ኮሮናቫይረስ ፡ ጽኑ ህሙማንን ያለንክኪ ገላቸውን የሚያጥብ አልጋ የሰሩት ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, BIRHANE YEHUWALEESHET
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ከ1 ሚሊየን በላይ ሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። የወረርሽኙ ሥርጭት አሁንም በአንዳንድ አገራት እያገረሸ ነው።
በሽታው እጅግ አስከፊ ነው። የታመሙ ሰዎች እንደየባህላቸው በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጠየቁ፤ በሽታው የበረታባቸው ሰዎች ሲሞቱ ደግሞ ቀብራቸው ላይ ሰው እንዳይቆም የገደበ በሽታ ነው።
በተለይ በሽታው የተከሰተ ሰሞን በቀብር ላይ የሚገኙ ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። የሚወዷቸውን ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በርቀት በኢንትርኔት አማካይነት ተከታትለው 'እርማቸውን ያወጡ' በርካቶች ናቸው። ይህ ሁሉ የሚደረገው የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ነው።
በኮሮናቫይረስ በጽኑ የታመመ የቤተሰብ አባልን ማጉረስ፣ ማጠብ፣ ከተኙበት ማገላበጥ፣ መደገፍማ የማይታሰብ ነው። ታዲያ በሆስፒታል ውስጥ ከሐኪሞች ጋር ብቻ ተፋጠው ያሉ ራሳቸውን መደገፍ የማይችሉ ጽኑ ህሙማን ስቃዩን እንዴት እያሳለፉ ይሆን?
በዚህ ወረርሽኝ ታመው ነገር ግን የቤተሰብና የወዳጆቻቸውን ድጋፍና እንክብካቤ ማግኘት ያልቻሉ ጽኑ ህሙማን ጉዳይ ያሳሰባቸው አንድ ኢትዮጵያዊ ችግራቸውን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚያቃልል አንድ የፈጠራ ሥራ ይዘው ብቅ ብለዋል።
ይህ የፈጠራ ሥራ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያስችሉና በኢትዮጵያ ባሳለፍነው 2012 ዓ.ም በአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ከተመዘገቡ ስምንት የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን የተቋሙ የፓተንት መርማሪ አቶ ጌታቸው ጣፋ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ያለንክኪ ገላን የሚያጥበው ሁለገቡ አልጋ
አልጋው ሁለገብ ነው። ሁለገብ ስንል ለተለያየ አገልግሎት ይውላል ማለታችን ነው። ሲያስፈልግ እንደ ፍራሽ አልጋ ላይ ማስቀመጥ ይቻላል። እንደ ቃሬዛ፣ እንደ ብርድ ልብስ፣ እንደ የአስክሬን ሳጥንም መጠቀም ይቻላል።
ብርድ ከሆነ ማሞቂያ፤ ሙቀት ከሆነ ደግሞ ማቀዝቀዣ ተገጥሞለታል። እዚያው ውስጥ ሆኖ ያለማንም ረዳት ገላን መታጠብ ያስችላል።
የፈጠራ ሥራ ባለቤቱ ብርሃኔ የኋላእሸት ይባላሉ። በሙያቸው የኤሌክትሪክ ባለሙያ ናቸው። በላውንደሪ እጥበት ንግድ ላይም ተሰማርተው ይገኛሉ። ከሙያቸው ጋር የተያያዙ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የመስራት ልምድ አላቸው።
አቶ ብርሃኔ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህንን የፈጠራ ሥራ የሰሩት ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ በተረጋገጠ በሁለተኛው ሳምንት ነበር።
ለዚህ ፈጠራቸው መነሻ ነበራቸው።
አንድ ጊዜ የኤሌክትሪክ ጥገና ባለሙያ በመሆናቸው የቴክኒክ ሥራ ለመስራት አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኘው ኮቪድ-19 ሕሙማን ማዕከል ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ያመራሉ።
እዚያም ጽኑ ህሙማንን የማየት አጋጣሚው ነበራቸው። ጽኑ ህሙማኑ በበሽታው ምክንያት ስለሚዳከሙና አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ ስለሚገጠምላቸው መንቀሳቀስ አይችሉም።
በሽታው ደግሞ ንክኪን ስለማይፈቅድ እንደልባቸው ቶሎ ቶሎ ሰውነታቸውን እንዲታጠቡ የሚረዳቸው የቅርብ ሰው የላቸውም። ይህን ጊዜ ነበር የፈጠራ ሥራው ሃሳብ ብልጭ ያለላቸው። ከዚያም ህሙማኑ እዚያው በተኙበት ሆነው በ'ስቲም' [እንፋሎት] እና ለብ ባለ ውሃ ገላቸውን የሚያጥባቸው አልጋ ሰሩ።

የፎቶው ባለመብት, BIRHANE YEHUWALEESHET
አልጋው የተሰራው ቆዳ ከሚመስል ፕላስቲክ ሲሆን ልክ እንደ 'ስሊፒንግ ባግ' [በዚፕ የሚዘጋ የመተኛ ሻንጣ] ዓይነት ነው።
ይህን ፈጠራ አልጋ ላይ በማስቀመጥም እንደ ፍራሽና ብርድልብስ ጠቅም ላይ ሊውል ይችላል።
ጋላ መታተብ የሚፈልግ ህመምተኛ በዚፕ ወደ ሚዘጋው መታጠቢያው ውስጥ ይገባል። ሻንጣው የንፁህ ውሃ ማስገቢያና የቆሻሻ ውሃ ማስወገጃ ቱቦ ተገጥሞለታል። እዚያው ውስጥ ሆነው ገላቸውን በውሃ ግፊት ይታጠባሉ።
ከታጠቡ በኋላም ቆሻሻ ውሃውን በተገጠመለት የማስወገጃ ቱቦ በመልቀቅ በተገጠመለት ፋን [በማድረቂያ] ሳይንቀሳቀሱ ሰውነታቸውን ማደራረቅ ይችላል።
በአልጋው ላይ የተገጠመው የእንፋሎት [ስቲም] ማሽን ብርድ ብርድ ሲላቸው ያሞቃቸዋል። ሰውነታቸው እንዲፍታታም እንደ ውሃ ገንዳ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ሙቀት ሲሰማቸው ቀዝቃዛ አየር፤ ሲበርዳቸው ሙቀት መጨመርና ያለውን የአየር ሁኔታ ማስተካከልም ያስችላል።
"አልጋው እንደ ማንኛውም አልጋ ምቹ ነው" የሚሉት አቶ ብርሃኔ፤ የተገጠመለት የአየር ሁኔታ ማስተካከያው ምን አልባት ንዝርት ሊያመጣ ይችላል የሚል አስተያየት እንደተሰጣቸውና ያን አሻሽለው ለመስራት እየሞከሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ጽኑ ህሙማኑ ሕይወታቸው ካለፈም የሻንጣውን ዚፕ በመዝጋት አስከሬናቸው በሙቀት እንዲደርቅ በማድረግ፤ ቱቦዎቹን በማላቀቅ ያለምንም ንክኪ ወደ ቀብር ለመሸኘትም ያስችላል።
"አልጋም፣ የሬሳ ሳጥንም፣ ብርድ ልብስም ነው" ይላሉ አቶ ብርሃኔ፤ በተላላፊው የኮሮናቫይረስ ምክንያት በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ለመንከባከብ የሚረዳውን የፈጠራ ሥራቸውን ሲገልጹት።
የዚህ ፈጠራ ሥራ አገልግሎቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም።
ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ህሙማንን እንደ ቃሬዛ በመጠቀም የበሽታውን ስጋት በሚያስወግድ ሁኔታ ያለ ንክኪ ወደ ህክምና ተቋማት ለመድረስም ጥቅም ላይ መዋል ይችላል።
በአንቡላንሶች ውስጥም ህሙማኑን በምቾት ለማውረድና ለማንቀሳቀስ በሚያስችል መልኩ የተሰራ ሲሆን፤ እንዲሁም በገጠር አካባቢ በሜዳ ላይ፣ በትምህርት ቤትም ሆነ በስፖርት ሜዳ በቀላሉ የሚጎተት ሆኖ ተዘጋጅቷል።
"በአንድ ቀን ከ500 እስከ 600 አልጋዎች ሊመረት ይችላል" የሚሉት አቶ ብርሃኔ፤ ነገር ግን በዚህ ዘመን አስፈላጊ ነው የተባለውን ፈጠራቸውን ወደ ምርት እንዲያስገቡ አስተያየት ቢሰጣቸውም፤ ድጋፍ በማድረግ አብሯቸው የሚሰራ አካል እንዳላገኙ ተናግረዋል።
የፈጠራውን ሃሳብ ወደ ተግባር በመለወጥ ባለፉበት ሂደት ውስጥ እስካሁን ድረስ ለሙከራ ሥራቸው ወደ 200 ሺህ ብር ገዳማ እንዳወጡም ገልፀዋል።
አቶ ብርሃኔ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጉዳት እያደረሰ ያለውን የአንበጣ ለመከላከል ያስችላል ያሉትን ፈጠራቸውን ባለፈው ዓመት አበርክተው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ለዚህም በባትሪና በፀሐይ ኃይል ቻርጅ ተደርጎ አንበጣን የሚገድል በእጅ የሚያዝና መኪና ላይ የሚገጠም መሳሪያ ቢሰሩም ፈጠራቸውን ሥራ ላይ ለማዋል ቀርቶ ለማት ፈቃደኛ የሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ማግኘት እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ "የፈጠራ ሥራን የሚደግፍና የሚያበረታታ አሰራር የለም" ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ነገር ግን በዚህ ተስፋ ያልቆረጡት አቶ ብርሃኔ የፈጠራ ሥራቸው ወደ ምርት ከገባ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድም አላቸው።













