመሰረተው ከዚሁ ሥራ በሚያገኘው ገቢ ነው።
ባለፈው ዓመት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ግን ወደ አካባቢው የሚመጡ የጎብኚዎች ቁጥር እንደቀነሰና ለዓይኑ እንኳ የውጭ አገር ዜጋ ካየ መከራረሙን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በዚህ ምክንያት አሁን ምንም ገቢ የለኝም። ኮቪድ-19 በህይወታችን ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም" ይላል።
የሚያገኘው ገቢ እየቀነሰ በመምጣቱ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ያቋቋመው ማኅበር አቅሙ እየተዳከመ፣ አባላቱም ተስፋ በመቁረጥ ወደ አለመግባባት መድረሳቸውን ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, Awol Sultan
ያጠራቀምኩትን ስለጨረስኩ ሥራ ለመቀየር ተገድጃለሁ
የዲንሾ ከተማ ነዋሪ የሆነው አወል ሱልጣን በአስጎብኚነት ለስምንት ዓመት ያህል ሰርቷል። በእነዚህ ዓመታት በሐረር፣ ቦረና አብጃታ፣ ሻላ፣ ላንጋኖና ሌሎች የቱሪስት መስህቦችን በማስጎብኘት ኑሮውን ይመራ እንደነበር ለቢቢሲ ይናገራል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ግን እርሱም ሆነ ሌሎች የሥራ አጋሮቹ እጅጉን መጎዳታቸውን ይመሰክራል።
"ህይወታቸው ከቱሪዝም በሚያገኝ ገቢ ላይ የተመሰረተ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ባጠራቀሙት ገንዘብ ነው እየኖሩ ያሉት። አንዳንዶች ያጠራቀሙትን ገንዘብ ጨርሰው ለችግር ተጋልጠዋል። ለምሳሌ እኔ በእጄ የነበረ ገንዘብ በመሟጠጡ ሥራ ለመቀየር ተገድጃለሁ።"
በሆቴል፣ ባህላዊ እቃዎችን ሰርተው የሚሸጡ፣ በማኅበር በመደራጀት ፈረስ የሚያከራዩ፣ እና ሌሎችም ሥራ ፈትተው ለችግር መጋለጣቸውን አወል ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA
ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ታጥቷል
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከውጭ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ቱሪዝሙም ተጎድቶ ቆይቷል ያሉት የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የብሔራዊ ሙዚየም፣ የአንድነት ፓርክን የመሳሰሉ ስፍራዎች ተዘግተው በመቆየታቸው የተነሳ ለትምህርታዊም ሆነ ለመዝናናት የሚመጡ ጎብኚዎች በዚሁ ምከንያት መቅረታቸውን ያስታውሳሉ።
አሁንም ቢሆን እንቅሳቃሴው ክፍት ሲሆን በፍጥነት ይሻሻላል ብለን የምንጠብቀው የውጭ አገር ጎብኚዎችን ሳይሆን የአገር ውስጦቹን ነው ሲሉ አቶ ስለሺ ተስፋቸውን ይናገራሉ።
ኃላፊው እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ ስጋት ቀንሶ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሲፋጠን ይሻሻላል ብለው የሚጠብቁት የአፍሪካ ቱሪዝም ነው።
ለአፍሪካ ቱሪስቶች የእንጦጦ፣ የሸገር እና የአንድነት ፓርክን የመሳሰሉት አዳዲስ መዳረሻዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጋር ተደምረው በርካታ ጎብኚዎችን እንደሚያመጡ ተስፋ አድርገዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የሥራ እድሎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል ያሉት አቶ ስለሺ፤ በቱሪዝም ዘርፉ ተፈጥረው የነበሩ የሥራ እድሎች ሆቴሎች፣ የባህል ምግብ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች፣ በየቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ያሉ የአስጎብኚ አገልግሎቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች በሙሉ መጎዳታቸውን ይጠቅሳሉ።
የኮቪድ-19 ከቱሪዝም ይገኝ የነበረውን ጥቅም ማሳጣቱን ሲገልፁም ድርጅታቸው በግሉ ያጣውን በማሳየት ይጀምራሉ።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ቀርጾት የነበረው "የኩነት ቱሪዝም ብራንድ"ን፣ በጀርመን ፍራንክፈርት ለማስተዋወቅ ይዞት የነበረውን እቅድ መሰረዙን ይገልፃሉ።
እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን ለማካሄድ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ይዘውት የነበረው በየክልሉ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚሰጧቸው ስልጠናዎች መቋረጣቸውንም ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር ስትወዳደር የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ካስቻሏት ነገሮች መካከል አንዱ የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት መስህቦቿ፤ ሌላኛው ርካሽ የዋጋ ተመን፣ ሦስተኛው ደግሞ የደኅንነት ጉዳይ አስተማማኝ ስለነበር እንደሆነ አቶ ስለሺ ያነሳሉ።
ስለዚህ ቱሪዝምና ሰላም ያላቸውን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነት በማንሳት፤ ይህንን ጠብቆ ማቆየት ለመዝናናት፣ ለእረፍት እንዲሁም ለቤተሰብ ጥየቃ በመምጣት የተለያዩ መስህቦችን በመዲናዋም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችን የሚጎበኙ ሰዎችን ማበረታታት ተገቢ መሆኑን ያሰምሩበታል።



















