ፌስቡክ ከታሊባን ጋር የሚያያዙ መልዕክቶችን እንዳገደ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፌስቡክ ታሊባንን እንደ አሸባሪ ቡድን እንደሚመለከተውና ከቡድኑ ጋር የተያያዙ መልዕክቶችን እንደሚያቅብ አስታወቀ።
ፌስቡክ ታሊባንን የሚያንቆለጳጵሱ ይዘቶችን፣ የቡድኑን መልዕክቶችንም አግዳለሁ ብሏል።
ይህን ሳንሱር እንዲሠሩለት አንድ ልዩ የአፍጋኒስታን ባለሙያዎች ቡድን ማዋቀሩን እና በእነዚህ ባለሙያዎች እየታገዘ የታሊባን ይዘቶችን ወዲያውኑ ከፌስቡክ ሰሌዳዎች ላይ እንደሚያጠፋ ፌስቡክ ዝቷል።
ታሊባን ለዓመታት መልዕክቶቹን በመላው ዓለም ለማድረስ ፌስቡክን እንደ አንድ መገናኛ ብዙኃን ሲጠቀምበት ቆይቷል።
ታሊባን አሁን የመንግሥትን መዋቅር መቆጣጠሩ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ቡድኑን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው በድጋሚ እንዲያጤኑ እያደረጋቸው ነው።
"በአሜሪካ ሕግ ታሊባን አሸባሪ ቡድን ነው። ይህ ሕግ እኛም በዚያው ሁኔታ እንድናያቸው የሚያደርገን ነው። በመሆኑም ከታሊባን ጋር የሚያያዙ ማናቸውንም መልዕክቶች እናቅባለን" ሲል ተናግሯል፣ የፌስ ቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ።
ፌስቡክ ዋንኛ የአፍጋኒስታን ቋንቋ የሆኑትን ዳሪ እና ፓሽቶን የሚናገሩ አፍጋኒስታዊያን ተወላጆችን ለዚሁ ተግባር ሲል መልምሎ፣ ቀጥሮ እያሠራ እንደሆነም ተናግሯል።
የፌስቡክ ኩባንያ እቀባውን ተግባራዊ የሚያደርገው በእህት ኩባንያዎቹ በኢንስታግራምና በዋትስአፕ የትስስር መድረኮች ጭምር ነው።
ታሊባኖች ዋትስአፕ የትስስር መድረክን በስፋት እንደሚጠቀሙ ይነገራል።
የፌስቡክን እርምጃ ተከትሎ ተገዳዳሪ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ጫና ውስጥ ወድቀዋል።
የታሊባን ቃል አቀባዮች ካቡልን ሲቆጣጠሩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የተጠቀሙት አንዱ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ትዊተርን ነበር።
ይህን በተመለከተ ከቢቢሲ የተጠየቁት የትዊተር ቃል አቀባይ ድርጅታቸው ጥላቻን፣ ሽብርንና ነውጥን በሚያራምዱ ድርጅቶች ላይ ያለው አቋም ወጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዪቱዩብ በታሊባን ጉዳይ የሚከተለውን አቋም ለመረዳት ቢቢሲ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።















