ኮሮናቫይረስ፡ በጨርቅ መልኩ የተዘጋጀ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናን የሰራው ኢትዮጵያዊ

ከጨርቅ የተሰራው የእጅ መታጠቢያ ሳሙና

የፎቶው ባለመብት, FISAL

የምስሉ መግለጫ, ከጨርቅ የተሰራው የእጅ መታጠቢያ ሳሙና

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሳደረው ተፅዕኖ ባሻገር የሰውን የሕይወት ዘይቤን ለውጦታል። ከዚህ ቀደም ከምናደርገው በበለጠ እጅን መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ የምንገለገልባቸውን የእጅ ስልኮችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ዘወትር ማፅዳት ለአፍታ እንኳን የማይዘነጋ ሆኗል።

እጅን መታጠብ ደግሞ ወረርሽኙን ከምንከላከልባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በሽታው መጀመሪያ በተከሰተበት ውቅት እጅን ደጋግሞና በሚገባ መታጠብን ለማስተማር በየቦታው ዘመቻዎች ነበሩ።

ይሁን እንጂ ብዙም አልዘለቀም። አንድም በሰው የአጠቃቀም ልምድ ምክንያት ለበሽታው ይበልጥ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች በመስተዋላቸው፤ በሌላ በኩልም በውሃ እጥረት እንዲሁም ለእጅ መታጠቢያ የተቀመጠው ሳሙና ከቦታው እየጠፋ የተቸገሩም ብዙዎች ነበሩ።

ታዲያ ይህ ያሳሰበው ፈይሰል ያሲን አንድ ፈጠራ አበርክቷል።

ይህ የፈጠራ ሥራ የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያስችሉና በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ከተመዘገቡ ስምንት የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን የተቋሙ የፓተንት መርማሪ አቶ ጌታቸው ጣፋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

መስመር

በግል ሥራ የሚተዳደረው ፈይሰል በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል።

ለፈጠራ ሥራው ማይ ሶፕ [የእኔ ሳሙና] የሚል ስያሜ ሰጥቶታል - ፈይሰል።

'ማይ ሶፕ' ኮሮቫይረስን ጨምሮ ሌሎች ተህዋስያንን ለመከላከል የሚረዳ ሲሆን፤ ሳሙናው ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሎ የሚወገድ ከመሆኑ በተጨማሪ ለመያዝ አመቺ በሆነ መልኩ የተዘጋጀ ነው።

ይህ ሳሙና በፀረ ተህዋስ ኬሚካል የተነከረ ጨርቅ [ዋይፕስ] አይነት የተዘጋጀ ነው።

እንዴት ይዘጋጃል?

በመጀመሪያ እንደ ፈሳሽ ሳሙና የሚዘጋጅ ውህድ አለ።

ውህዱ አልኮል፣ ሶዲየም ላውሮት ሰልፌት [ኤስኤልኤስ] የነጭ ሽንኩርት ጭማቂና ግሪስሊን አለው። ግሪስሊኑ እጃችን እንዳይደርቅና ልስላሴ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ይላል- ፈይሰል።

ይህን ውህድ ለማዘጋጀት ከሳይንሳዊ ጆርናል እና ቬትናም ውስጥ ከተደረገ ጥናት ላይ ሃሳቡ እንደተወሰደ የሚናገረው ፈይሰል፤ "ቬትናም ውስጥ የነጭ ሽንኩርት ጭማቂን በመጠቀም የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመቀነስ አገልግሎት ላይ እንደዋለ ጥናቱ ያስረዳል" ይላል።

ፈይሰል እንደሚለው የውህዶቹ መጠን የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህንን በላብራቶሪ ለመፈተሽ በሒደት ላይ መሆኑንም ተናግሯል።

ከዚያም 'ዋይፕሱን' በተዘጋጀው ውህድ ፈሳሽ ሳሙና ውስጥ በመንከር በእርጥብና በደረቅ መልኩ በማሸግ ለገበያ ይቀርባል። አንድ ሰው ይህንን የእጅ ማፅጃ መጠቀም ሲፈለግ አንዷን የ'ዋይፕስ' ቅጠል በውሃ አርጥቦ እጅን በማሸት መታጠብ ይችላል - ልክ እንደ ሳሙና።

ይህ የፈጠራ ሥራ ከሌላ የሚለየው በቀላሉ በኪስ ለመያዝ አመቺ በሆነ መንገድ በመሰራቱ ነው።

ፈይሰል እንደሚለው ገበያ ላይ ያሉት 'ዋይፕሶች' ሳሙናነት የላቸውም። የሚዘጋጁትም በእርጥበት መልክ ብቻ ነው። ይህ የፈጠራ ሥራ በደረቅ መልክና በኪስ መያዝ በሚያስችል መልኩ ነው የሚዘጋጀው። ሳሙናን ይዞ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ቦታ ላይ ይህ አያያዙን ቀላል ያደርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሳሙናው ለአንድ ሰው አገልግሎት ብቻ የሚውል በመሆኑ፤ ግለሰቡ/ግለሰቧ ለራሳቸው ብቻ የሚሆን ይዘውት የሚንቀሳቀሱት አንድ የግል ሳሙና ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ፈይሰል እንደነገረን ከሆነ የእጅ ማፅጃው ታሽጎ እስከሚወጣ ድረስም የእጅ ንክኪ የለውም።

የመጥረጊያ ጨርቁን [ዋይፕሱን] በደረቅ መልኩ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ?

ደረቅ ሆኖ መዘጋጀቱ ተማሪዎች በቦርሳቸው እንደሚይዙት የመማሪያ ቁሳቁስ ትምህርት ቤት ይዘውት ለመሄድ ምቹ ነው የሚለው ፈይሰል፤ እንደ ሳሙና ስለሚያገለግልም አንዱን እየመዘዙ እጃቸውን ሊታጠቡበት ይችላሉ።

አንዱ እሽግም 24 ፍሬ ስለሚይዝ ለብዙ ጊዜ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

ተጠቅሞ የሚጣለው ጨርቅም ቧንቧውን ለመዝጋትና ለመክፈትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የመኪና በርንም በዚያ ለመክፈት ያገለግላል።

ከዚህም ባሻገር ላብቶፕና ስልክን የመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎችን ለማፅዳት ይውላል። ደረቅ በመሆኑም በቁሶቹ ውስጥ ፈሳሽ ገብቶ በስክሪኖችና ኤሌክትሪክ ገመዶች ላይ የሚያደርሰውን መሰነጣጠቅና የተለያየ አደጋ አይኖርም። በመሆኑም ንክኪ የሚበዛባቸውን የእጅ ስልኮች በደረቁ በማፅዳት ያለ ስጋት በቀላሉ መጠቀም ይቻላል ይላል።

ይህን ፈጠራ ለመስራት ምን አነሳሳው?

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እጅን በውሃ እና በሳሙና በሚገባ መታጠብ ወይም ፀረ ተህዋስ ኬሚካል በተነከሩ የእጅ ማፅጃዎች መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ነገር ግን በርካታ ሕዝብ በሚገኝባቸው ስፍራዎች አንድ ሳሙናን በመጋራት እጅን መታጠብ ከወረርሽኙ አንጻር ስጋት እንደፈጠረበት የሚናገረው ፈይሰል፤ በተጠቃሚው ልክ ሳሙናን በየቦታው ለማስቀመጥ አመቺ አለመሆኑና ሰዎች የራሳቸውን ሳሙና ሲጠቀሙ ልክ እንደ እርሱ ደኅንነት እንደሚሰማቸው በማሰብ ይህንን አማራጭ ለመፍጠር መነሳቱን ይገልጻል።

ፈይሰል ይህንን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማምረት የሚያስፈልገውን ጨርቅ በሚፈለገው ሁኔታ ቆርጦ ለማዘጋጀት የሚያስችል ማሽን ያስገጠመ ሲሆን፤ ለዚህ ማሽን ብቻ ወደ 800 ሺህ ብር ገደማ እንዳወጣ ይናገራል።

በቀጣይ አምርተው ይህንን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ የጨርቅ ሳሙና በስፋት ለማምረትና ለተጠቃሚው ለማቅረብ በተለይም ተማሪዎች የግላቸውን ሳሙና ይዘው መንሳቀስ ስለማይችሉ ይህንን ምርት ትምህርት ቤቶች እንዲጠቀሙ ትኩረት አድርጓል።

በተጨማሪም ሰዎች ሆስፒታሎች፣ በምግብ ቤቶችና በመሳሰሉት ቦታዎች ሁሉ ሳሙናውን ይዘው መሄድና መጠቀም እንዲችሉ ምርቱን በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እቅድ ይዟል።

እስካሁን የመከላከያ ክትባትም ሆነ የፈውስ መድኃኒት ያልተገኘለት የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመቆጣጠር እጅን በተደጋጋሚ በውሃና በሳሙና መታጠብ፣ ከአንድ በላይ ሰው በሚገኝባቸው ስፍራዎች አፍና አፍንጫን በጭምብል መሸፈን፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የሚቻል ከሆነ በርካታ ሰዎች ከሚገኙባቸው ስፍራዎች እራስን ማራቅ በባለሙያዎች ይመከራል።

በተለይም ከማንኛውም ንክኪ በኋላ እጅን በአግባቡ በሳሙናና በውሃ ለ20 ሰከንዶች ያህል መታጠብ በንክኪ የሚያጋጥምን በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል።

በሽታው ከተከሰተ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ቢሆነውም እስካሁን በዓለም ዙሪያ ከ38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ ወደ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ለሞት ተዳርገዋል።

በኢትዮጵያም እስካሁን 86 ሺህ 430 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ የ1 ሺህ 312 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን የጤና ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን ቁጥሩም ከዕለት ዕለት እየጨመረ ይገኛል።

ኮሮና
Banner