በተቃውሞ እየተናጠች ባለችው ሱዳን ሰልፈኞች በካርቱም ጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን አሰሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሱዳን ሽግግር መንግሥት ደጋፊዎች ወደ ካርቱም ጎዳናዎች ሲተሙ ተቃዋሚዎች ደግሞ ወታደራዊ መንግሥትን በመደገፍ በቤት የመቀመት አድማ አድርገዋል።
በወታደራዊ እና በሲቪል መሪዎች መካከል ያለው ከፍተኛ መከፋፈል ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር ሊያደናቅፈው ይችላል ተብሏል።
ለረዥም ጊዜ በፕሬዝዳንት ያገለገሉት ኦማር አልበሽር እአአ በ2019 ከስልጣን ከተነሱ ማግስት ስልጣን ለመጋራት ተስማምተው ነበር።
በመስከረም ወር በአልበሽር ተከታዮች ተደረገ ከተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተከሸፈ በኋላ ውጥረቱ አይሏል።
መከፋፈሉ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ለማስወገድ ያገዘውን የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች በተባለው ስብስብ መካከል እንዲከፋፈል ምክንያት ሆኗል።
ሐሙስ ዕለት የሲቪሉን መንግሥት የሚደግፉ አንቂዎች ጎማ ሲያቃጥሉ እና የሱዳን ባንዲራን ሲያውለብልቡ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።
የጦሩ ደጋፊ ሰልፈኞች የሲቪል መንግሥት እንዲወገድና ጦር ሠራዊቱ ቦታውን እንዲይዝ ይፈልጋሉ። ያለው አስተዳደር የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲነቃቃ ካለማድረጉ በተጨማሪ የዳቦ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ነው በማለት ይከሱታል።
በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሌላ ቡድን በሚደረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ዋነኛው ወደብ ፖርት ሱዳን እንዲዘጋ በማድረግ ሁኔታው እንዲባባስ አድርጎታል።
ቅዳሜ ዕለት የጦሩ ደጋፊዎች "የረሀቡ መንግሥት ይውረድ" ሲሉ መፈክር አሰምተዋል። የጦር ኃይሎች እና የሱዳን የጋራ ወታደራዊ-ሲቪል ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪው ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ አገሪቱን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አንዳንዶቹ በመዲናዋ ካርቱም በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ቆይተዋል።
"ሲቪሉ የሕዝብ ምርጫ ነው" የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ሰልፈኞች ሐሙስ በከተማዋ መታየታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አክለውም "አል-ቡርሐን ስልጣንን ይልቀቁ" ማለታቸውን ገልጿል።
የሉዓላዊው ምክር ቤት ስልጣን የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አካል ሆኖ በሚቀጥሉት ወራት ወደ ሲቪሎች ይተለለፋል።
ምዕራባውያን አገራት ለሲቪሉ መንግሥት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሁሉም ወገኖች የተስማሙበትን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲከተሉ አሳስበዋል።
ባለፈው ሳምንት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሐምዶክ በሁለት ዓመት የሽግግር ዘመናቸው የአገሪቱን "እጅግ የከፋና አደገኛ" የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ያለመውን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
"በዚህ ግጭት ውስጥ እኔ ገለልተኛ ወይም አስታራቂ አይደለሁም። የእኔ ግልፅ እና ጽኑ አቋም ከሲቪል ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ነው" ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄዱ ከፍተኛ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ጦሩ ጣልቃ በመግባት የ30 ዓመቱ የበሽር አገዛዝ እንዲያከተም አድርጓል። በዚያው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሐምዶክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ።
በሐምዶክ የሚመራው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የነዳጅ ድጎማን ከማንሳቱ ባለፈ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ በመምጣቱ ከቅርብ ወራት ወዲህ የሽግግር መንግሥቱ ድጋፍ ቀንሷል።












