ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ፌስቡክ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን ለምን አገደ?

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ በኩል የተጋራ አዲስ የጦሩ ምልምል አባላት ምስል

የፎቶው ባለመብት, @OdaaTarbiiWBO

የምስሉ መግለጫ, የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ በኩል የተጋራ አዲስ የጦሩ ምልምል አባላት ምስል

የዓለማችን ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረክ የሆነው ፌስቡክ የኦሮሞ ነጻነት ጦር የተባለውን ታጣቂ ቡድን ከገጹ ማገዱን ለቢቢሲ አረጋገጠ።

ፌስቡክ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን ከፌስቡክ ያገድኩት 'አደገኛ ድርጅቶች' በሚለው መመሪያው መሠረት እንደሆነ ገልጿል።

"የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከፌስቡክ የታገደው 'አደገኛ ድርጅቶች' በተለይ ደግሞ 'መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት' በሚለው ፖሊሲ ሥር ነው" ሲሉ የኩባንያው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በኢሜይል በሰጡት ምላሽ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀውን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ ኦሮሚያ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደረግ ቡድን መሆኑ ይነገራል።

የጦሩ ከፌስቡክ መታገደ ምን ማለት ነው?

ፌስቡክ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን ከፌስቡክ አግጃለሁ ማለት፤ በኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም ጦሩን ወክለው የሚከፈቱ ወይም የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶች እንዲኖሩ አይፈቀድም።

"ለዚህ ቡድን ድጋፍ የሚሰጥ ወይም ቡድኑ የሚፈጥረውን ሁከት የሚያወድስ" ይዘት ከፌስቡክ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረክ ላይ ይጠፋል።

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ኩባንያው ድርጅቶችን በተለያየ ጎራ ከመፈረጁ በፊት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር ዝርዝር ሥርዓቶችን እንደሚከተል ጨምረው ገልጸዋል።

ቢቢሲ የፌስቡክ ውሳኔ ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይን አስተያየት ጠይቆ በተሰጠው ምላሽ፣ በፌስቡክ በቡድኑ ላይ የወሰደውን እርምጃ እንደሚያውቅ ገልጾ፤ ይህም ውሳኔ በተለያዩ ቡድኖች "የኦሮሞ ሕዝብን እና ሌሎች የተጨቆኑ ቡድኖችን ድምጽ ለማፈን" በተካሄደ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጽእኖ ነው ብሏል።

ጨምሮም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች "የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጭፍጨፋዎች የፈጸሙና ማስረጃ የሚቀርብባቸው ቡድኖች" በነጻነት ፌስ ቡክን እየተጠቀሙ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን በመሠረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ ማገድ "የፌስቡክን ፖሊሲ ማን ተጽእኖ እያደረገበት እንደሆነ ግልጽ ነው" ብሏል።

ሌሎች ቡድኖችና ድርጅቶችን በተመለከተ

በኢትዮጵያ ውስጥ ከፌስቡክ መመሪያ በተቃራኒ የተለያዩ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ሌሎች በርካታ ቡድኖችና ግለሰቦች መንግሥታዊ ባልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት ወይም በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ተካተው እገዳ እንደተጣለባቸው የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጨምረውም በዓለም ላይ ካለው ፖለቲካዊ ጥቃት፣ የተደራጀ የጥላቻ እንቅስቃሴ እና የወንጀል ድርጊቶች አንጻር የፌስቡክ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያካተታቸው የጥሰቶቹ ፈጻሚዎች ዝርዝር ተሟላ እንዳልሆ አመልክቷል።

"ነገር ግን ይህንን የሚከታተሉት ቡድኖቻችን ያሉ የስጋት ሁኔታዎች ሲቀያየሩና ወደ ትኩረታቸው ሲገቡ እንዲህ አይነት አዲስ ቡድኖችን በመደበኛነት ግምገማ ያደርጉባቸዋል" በማለት ድርጅቱ የሚያደርገው ክትትል እና ውሳኔ የአንድ ጊዜ ሳይሆን ተከታታይና ዘላቂ ነው ብሏል።

በተጨማሪም በተለያዩ የክትትል ዘርፎች የሚካተቱ ቡድኖችን ለመለየት ፌስቡክ የራሱ የቅደም ተከተል ማዕቀፍን ይጠቀማል። በዚህም በተጨባጩ ዓለም እና በማኅበራዊ መድረኩ ላይ ከፍ ያለ ስጋትን የሚፈጥሩት በቀዳሚነት ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ መድረኩን ደንቦች የሚተላለፉ ሌሎች ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አስካሁን ከዚህ ውስጥ ያልተካተቱ ድርጅቶች በጥልቅና በተከታታይ የምርመራ ሂደት አልፈው ዝቅተኛው መመዘኛ ላይ ባለመድረሳቸው ሊሆን ወይም ደግሞ ድርጅቶቹ አስካሁን ለእገዳ የሚያደርሳቸው ምርመራ ስላልተደረገባቸው ሊሆን ይችላል።

ቢቢሲ በአሁኑ ወቅት በፌስቡክ ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ የኢትዮጵያ ቡድኖች ወይም ተቋማት ይኖሩ እንደሆነ ላቀረበው ጥያቄ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ በዚህ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

"አደገኛ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ፖሊሲ"

የፌስቡክ አደገኛ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ፖሊሲ አሸባሪ ድርጅቶችን፣ የጥላቻ ቡድኖችን እና የወንጀል ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን የሚመለከት ፖሊሲ ነው።

መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት (ቫዮለንት ነን-ስቴት አክተርስ) የሚለው የፌስቡክ ፖሊስ በፌስቡክ አደገኛ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ፖሊሲ ሥር ይገኛል። በፌስቡክ አተረጓጎም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት በአጠቃላይ ንጹሃንን ዒላማ የማያደርጉ ነገር ግን በመንግሥት እና በጦር ሠራዊት ላይ ሁከት የሚፈጥሩ ናቸው።

ግዙፉ ማኅብራዊ ሚዲያ አንድ ቡድን 'መንግሥታዊ ያልሆነ ሁከት ፈጣሪ አካል' ተብሎ ሲፈረጅ የቡድኑ ውክልና (አካውንት) እና ለቡድኑ ድጋፎችን የሚገልጹ ይዘቶችን እንዲሁም ተዋቂ አባላቶቹን ከፌስቡክ አጠፋለሁ ብሏል። እንዲሁም የእነዚህን ቡድን የኃይል ድርጊት (ሁከት) የሚያወድስ ይዘት ይጠፋል ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሰዎች ቡድኑ የሚፈጽመውን የኃይል ድርጊት ሳያወድሱ ለቡድኑ ያላቸውን ደጋፍ መግለጽ እንደሚችሉ አመላክቶ፤ ሰዎች በፌስቡክ ላይ የሚያጋሯቸው ይዘቶች ዓላማ ግልጽ ካልሆነ ግን ቡድኑን የተመለከተ ይዘት ከገጹ ሊጠፉ እንደሚችል ገልጿል።

አሸባሪ ድርጅቶች

ፌስቡክ እንደ አል-ቃኢዳ እና አይኤስአይኤስ ያሉ ድርጅቶችን አሸባሪ ሲል ይፈርጃል። አሸባሪ ድርጅቶች መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት በምን ይለያሉ ለሚለው ጥይቄ ፌሰቡክ የሚከተውን ማብራሪያ ለቢቢሲ ሰጥቷል።

አሸባሪ ድርጅቶች በንጹሃን ላይ አቅደው የኃይል ድርጊት ይፈጽማሉ ወይም እንዲፈጸም ጥሪ ያቀርባሉ። መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት ደግሞ በአጠቃላይ ንጹሃንን ዒላማ የማያደርጉ በመንግሥት እና በጦር ሠራዊት ላይ ሁከት የሚፈጥሩ ናቸው።

ፌስቡክ አሸባሪ ሲል የፈረጃው ድርጅትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት የሚላቸው ቡድኖች በማኅበራዊ ገጹ ላይ እንዲኖሩ አይፈቅድም።

ቡድኖቹ ይታገዳሉ። ለቡድኖቹ ድጋፍን መግለጽ ወይም የሚፈጽሙትን የኃይል ድርጊት ማወደስ አይቻልም።

ማወደስ፣ ድጋፍ መግለጽ፣ መወከል

በፌስቡክ ኮሚኒቲ ስታንዳርድ (የአጠቃቀም ደንቦች) መሠረት መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላትን ወይም ተግባርን የሚያወድሱ፣ ድጋፍ የሚሰጡ እና የሚወክሉ ይዘቶች ይጠፋሉ ይላል።

ማወደስ፡ ስለ ኦሮሞ ነጻነት ጦር በአዎንታዊ ሁኔታ ማውራት ወይም ቡድኑ የሚወስደውን እርምጃ እንደ ስኬት መዘከርን ፌስቡክ አይፈቅድም።

መወከል፡ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን የሚወክል ወይም እወክላለሁ ተብሎ የተከፈተ ገጽ፣ 'ፕሮፋይል'፣ ኩነት (ኢቨንት) ወይም ቡድን ይጠፋል።

ለምሳሌ "የኦሮሞ ነጻነት ጦር አውራ አባል ነኝ" የሚል ይዘት ይጠፋል።

ድጋፍ፡ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር የገንዘብ/የቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ወይም ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ለጦሩ ምልመላ ለማከናወን የሚለጠፉ ይዘቶች ይጠፋሉ።

ለምሳሌ "ለኦሮሞ ነጻነት ጦር መዋጮ ያደርጉ" የሚል ይዘት ይጠፋል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር አርማ እና መሪ

ቢቢሲ ያገኘው ሰነድ ፌስቡክ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተገንጥሎ የወጣ የጦር ክንፍ ነው ይላል። በዚህም የቡድኑን አርማ ፌስቡክ ለይቷል።

ከኦሮሞ ነጻነት ጦር በተጨማሪ፤ 'ወራነ ቢሊሱማ ኦሮሞ' በሚል የሚታወቀውን ቡድን በመምራት ከሚታወቁ መሪዎች መካከል ዋነኛው ዲሪባ ኩምሳ (ጃል መሮ) ነው ይላል ፌስቡክ።