ኮሮረናቫይረስ፡ "በአባታችን ቀብር ላይ ሆነን የእናታችንን ሞት ሰማን"

ጆን እና ሜሪ ከ60 ዓመት በፊት በጋብቻቸው ዕለት

የፎቶው ባለመብት, ELAINE BOXER

የምስሉ መግለጫ, ጆን እና ሜሪ ከ60 ዓመት በፊት በጋብቻቸው ዕለት

አዛውንቶቹ ጆን እና ሜሪ ትዳር የመሰረቱበትን 60ኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት ነበር የሚያከብሩት። ቤተሰቡ ይህንን ቀን ደመቅ ባለ ሁኔታ ለማክበር ሽር ጉድ ሲል ነበር የሰነበተው።

ነገር ግን ያልታሰበው ተከስቶ የስድስት አስርት ዓመታት የትዳር ዘመናቸውን የሚዘክሩበት በዓልን ማክበር ሳይችሉ ሁለቱም በቀናት ልዩነት ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

"ሁለቱም በርካታ አባላት ካሉት ቤተሰብ የመጡ ሲሆን ሁለቱም በቤተሰባቸው ካሉት ሰባት ልጆች መመካከል ነበሩ'' ትላለች ሴት ልጃቸው ኢሌይን።

"አራት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ስንሆን፤ አባታችን በአንድ ቴሌኮም ድርጅት ውስጥ ነበር የሚሰራው። እናታችን ደግሞ በጽዳት ሥራ ከዚያም ሰንደርላንድ ሮያል ሆስፒታል ውስጥ የምግብ አቅርቦት ተቆጣጣሪ በመሆን አገልግላለች።''

ጥንዶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ጓደኛሞች የነበሩ ሲሆን በሰሜን ምሥራቅ እንግሊዝ ሰንደርላንድ ውስጥ በአንድ አካባቢ ነበር እድገታቸው።

"እናቴ እድሜያችንን በሙሉ አብራን የኖረችው ሴት አያታችንን መንከባበከብ ስለፈለገች ሥራዋን አቁማለች። አያቴ ወደ አዛውንቶች መንከባከቢያ ማዕከል የገባችው በ103 ዓመቷ ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ እናቴ የጤና እክል ስላጋጠማት መንከባከብ ባለመቻሏ ነው" ትላለች ኢሌይን።

ኢሌይን እና እህቷ ግሊኒስ የወላጆቻቸውን 60ኛ ዓመት የትዳር በዓል ለማክበር ዝግጅት ላይ ነበሩ።

"የበዓል ቀናቸውን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር አዳራሽ ልንከራይና ዘፋኝ የሆነው የባለቤቴ ወንድም ደግሞ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲያቀነቅን እያሰብን ነበር" ትላለች ኢሌይን።

''ወላጆቼ የባለቤቴ ወንድም ሲዘፍን መመልከት በጣም እንደሚያስደስታቸው አውቅ ነበር። ልክ የእንቅስቃሴ ገደቡ መሆን ሲጀምር ሲጀምር በዓሉን ለማክበር የምናደርገውን ዝግጅት ለጊዜው ማቆም ነበረብን።''

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ አዛውንቱ አባት ጆን የጤና እክል አጋጥሟቸው ወደ ሰንደርላንድ ሮያል ሆስፒታል የተወሰዱት በዕለተ ስቅለት ነበር። የሆስፒታሉ ሠራተኞች ምንም አይነት ምልክት ማየት ባለመቻላቸው መልሰው ወደቤታቸው ይልኳቸዋል።

ነገር ግን ከሁለት ቀን በኋላ በፋሲካ ዕለት ሚስተር ጆን ወደ ሆስፒታል በመመለስ የኮቪድ-19 ምርመራ ያደርጋሉ። በሁለተኛው ቀን የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋገጠ።

"ሆስፒታሉ አሁንም ቢሆን በድጋሚ ወደቤት ሊመልሰው ሲል የባለቤቴ ወንድም ሆስፒታል ሄዶ ተቀበለው። መራመድ አይችልም ነበር፤ የስኳርና በሽታና የእንቅስቃሴ ችግር ነበረበት። በተደጋጋሚ ድካም እንደሚሰማውና ሰውነቱ እንደሚዝል ይናገር ነበር'' ትላለች ልጃቸው ኢሌይን።

ጆን እና ሜሪ ከልጆቻቸው ግሊኒስ እና ኢሌይን ጋር

የፎቶው ባለመብት, ELAINE BOXER

የምስሉ መግለጫ, ጆን እና ሜሪ ከልጆቻቸው ግሊኒስ እና ኢሌይን ጋር

ጆን የጤና ሁኔታቸው እየተባባሰ በመምጣቱ ሆስፒታል እንዲቆዩ ቢደረጉም ሊሻላቸው አልቻለም። ከሰባት ቀናት በኋላም ህመማቸው እጅግ ስለጠናባቸው ይህችን ዓለም በሞት ተሰናበቱ።

''ማመን አልቻልኩም ነበር፤ ሰኞ እና ሐሙስ ዕለት አውርተን ነበር። እንደተለመደው እየተጫወተና እየሳቀ ነበር'' ትላለች ልጃቸው።

አክላም በዚህም ምክንያት ''እናቴ በጣም ከማዘኗ የተነሳ ምግብ መብላት አቆመች'' ብላለች።

ኢሌይን የአባቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሊፈጸም ቀናት ሲቀሩት እናቷን ለመጎብኘት ወደ እህቷ ቤት መሄድ ነበረባት።

"እህቴ ስልክ ደውላ በፍጥነት መምጣት እንዳለብኝ ነገረችኝ። እናታችን ጥሩ ስሜት ላይ እንዳልሆነችና የሰውነቷ የሙቀት መጠንም እንደጨመረ ነገረችኝ። ሳልም ሆነ ሌሎች የኮሮረናቫይረስ ምልክቶች ባይታዩባትም የኦክስጂን መጠኗ ግን ዝቅ ብሎ ነበር።"

እናታቸው ሜሪ በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ላይ ሆስፒታል እንዲገቡ ተደረጉ። በተደረገላቸው ምርመራም ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋገጠ። ሜሪ ሆስፒታል ውስጥ እንዲቆዩ ቢደረጉም ቤተሰባቸው ግን በየቀኑ በቪዲዮ ያገኛቸው ነበር።

ኢሌይን ለአባቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ ቤታቸው ተመለሰች። በሴንት ሂሊንዳ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተደረገው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት የቻሉት ሰባት ሰዎች ብቻ ነበሩ።

ኢሌይን፣ የፍቅር አጋሯ፣ እህቷ፣ የአባታቸው ታላቅ ወንድምና ሌሎች ተጨማሪ ሦስት ሰዎች ብቻ በተገኙበት የአባታቸው የጆን ግብዓተ መሬት ተፈጸመ።

"በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘነው ሁላችንም ስልካችንን አጥፍተን ነበር። ቀብሩ ከተፈጸመ በኋላ ወደ ቤት ተመልሰን ስልካችንን ስናይ ብዙ ጊዜ ተደውሎልን ነበር። ወዲያው መልሰን ስንደውል ጥሪው እናታችን ትታከምበት ከነበረው ሆስፒታል እንደሆነና እናታችን ሕይወቷ እንዳለፈ ተነገረን።"

"ሁላችንም ተቃቅፈን ማልቀስ ጀመርን። ምንም እንኳን እናታችን እድሜዋ እንደገፋና ጤናዋ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብናውቅም ሕልፈቷ በጣም አስደንግጦናል። በአባታችን በተቀበረበት ዕለት ማረፏ ደግሞ አስገርሞናል።"

የእናታቸው የሜሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከቀናት በኋላ ሲፈጸም በወረርሽኙ ምክንያት ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ትንሽ ላልቶ መሰባሰብ የሚችሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍ ብሎ ነበር። በዚህም የቀብራቸው ላይ 16 የቤተሰብ አባላት፣ ዘመዶችና ወዳጆች መገኘት ቻሉ።

"እናትና አባቴ ሁለቱም በጣም ትልቅ ቤተሰብ ነው ያላቸው። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ በጣም ትንሽ ሰው ብቻ ተገኝቶ አሸኛኘት ማድረጉ በጣም ነው የሚያሳዝነው።

"ሁለቱም ላለፉት በርካታ ዓመታት በጣም ብዙ ጥሩ ትዝታዎችን አሳልፈዋል። የ40ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ለማክበር ወደ አሜሪካ ነበር የሄዱት። በፍሎሪዳና ላስቬጋስ ቆይታም አድርገው ነበር።"

መላው ቤተሰብ በአሁኑ ጊዜ በሚቀጥው ዓመት የጆን እና የሜሪን ሕይወት ለመዘከር በዝግጅት ላይ ነው። እነሱ አብረዋቸው ባይኖሩም የ60ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ቤተሰቡ ተሰብስቦ ለማክበር አቅዷል።

ኮሮና
Banner