ዝክረ ጥላሁን ገሠሠ በ80ኛ የልደት በዓሉ

የፎቶው ባለመብት, Zekeria
- ፀሐፊ, በዘከርያ መሐመድ*
- የሥራ ድርሻ, ጋዜጠኛና ፀሐፊ
በመስቀል በዓል ዕለት የተወለደው ታላቁ የሙዚቃ ሰው ጥላሁን ገሠሠ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ዛሬ 80 ዓመት የልደት በዓሉ ነበር። ቢቢሲ አማርኛ የጥላሁን ገሠሠን 80ኛ ዓመት የልደቱ ዕለት እንዲህ ዘክሯል።

ፋሺስት ኢጣሊያ፣ ኢትዮጵያን ወርራ የቆየችባቸው ዓመታት እና የ1932 ክረምት አልፈው፣ የነጻነት ብሥራት በተሰማበት ዓመት፣ በወሊሶ አውራጃ፣ ጎሮ ወረዳ፣ ሶየማ ቀበሌ፣ "መስከረም 17 ቀን 1933፣ ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ወ/ሮ ጌጤነሽ [ጉርሙ] ኢተኣ ወንድ ልጅ ተገላገለች" ይላል በአቶ ፈይሣ [ኃይሌ] ሐሰና ቤኛ ከ1934 ጀምሮ የተከተበው የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ።
አቶ ፈይሣ ከአያታቸው ቤኛ ትክሴ እየጠየቁ የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻውን መጻፍ የጀመሩት፣ "አያት ቅድመ አያቶቻችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደ ነበሩ፣ ምን ይሠሩ እንደነበር" ለማወቅና ታሪካቸውን ጽፎ ለማኖር በመሻት ነበር።
የአያት ቅድመ አያቶች ታሪክ ተከትቦ፣ የቤተሰቡ ታሪክ እርሳቸው በውል የሚያውቁት ትውልድ ዘንድ ከደረሰ በኋላ ያለውን ታሪክ እራሳቸው እየጻፉ ቀጠሉ።
ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት እስከ 1985 ድረስም፣ በቤተሰቡ ውስጥ ዐበይት የኾኑ ሁነቶችን መዝግበው አኖሩ።
በዚህ የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ታሪካቸው ከተከተበላቸው የቤተሰቡ አባላት መካከል፣ አቶ ፈይሣ የቤተሰብ ታሪክ መጻፍ ሲጀምሩ ገና የአንድ ዓመት ሕጻን የነበረው የቤተሰቡ አባል ይገኝበታል።
ስለዚህ ሕጻን የሰፈረው ማስታወሻም፣ ሕጻኑ አንድ ዓመት ሲሞላው፣ ከቤተሰቡ ጋር ቅርበት በነበራቸው ቀኛዝማች መኮንን መሸሻ አማካይነት በወሊሶ ከተማ፣ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተጠመቀ።
በዚህም ጊዜ ቀኛዝማች መኮንን "ጥላሁን" ብለው ስም አወጡለት ይላል። እንደተወለደ፣ አያቱ ወ/ሮ ነገዬ አብደላ ያወጡለት ስም ደገፋ ነበር።
የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻው ይቀጥላል። ጌጤነሽ በሶየማ በወጉ ከታረሰች በኋላ፣ ከባለቤቷ አቶ ገሠሠ ወልደኪዳን ጋር፣ የእናቷ የወ/ሮ ነገዬ አብደላ ሌላ ርስት ወደሚገኝበት አመያ፣ ልጃቸውን ይዘው በመሄድ በዚያ መኖር ጀመሩ።… ለአምስት ዓመታት አብረው ከኖሩ በኋላ ግን፣ በ1938 ወ/ሮ ጌጤነሽ በጊዜው ወዴት እንደኾነ ወዳልታወቀ ስፍራ ጠፋች።
አቶ ገሠሠ በበኩሉ በአመያ ለመሠረተው ኑሮ ምክንያት የሆነችው ባለቤቱ ጥላው ከሄደች በኋላ፣ በወ/ሮ ነገዬ ርስት ላይ መቆየትን ስላልወደደ ይመስላል፣ ሕጻኑን ለአያቱ ትቶ እርሱም [በጊዜው ወዳልታወቀ ስፍራ] ኮበለለ።

የፎቶው ባለመብት, Zekeria
የጥላሁን መተውና እንጉርጉሮ
በ1939 ጥላሁን በቀኛዝማች መኮንን ጥያቄ እና በአቶ ፈይሣ ምክር፣ ወሊሶ ከተማ በሚገኘው ራስ ጎበና ዳጨው ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ።
አያቱ ወ/ሮ ነገዬም፣ ለእርሱ ሲሉ በወሊሶ ቤት ተከራይተው መኖር ጀመሩ። …የወላጆቹ እርሱን ጥለው መጥፋት ሳይፈጥርበት እንዳልቀረ ከሚገመተው የመተው (Abandonment)፣ ትኩረት የመነፈግ አልያም የብቸኝነት ስሜት ጋር ሲታገል ከመቆዘም ይልቅ ወደ እንጉርጉሮ ያደላ ነበር።
በራስ ጎበና ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ፣ "'ሆያ ሆዬ የሚሉትን በማየት' እና 'ጠላታችን ወደቀ፣ ፍፁም ጠፋ ሙሶሎኒ' የምትለዋን መዝሙር በማዳመጥ" አጥንቶ ይዘምር ነበር። ይህን ያዩት የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር (ሱዳናዊው) ሚስተር ሸዳድ በአድናቆት አበረታቱት። ወንድማቸው ማህሙድ ሳንሁሪም ቤቱ እየወሰደ በሸክላ የተቀረፁ ዘፈኖችን አስደመጠው። የሰማውን በቃሉ ይዞ ማንጎራጎር ሥራው ሆነ። ከሙዚቃ ጋር ተዋወቀ።
በቤተሰባዊ ሕይወቱ ላይ የተከሰተው ነገር እንኳንስ ድምጽን ከፍ አድርገው ለሰው ሊነግሩት፣ በአዕምሮ ሲያሰላስሉት ስሜትን የሚጎዳና፣ ተስፋ የሚያጨልም ነበር።
ነገር ግን በዚህ የተጎዳ ስሜት አንገቱን ደፍቶ እንዳይቀር፣ አንደበቱን ለጉሞ በሐዘን እንዳይኮማተር፣ ጮኽ ብሎ ቢዘምርበት አድማጭ የሚስብ፣ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር 'ሆያ ሆዬ' ቢጨፍር 'ለመሪነት' የሚያበቃ፣ በልበ ሙሉነት ሰው ፊት ቆሞ ቢያዜም የሰዎችን ቀልብ የሚጠራ ውብ ድምጽን ፈጣሪ ሰጠው። ጥላሁን ይህን ተፈጥሯዊ ፀጋ በታላቅ ፍቅር ተቀበለ።
ወደ አዲስ አበባ
የአምስት ዓመት ሕጻን ሳለ ድንገት የጠፋችው ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ጌጤነሽ ከአምስት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ተገኘች።
በዚህም ምክንያት ከእናቱ ጋር እንዲገናኝ ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1943 ወደ አዲስ አበባ መጣ። ከእናቱ ጋር ከተገናኘ በኋላ ትምህርቱን ይቀጥል ዘንድ ወሊሶ እንዲመለስ ቢደረግም፣ ልቡ ወደ አዲስ አበባ የሸፈተበት ጥላሁን ከሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ፣ በ1944 አዲስ አበባ ጠቅልሎ ገባ።
አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ፣ የድምጻዊነት ሕይወቱን በይፋ ይጀምር ዘንድ በ1947 ሀገር ፍቅር ማኅበር ተቀጠረ።
በሀገረሰብ የሙዚቃ ቡድኖች በተዋቀረው የሀገር ፍቅር ቆይታው፣ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ መሠረታዊ ቅኝቶች ጋር ለመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል።
በሀገር ፍቅር ማኅበር የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ቆይታው፣ 'ጥላ ከለላዬ'፣ 'ጽጌረዳ ነሽ'፣ 'ደጉ ንጉሥ' እና 'ፍቅሬ ሰውነቴ' የተሰኙ ዘፈኖችን በመዝፈን ከሕዝብ ጋር ተዋወቀ።

የፎቶው ባለመብት, Zekeria
ስኬታማ የሙዚቃ ሕይወት
የጥላሁን ገሠሠ ተፈጥሯዊ ክህሎት ፍንትው ብሎ መውጣት የቻለው ግን በ1949 በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከተቀጠረ በኋላ ነው።… ከ1950ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጥላሁን በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አጃቢነት አያሌ ድንቅ ዘፈኖችን ተጫውቷል።
ንጉሣዊው ሥርዓት ወድቆ፣ በወታደራዊው ደርግ ዘመን ኦርኬስትራው የአንደኛ ክፍለ ጦር ወይም የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ባንድ ከተባለ በኋላም፣ ጥላሁን የባንዱ ኮከብ ድምጻዊ ሆኖ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ ዘልቋል።
በረጅሙ የሙያ ዘመኑ፣ ጥላሁን ከክብር ዘበኛ/ማዕከላዊ ዕዝ በተጨማሪ በተለያዩ ኦርኬስትራዎችና ባንዶች ታጅቦ ዘፍኗል።
"ጩኸቴን ብትሰሙ"፣ "እኔ ነኝ ወይ አንቺ"፣ "አይከዳሽም ልቤ" እና "ማስታወሻ"ን በምድር ጦር ኦርኬስትራ አጃቢነት ሲጫወት፤ "ሰው ማንን ይመስላል" እና "ስማ" የተሰኙ ሁለት ዘፈኖችን በፖሊስ ኦርኬስትራ፤ "በይ ደህና ክረሚ" እና "ስንብት" የተሰኙ ሁለት ዘፈኖችን ደግሞ በ"ሬይንቦው" ባንድ አጃቢነት ተጫውቷል።
በተጨማሪም "የኔ ፍላጎቴ" እና "በደህና እስኪገጥመን"ን በኤግዚቢሽን ባንድ፤ "ኩሉን ማን ኳለሽ"፣ "አለኝታዬ"፣ "ላንቺ ብዬ"፣ "ስትሄድ ስከተላት"፣ "ትዝ አለኝ የጥንቱ" እና "የሀገሬ ሽታ"ን በሙላቱ አስታጥቄ [ኦል ስታር ባንድ] አጃቢነት ተጫውቷል።
"ውበትሽ ይደነቃል"፣ "ጽጌረዳ"፣ "አካም ነጉማ"፣ "የቆለኛ ልጅ"፣ "ፍቅሬ ሆይ ያላንቺ" እና ሌሎች አምሥት ዘፈኖች የሚገኙበትን ካሴት ከአይቤክስ ባንድ ጋር ነው የሠራው።
የአይቤክስ ባንድ ከፈረሰ በኋላ በ197ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከተመሠረተው ሮሃ ባንድ ጋር፣ በ1980 "የ13 ወር ፀጋ" እና በ1984 ደግሞ "እንቆቅልሽ" የተሰኙትን ካሴቶች ሠርቷል።
በ1981 ጥላሁን፣ ብዙነሽ፣ ማህሙድ እና ሒሩት በጋራ ያወጡት ካሴትም በሮሃ ባንድ ነው የታጀበው። የ"ከሌለህ የለህም" እና የ"ይቺ ናት ጨዋታ" አልበሞች የታጀቡት ደግሞ በዋሊያስ ባንድ ነው።
ለአራት አስርት ዓመታት በዘለቀ የሙያ ሕይወቱ ጥላሁን የተጫወታቸው ዜማዎች፣ የየዘመኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ማኅደር ለመሆን በቅተዋል።
በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ከክቡር ዘበኛ ጋር የተጫወታቸው ዘፈኖች ውበት፣ ለዛ እና ጣዕማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍቅርን ከመስበክ ባሻገር ማኅበረሰብን ወደ ማስተማር የሚያደሉ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Zekeria
በዘመነ ደርግ፣ ጥላሁን ብዙ የፍቅር ዜማዎችን ከመጫወቱ በተጨማሪ የዚያኑ ያህል የበዙ ሀገራዊነት የሚጎላባቸው ዘፈኖች ተጫውቷል።
እርግጥ በወቅቱ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደነበረች በማሰብ፣ ዘፈኖቹን "ሀገራዊ" ከማለት ይልቅ "የደርግ መንግሥት ጦረኛ ፖሊሲ ነፀብራቅ ነበሩ" የሚሉ አሉ። ይህ አስተያየት መሠረተ ቢስ የሚባል አይደለም።
ጥላሁን በረጅሙ የድምፃዊነት ሕይወቱ በቁጥር ብዙ ዘፈኖች ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮችም ላይ ዘፍኗል። በሕይወት ዘመኑ የተጫወታቸውን ዘፈኖች ትክክለኛ ቁጥር ደፍሮ ለመናገር ያስቸግራል።
ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሳለ የዘፈናቸው፣ አልያም በመድረክ የተጫወታቸው፣ ነገር ግን የመቀረጽ ዕድል ያላገኙ ብዙ ዘፈኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል።
በርዕሰ ጉዳይ ረገድ ሀገር ፍቅር ማኅበር ሳለ ከዕድሜውም ትንሽነት ይሆናል፣ ሀገር ወዳድነትን የሚመለከቱ ዘፈኖችን ይጫወት የነበረ ሲሆን፣ ክብር ዘበኛ ከገባ በኋላ ደግሞ ፍቅርንና ውበትን ከሚያሞግሱ ውብ ዘፈኖች ባሻገር የተለያየ ማኅበራዊ ይዘት ያላቸው ብዙ ዘፈኖችን ተጫውቷል።
ከእነዚህ ውስጥ ስምንት ያህል የተመረጡ ዘፈኖች በብሔረ ጽጌ መናፈሻ ተቀርፀው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1964 በቴሌቪዥን ለሕዝብ ቀርበዋል።
በ1966ቱ የሥርዓት ለውጥ ማግሥት የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ የአንደኛ ክፍለ ጦር የሙዚቃ ባንድ ከመባሉ በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታት ጥላሁን በተቋሙ ባንድ የዘፈናቸው ዘፈኖች በይዘታቸው ከፖለቲካ ለውጡ ጋር ተያያዥ ነበሩ።
ወታደራዊው ደርግ የ"ኅብረተሰብአዊነት" ርዕዮት እከተላለሁ ካለ በኋላ ኪነት አንዴ "ለጭቁኑ መደብ"፣ አንዴም "ለአብዮቱ መቆም" አለባት ተብሎ፣ በጊዜው መንግሥት ለሚያካሂዳቸው ሀገር አቀፍ መርሃግብሮች ሁሉ የማጀቢያ፣ አልያም ሕዝብ የማነቃነቂያ ዘፈኖች ይደረሱ ስለነበር ጥላሁንም በዚሁ መንፈስ "ለዕድገት በሕብረት"ን በመሰሉ ኅብረ ዝማሬዎች ላይ መሪ ድምፃዊ ሆኖ ተጫውቷል።
በሌላ በኩል ግን በግሉ በተለይ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ መሪ ከነበሩት አቶ ተስፋዬ ለማ ጋር በ1968 እና 69 የሠራቸው ዘፈኖች የፍቅር ዘፈን ቃና ቢኖራቸውም፣ አብዛኞቹ በሀገራዊ ጉዳይ ዜጎችን የሚሞግቱ፣ አንዳንዴም በሒስ የሚቆነጥጡ ነበሩ።
ከ1969ኙ የሶማሊያ ወረራ በኋላ ባሉት ዓመታት ጥላሁን በማዕከላዊ ዕዝ (የአንደኛ ክፍለ ጦር ሙዚቃ ባንድ) ታጅቦ የወታደር ወኔን የሚያነቁ፣ አልያም ሀገር ወዳድነትን የሚያጎሉ በዛ ያሉ ዘፈኖችን ተጫውቷል።
ምንም እንኳ እነዚህ ዘፈኖች በጦር ሜዳ የሠራዊቱን ወኔ በማነሳሳት ዓላማ የተዘጋጁ ቢሆኑም፣ በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ጥበባዊ ለዛ የራቃቸው ግን አልነበሩም።
በዚህ መንፈስ ጥላሁን ከተጫወታቸው ሀገራዊ ዘፈኖች ውስጥ በ1969 የተጫወተው "አጥንቴም ይከስከስ" እንዲሁም በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ ለሕዝብ የቀረበው "ቃል ኪዳን" የተሰኘው ግጥሙ በሻምበል ክፍሌ አቦቸር የተጻፈ ዘፈን ለየት ብለው ይታወሳሉ።
"ቃል ኪዳን" ባሕር ማዶ የሚኖሩ ወገኖች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በጥላሁን ጥበባዊ አንደበት የቀረበ "የእናት ሀገር ጥሪ" ነበር ማለት ይቻላል።
በቴሌቪዥን ከተቀረፁ የጥላሁን ድንቅ ዘፈኖች ቀይ ሸሚዝ ለብሶ በልዩ ተመስጦ፣ "ለወሬም አይመች" የሚሰኘውን ዘፈን ሲጫወት የሚታይበት በሚሊዮኖች ትውስታ ውስጥ የቀረ ነው።
በሱዳን የቴሌቪዥን ጣቢያ የተቀረፀው ይህ ዘፈን ዜማው ለሱዳናውያን እንግዳ ካለመሆኑም በላይ፣ ጥላሁን አረብኛም አጥንቶ በሁለት ቋንቋ በልዩ ስሜት ስለተጫወተው በጎረቤት ሱዳን ጭምር ተወዳጅነትን አትርፏል። ጥላሁን የኢትዮጵያና የሱዳን ወዳጅነትን የሚያጎለብት "ጤና ይስጥልኝ" የሚሰኝ ዘፈንም አረብኛ ቀላቅሎ ዘፍኗል።

የፎቶው ባለመብት, Zekeria
ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ ሆኖ በሕዝብ ውስጥ የኖረው ጥላሁን፣ ሀገሩ ኢትዮጵያን የወላጆቹ ምትክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደግሞ ወንድምና እህቶቹ አድርጎ የሚያስብ፣ "የእኔ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው" የሚል ልባዊ እምነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገር ሰው ነበር።
ጥላሁን በሚያዘያ ወር 1985 አንገቱ ላይ በስለት የመወጋት አደጋ ደርሶበት ነበር። ነገር ግን ይህ በድምጻዊነት ከመቀጠል አላገደውም።
"ወገን አለኝ"ን ጨምሮ ከ1980ዎቹ በኋላ በድጋሚ ተጫውቶ ካሰቀረጻቸው ነባር ዜማዎቹ የተወሰኑት የተቀረፁት አደጋው ከደረሰበት በኋላ ነው። በዚህ ዘመን ከተጫወታቸው ዜማዎች አንዳንዶቹ በተለይም "ፍቅርሽ ነው የጎዳኝ" እና "አይ ዘመን" የተሰኙት ዘፈኖች ከታላላቅ ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ለመሆን በቅተዋል።
ጥላሁን ከ1990ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ጀምሮ፣ ለድምጻዊነት ዘመኑ የመጨረሻውን አልበም ለሕዝብ በምርቃት መልክ ማቅረብ ፍላጎቱ ነበር። ይህን ፍላጎቱን ከሞላ ጎደል "ቆሜ ልመርቅሽ" በተሰኘው አልበሙ እውን አድርጎታል።
በሀገር ፍቅር ማኅበር "ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ"ን በመጫወት በይፋ የተጀመረው የጥላሁን የግማሽ ምዕተ ዓመት የሙዚቃ ሕይወት "ቆሜ ልመርቅሽ" በሚሰኘውና ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ባስቀረፀው የመጨረሻው አልበም ነው የተደመደመው።
የጥበብ ሕይወቱን ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ አሟሽቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ ኖሮ፣ ስለ ኢትዮጵያ የዘመረ ውብ ድምፁን፣ ጣፋጭ ቅላፄውን፣ አቻ ያልተገኘለት የመድረክ አቀራረብ ጥበቡን አሻራ፣ እንዲሁም ልዩ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅሩን አውርሶ የሄደው ጥላሁን ገሠሠ፣ በድምፁ ሐውልቱን የተከለ ታላቅ ከያኒ ነበር።. . .
በኅልፈቱ ማግሥት፣ ሐሙስ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ እርሱን በክብር ለመሸኘት አደባባይ የወጣበት ትዕይንት፣ ጥላሁን ገሠሠ በእርግጥም የሕዝብ ልጅ መሆኑን ያሳየ ነበር።
"ቆሜ ልመርቅሽ" የተሰኘው የመጨረሻ አልበሙ ለሀገሩ እና ለወገኖቹ ያቀረበው የድኅረ ኅልፈት የምሥጋና ቃሉ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
*ዘከርያ መሐመድ ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት እየሠራ ያለ ባለሙያ ሲሆን፤ የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክን በጥልቀት የዳሰሰ "ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር" የተሰኘ ተነባቢ መጽሐፍ አሳትሟል።














