ጄነራል አል ቡርሐን የአገሪቱን ሲቪል አመራሮችና ሚኒስትሮች በተነው በሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ ጦር ኃይሉ የሲቪል አስተዳደሩን በመበተን፣ የፖለቲካ መሪዎችን ካሰረ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ለዚህ እርምጃ ምክንያቱ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ነው ብለዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱን የተቃወሙ ሰዎች በዋና ከተማዋ ካርቱም እና ሌሎች ከተሞች ውስጥ ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ነበረ ሲሆን ተኩስ እንደነበረም ተዘግቧል።
በቴሌቪዥን ቀርበው እርምጃውን ይፋ ያደረጉት ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የአገሪቱን የሲቪል አስተዳደር በመበተን፣ በመላው ሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አስታወቁ።
በተጨማሪም አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትሸጋገር ሂደቱን የሚመራው ሉዓላዊ ምክር ቤት እና የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን መበተናቸውን አስታውቀዋል።
በሱዳን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉ ከተነገረ በኋላ የአገሪቱ ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አብደላ ሐምዶክን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ባለሥልጣናት በወታደሮች ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተነግሯል።
ይህንንም ተከትሎ መፈንቅለ መንግሥቱን የተቃወሙ ሱዳናውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ባሰሙ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ላይሎች በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ 12 መጎዳታቸው ተዘግቧል።
ጄነራል ቡርሐን በአገሪቱ ምርጫ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚካሄድ በመግለጽ ከሁለት ዓመት በፊት የተመሰረተውን የሽግግር መንግሥት እንዲያበቃ አድርገዋል።
ጄነራሉ እና ሌሎች ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ከግብፅ፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ድጋፍ አላቸው።
መስከረም ወር ማብቂያ ላይ የቀድሞው አምባገነን መሪ ኦማር ሐሰን አል ባሽር ደጋፊዎች ናቸው በተባሉ የሠራዊት አባላት የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱን የሽግግር መንግሥት በጥምረት በሚመሩት ሲቪሎችና ወታደራዊ መኮንኖች መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ሁለቱንም ወገኖች የሚደግፉ ተከታታይ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የጦር ሠራዊቱ ደጋፊዎች በሜጀር ጄነራል አብዱልፋታህ አል ቡርሐን የሚመራውን ወታደራዊ የመንግሥት ክንፍ የሚደግፉ ሰልፈኞች ጦር ሠራዊቱ ደካማ ያሉትን የሲቪሎች አስተዳደር አስወግደው አገሪቱን እንዲመሩ በይፋ ሲጠይቁ ተሰምተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሽግግር መንግሥቱ አንድ አካል የሆኑትን ሲቪል መሪዎች በመደገፍ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር አንዲያሸጋግሯት ጠይቀዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው የሲቪሎችና የወታደሮች ጥምር የሽግግር መንግሥት አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዲያደርስ የተዋቀረ ሲሆን በሚቀጥለው የኅዳር ወር ላይ የሥልጣን ጊዜው ያበቃል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።
በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሱዳን በሁለት ወር ውስጥ ሁለተኛው የመፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ የተዘገበው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም ማለዳ ነው።
የታጠቁ ወታደሮች በርካታ የአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ሲቪል ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክም አንዱ መሆናቸው ተነግሯል።
በአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣ መግለጫ እንዳለው ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ስር የማዋል ድርጊት የተፈጸመው "በጥምር ወታደራዊ ኃይሎች" መሆኑንና የተያዙት ሰዎች ያሉት "በማይታወቅ ስፍራ" መሆኑን አመልክቷል።
ጨምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ መፈንቅለ መንግሥቱን እንዲደግፉ ግፊት ቢደረግባቸውም መቃወማቸውንና ሕዝቡ በሰላማዊ ተቃውሞ "አብዮቱን እንዲከላከል" ጥሪ አቅርበዋል ብሏል።
ከዋና ከተማዋ ካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ ያለውን የአገሪቱን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤትን ወታደሮች ጥሰው እንደገቡ የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጨማሪም ወታደራዊ ኃይሎቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተቋሙን ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ከተዘገበ በኋላ ስርጭታቸው ተቋርጧል።
በከባድ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮች እና የፀጥታ ኃይሎች በካርቱም ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የተሰማሩ ሲሆን የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ገድበዋል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተካሄደ መሆኑ ከተሰማ በኋላ የሲቪል አስተዳደሩን የሚደግፉ ሰዎች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ለመውጣት መሞከራቸውን ተከትሎ ወደ ዋና ከተማዋ የሚያስገቡ ዋና መንገዶችን ወታደሮች ዘግተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አረብ ሊግ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎችም በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዘዋል።












