በምዕራብ ኦሮሚያ ታግተው የነበሩ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ሠራተኞች መለቀቃቸው ተገለጸ

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የቱሉ ኬፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት ኩባንያ ለሳምንታት ታግተው የቆዩት አራት ሠራተኞቹ መለቀቃቸውን ለቢቢሲ አስታወቀ።
ቢቢሲ ከአራቱ ታጋቾች መካከል የውጭ አገር ዜጋ መኖሩን መረጃ ያገኘ ቢሆንም ኩባንያው "ሠራተኞቹን በእኩል የሚመለከት በመሆኑ በዜግነታቸው ለመለየት ፍላጎት የለውም" በማለት ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥቧል።
የኩባንያው ሠራተኞች የታገቱት መሰከረም ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን እገታውን የፈፀሙ አካላት ማንነት እስካሁን ድረስ ይፋ አልሆነም።
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው መንግሥት 'ሸኔ' የሚለውና በሽብር ቡድንነት የተፈረጀውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ስለዕገታው የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ቀደም ሲል ገልጿል።
የኩባንያው ሠራተኞች በአካባቢው በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በእገታው ምክንያት ድርጅቱ ሥራውን ለማቋረጥ ተገድዶ ነበር።
የተለያዩ ምንጮች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ከታገቱት ሠራተኞች መካከል አንደኛው የተያዘው ከማዕድን ማውጫው ስፍራ ነው።
ኩባንያው ከሠራተኞቹ መለቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ግለሰቦቹ የታገቱት ለማዕድን ማውጫው ፕሮጀክት የሚያገለግሉ የትራንስፖርት መስመሮችን በመለየት ላይ ሳሉ ነበር።
ስለታጋቾቹ ዜግነት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለሠራተኞቹና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲባል ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን፣ ከእገታው ነጻ ሲወጡ ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ተጠቅሷል።
ቢቢሲ የቱሉ ኬፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት አራት ሠራተኞች መታገታቸውን ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ሲከታተለው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ የድርጅቱ ዋና ሊቀ መንበር ሃሪ አናግኖስታራስ-አዳምስን ስለጉዳዩ ጠይቆ በማዕድን ማውጫ አካባቢው የተፈጠረውን ሁኔታ በደፈናው "የፀጥታ ስጋት" በማለት ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበው ነበር።
ኩባንያው ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ግን ካለፈው መስከረም ጀምሮ ታግተው የነበሩት አራት ሠራተኞቹ እና ኮንትራክተሮች "ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በደህና ሁኔታ" መለቀቃቸውን ገልጿል።
ነገር ግን ድርጅቱ ስለግለሰቦቹ ዜግነት፣ በእገታው ስር አውሏቸው ስለቆየው ወገን እና ስለተለቀቁበት ሁኔታ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
በተጨማሪም ችግሩ መፍትሔ አስኪያገኝ ድረስ የታገቱትን ሠራተኞቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከክልልና ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በትብብር ጥረት ሲያደረግ እንደነበር አመልክቶ፣ ይህ ክስተት ፕሮጀክቱ ለተወሰኑ ወራት እንዲዘገይ አድርጓል ብሏል።
ኩባንያው ከመስከረም 19/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ማቆሙን ዋና ሊቀመንበሩ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሃሪ የደኅንት ስጋት ያሏቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ሳያብራሩ "ያሉት የደኅንነት ስጋቶች በበቂ ሁኑታ መፍትሔ ማግኘታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ሥራው በጊዜያዊነት ቆሟል" ብለዋል።
ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ የማዕድን ሚኒስቴር የቱሉ ኬፒ እናት ኩባንያ ለሆነው የኬፊ ማዕድን ማውጫ ፈቃድን አላድስም ማለቱን አንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ ዘግቧል።
ዘገባው ኩባንያው አጋጠመኝ ያለውን የደኅንነት እንቅፋት በመጥቀስ የማዕድን ሚኒስቴር ፈቃዱን እንዲታደስለት የጠየቀበትን ደብዳቤ ጠቅሷል።
ይኸው ዘገባ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለኩባንያው የፈቃድ ይራዘምልኝ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ላይ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ በቅርቡ መሻሻሉን በመጥቀስ የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄውን ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ቢቢሲ በማዕድን ማውጫው አካባቢ ያለውን ፀጥታ በመጠበቅ በኩል የአካባቢና የፌደራል መንግሥቱ ሚና ምን እንደሆነ ሚስተር ሃሪን ጠይቆ ". . . በመስክ ሥራችን ላይ ያለውን ደኅንት በማስጠበቅ በኩል ምንም ችግር የለም" ብለዋል።
የማዕድን ፕሮጀክት ሥራው በመቋረጡ የሚያስከትለው ትልቁ የምጣኔ ሀብት ጉዳትን በተመለከተ ሊቀመንበሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የፕሮጀክቱ መዘግየት በቱሉ ካፒ እና በዙሪያዋ ባሉ ቀበሌዎች ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ላይ ተጽእኖ አለው" ብለዋል።
ጨምረውም በኩባንያው ፈሰስ የተደረገው ገንዘብ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑንና ሁኔታዎች ተስተካክለው መደበኛ ሥራ ሲቀጥሉ የተያዘው ዕቅድ ተግባራዊ እንደሚሆን፣ "ምርትና ገቢ ማግኘት ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ይጀምራል" ብለዋል።
ለዚህም ሥራው እንዲቋረጥ ስላደረገው ክስተትና የማስተካከያ እርምጃዎችን በተመለከተ የሚዘጋጀው ሪፖርት በ30 ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቀቅ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለሳምንታት ታግተው የነበሩት የማዕድን ኩባንያው ሠራተኞች በማን እጅ ስር እንደቆዩ ባይታወቅም በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ጦር አባላት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ የነበረ ቢሆንም፤ ቡድኑ በድርጊቱ ውስጥ እጁ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ ለቢቢሲ በሰጡት የጽሁፍ መልስ "ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የምናውቀው ነገር የለም። ቀደም ሲል በተከሰቱ ሁኔታዎች ላይ በቁጥጥራችን የገቡ ዜጎች ሲኖሩ ለሚመለከታቸው ኤምባሲዎች በደህና እንዲመለሱ ለማድረግ ለሕዝብ ይፋ እንዳርጋለን" ብለዋል።
የወርቅ ማዕድን ማውጫው ስምምነት በአልሚውና በመንግሥት መካከል የተደረሰው ከአምስት ዓመት በፊት ለ20 ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ እንደሆነ በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ የወጣ መረጃ ያመለክታል። ኩባንያው እንደሚለው በማዕድን ማውጫው አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና ሌሎች የማዕድን ክምችቶች ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደም በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚቀሳቀስ የሚነገረው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ሁለት ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰራሉ ያሏቸውን የአፍጋኒስታን ዜጎችን በመነሲቡ ወረዳ ማገታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ኦሮሚያ ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰሩ የነበሩ ሶስት ቻይናውያን በቡድኑ ከታገቱ በኋላ ለዓለም አቀፉ ኩባንያ መሰጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።














