ለንደን ማራቶን፡ አትሌት ሹራ ቂጣታ ከኬንያዊው ኪፕቾጌ የማራቶን ድል እንዲነጥቅ የረዳው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤሉድ ኪፕቾጌን ለማሸነፍ እንዴት ያለ ወኔ ይበቃ ይሆን? ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች የሮጠውን ብርቱ አትሌት ለማሸነፍ ምን ሲደረግ ይቻላል?
ጥብቅ ልምምድ ወይስ ተሰጥኦ? ለለንደን ማራቶን አሸናፊው ሹራ ቂጣታ ግን ጥሩ ቁርስ በቂ ነው።
ባለፈው ዓመት በዩኬ ዋና ከተማ አራተኛ በመሆን ነው ያጠናቀቀው። ያኔ ኬኒያዊው ኪፕቾጌ ነው ያሸነፈው።
በወቅቱ ሹራ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ባዶ ሆዱን መሮጡን፣ ለቁርስ ፍራፍሬ ብቻ መመገቡን ገልጾ ነበር።
ሹራ በወቅቱ 35 ኪሎ ሜትሮች ከሮጠ በኋላ የተሰማውን ሲያሰፍር "ሆዴ ከጀርባዬ ጋር የተጣበቀ መስሎኝ ነበር፤ ሞርሙሮኝ ነበር" ብሏል።
በዚህ ዓመት ከስህተቱ የተማረው ሹራ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ጥሩ ምግብ ወሳስዷል።
ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ " ሁሉንም ነገር ተመግቤያለሁ" ብሏል።
"ሾርባ፣ ዳቦ፣ እንቁላል እና እርጎ ወስጃለሁ፤ አቅም የሚሆነኝንና ውድድሩን በጥሩ ጉልበት መፎካከር የሚያስችለኝን ሁሉ ወስጃለሁ።"
ውድድሩ ደግሞ ከ2014 ጀምሮ በማራቶኑ መስክ አልበገር ያለውን ኬንያዊ ማንበርከክን ያካተተ ነበር።
ኪፕቾጌ የዋዛ አትሌት አይደለም። በኦሎምፒክ መንደር ስሙ በደማቅ ተጽፏል። የዓለም ክብረ ወሰን በእጁ ነው።
የ35 ዓመቱ ኪፕቾጌ በለንደን ለአምስተኛ ጊዜ ድልን ለመቀዳጀት ጉልበቱን አበርትቶ ሞራሉን አደርጅቶ ነው የተገኘው።
የዓለም መገናኛ ብዙኃንም ስሙን ደጋግመው ያነሳሉ። ምስሉን ደጋግመው ያሳያሉ። ጋዜጦች የፊት ገጻቸው ላይ አትመውታል።
ለንደን ለኪፕቾጌ፣ ኪፕቾጌም ለለንደን መሃላ ያላቸው ይመስላል።
ኪፕቾጌና ለንደን ግን ያላቸው ቃል ኪዳን ፈረሰ። መፍረስ ብቻ ሳይሆን ስምንተኛ ወጣ። ከፊት የፈለጉት ከኋላ አገኙት። በኋላም ጆሮውን አሞት እንደነበር አስረዳ።
ለረዥም ርቀት ሩጫ እርጥበታማ አየርና ቅዝቃዜ ምቹ አይደለም።
ሹራ የገባበት ሰዓትም፣ ሁለት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ41 ሰከንድ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ሹራ ግን እንደውም አየሩ ረድቶኛል ሲል ያምናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እኤአ ከ2013 ወዲህ የለንደን ማራቶንን ሲያሸንፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆነው ሹራ "ሲዘንብ በጣም ደስ አለኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በከባድ ዝናብ ውስጥ ነው ልምምድ ስሰራ የነበረው" ይላል።
"አንድ ቀን ሶደሬ ለልምምድ ሄድኩኝ፣ ከባድ ዝናብ እየዘነበ ከተማው በጎርፍ ተጥለቅልቋል። አሰልጣኜ እኔን ለማዳን መምጣት ሁሉ ነበረበት" ሲል የነበረውን የልምምድ ሁኔታም ያስታውሳል።
"የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት፣ ቤት አልተቀመጥኩም። ለአምስት ወራት ያህል ከአሰልጣኜ ጋር ልምምድ ስሰራ ነበር። ይህን ድል ኪፕቾጌን ማሸነፌ ልዩ አያደርገውም፤ ጠንክሬ መስራቴ ነው ልዩ የሚያደርገው።"
ቀነኒሳ በቀለ ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ ከውድድሩ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ በኪፕቾጌና በቀነኒሳ መካከል ይኖራል ተብሎ የታሰበው ፍልሚያ ሳይሳካ ቀረ።
ስለዚህ ማንም የቀነኒሳን አገር ልጅ፣ ሹራን ከኪፕቾጌ ጋር አነጻጽሮ ለማወዳደርና የዜና ፍጆታ ለማድረግ ፍላጎት አላሳየም።
ሹራም ቢሆን "ሁሉም ትኩረቱ የነበረው ኪፕቾጌ እና ቀነኒሳ ላይ ነበር፤ እኔን ዞርም ብሎ ያየኝ አልነበረም" ሲል ይገልጻል።
"ለራሴ ለዓለም ሌላ ሻምፒዮን መኖሩን አሳያለሁ ብዬ ነገርኩት፤ እናም ይህ ስሜት ነው እስከመጨረሻው ድረስ በራስ መተማመንና በሙሉ አቅም እንድቀጥል የረዳኝ።"
ሹራ በበርካታ የስፖርቱ አድናቂዎች ዘንድ የሚታወቅ ስም አይደለም። ነገር ግን በለንደን ሁለት ጊዜ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቅቋል፣ በ2018 ደግሞ በኒውዮርክ ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በመግባት የራሱን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
በዙሪያው ያሉ አትሌቶች የ24 ዓመቱን ሹራ ዝምተኛ ግን በራስ መተማመን ያለው ሲሉ ይገልፁታል።
የሹራ ወኪል ሁሴን ማኬ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ፤ " በጣም መልካም፣ የሚፈልገውን የሚያውቅ፣ ቤተሰቡን የሚያስቀድም ሰው ነው። እናም የእርሱ ምርጥ ነገሩ በራስ መተማመኑ ነው" ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
"በለንደን በራሱ በብርቱ ተማምኖ ነበር፤ እናም ወደ ውድድር ሲገባ ውድድሩ ውስጥ ስላሉት አትሌቶች ግድ አልሰጠውም፤ ያም አሁን ላገኘው ሻምፒዮናነት ረድቶታል። ተስፋ አደርጋለሁ በዚሁ ይቀጥላል።"
ሹራ አትሌቲክስን የተዋወቀው በትምህርት ቤት ውስጥ ነው። ኋላም እኤአ ከ2015 ጀምሮ አሰልጣኝ ሃጂ አዲሎ በአዲስ አበባ እያሰለጠኑት ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በጣም ደፋር አትሌት ነው፤ እናም ሁልጊዜ አቅሙን እስከቻለ ድረስ ይጠቀማል" ይላሉ አሰልጣኙ።
አሰልጣኝ ሃጂ ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ቀናት ሲቀራቸው የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው በምርመራ በመረጋገጡ ድሉን በአካል ተገኝተው ለማጣጣም አልታደሉም።
ቢቢሲ ሹራን እንዴት ማሰልጠን እንደጀመሩ ሲጠይቃቸው "ሹራ ከመጣበት አካባቢ የሆነ ሰው ከኔ ጋር አብሮ ይሮጥ ነበር። እናም እኔ ወዳለሁበት ካምፕ አምጥቶት እስቲ እየው አለኝ። ሞከርነው፤ ጥሩ ነበር ግን ፅናቱንና ፍጥነቱን ማሻሻል ነበረበት" በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
"በሶስት ወር ውስጥ፣ በጣም በርካታ ነገር አሻሻለ፤ እናም የመጀመሪያውን ማራቶን እንዲካፈል ወደ ሻንጋይ ላክነው።"
ሹራ የተገኘው ሰባት ልጆች ካሏቸው ገበሬ ቤተሰቦች ነው።
"ትምህርት በጣም እወድ ነበር፤ ዶክተር አልያም ፓይለት ነበር መሆን የምፈልገው። ነገር ግን ከድሃ ቤተሰብ ስለሆነ የተገኘሁት ቤተሰቦቼን ለመርዳት ትምህርቴን ማቋረጥ ነበረብኝ" በማለት ልጅነቱን ያስታውሳል።
"አንድ ቀን ዝነኛ እሆናለሁ፤ አለምን እዞራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለ እርሱ እና ስለድሉ በትዊተር ሰሌዳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መጻፋቸውን በመግለጽ፤ "አስቤ የማላውቀውን ህይወት ነው እየኖርኩ ያለሁት" ይላል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ሹራ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ በወንዶች ማራቶን ለሁለት አስርታት ያጣችውን ድል መመለስ ይፈልጋል።
"ለአገሬ እና ለልጆቼ ጥሩ ትዝታ እንዲሆን የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት እፈልጋለሁ። ከዚያም 'አባታችን የኦሎምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊ ነው' ይላሉ።"















