ከሃያ ዓመታት በኋላ ወደ ካቡል የተመለሱት ታሊባኖች እነማን ናቸው?

የታሊባን ታጣቂዎች በአፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታሊባን ታጣቂዎች በአፍጋኒስታን

አፍጋኒስታንን ሲያስስተዳድሩ የነበሩት ታሊባኖች እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2001 ሥልጣናቸውን አጡ።

ለ20 ዓመታት ተዋግተው መልሰው ሥልጣን በእጃቸው አስገብተዋል።

ታሊባኖች ከአሜሪካ ጋር ለሁለት ዐሥርታት ጦርነት ላይ እንጂ ድርድር ውስጥ አልነበሩም።

ከሦስት ዓመት በፊት ነው ለመጀመርያ ጊዜ ለፊት ለፊት ድርድር የተቀመጡት።

ይህም በኳታር ዶሃ የተደረገ ነበር።

ድርድሩ አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ለማውጣት መወሰኗን ተከትሎ የተጀመረ ይመስላል።

በታሊባንና በአሜሪካ መካከል የተደረገው ድርድር ዘለግ ያለ ጊዜን ከወሰደ በኋላ በ2020 የካቲት ወር ላይ ስምምነት ላይ ደረሱ ተባለ።

ስምምነቱ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ፣ በአንጻሩ ታሊባን በአሜሪካ ኃይል ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጽም፣ አል-ቃኢዳ ወይም ሌሎች አሸባሪዎች ጋር ታሊባን እንዳይተባበር አልያም ታሊባን ተቆጣጥሮ በያዛቸው ስፍራዎች ቡድኖቹ እንዳይንቀሳቀሱ የሚሉ ናቸው።

ለመሆኑ ታሊባኖች እነማን ናቸው?

taሊባን ማለት በፓሽቶ ቋንቋ "ተማሪዎቹ" ማለት ነው። ፓሽቶ በፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ኢራን ውስጥ የሚነገር ቋንቋ ነው።

ታሊባን በጎርጎሮሲያዊያኑ 1990ዎቹ መጀመርያ በሰሜን ፓኪስታን ብቅ ያለ መደበኛ ያልነበረ እንቅስቃሴ ሲሆን ይህም የያኔዋ ሶቭየት ኅብረት ከአፍጋኒስታን ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ የተጀመረ ነበር።

ይህ የፓሽቱን እንቅስቃሴ ሲጀምር መንፈሳዊ ቅርጽ የነበረው ይመስላል።

ከሳኡዲ አረቢያ ጥብቅ እስልምናን በሚሰብኩ ሰዎች የተማረኩ ወጣቶች አማካኝነት ስብስቡ እየተጠናከረ መጣ።

መንፈሳዊ እንቅስቃሴው ፖለቲካዊ መልክን እየያዘ መጣ። ከኢመደበኛ እንቅስቃቄ ወደ ቡድን ከፍ አለ።

ይህ ቡድን በፖኪስታንና አፍጋኒስታን መሀል የሚገኘውን ፓሽቱን አውራጃን ቀስ በቀስ በመያዝ ጽኑ የሸሪዓ አስተዳደርን በመትከል ሰለምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ቃል ገባ።

እንዲህ እንዲህ እያሉ ከደቡብ ምዕራብ አፍጋኒስታን ተነስተው ወጣቶቹ ታሊባኖች ተጽእኗቸውን ማስፋት ያዙ።

በመስከረም 1995 ደግሞ ኢራንን የምትዋሰነውን ሔራት የምትባለውን አውራጃ መያዝ ቻሉ።

ይህን ካሳኩ ከዓመት በኋላ ደግሞ ካቡልን ተቆጣጠሩ። ያን ጊዜ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቡርሃንዱኒ ራባኒ ነበሩ።

ቡርሃንዱኒ ራባኒ ከአፍጋኒስታን የነጻነት አባቶች አንዱ ተደርገው የሚወሰዱና የሶቭየት ኅብረትን ታግሎ ያስወጣው የሙጃሂዲን (አርበኞቹ) ቡድን መሥራች ነበሩ።

እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ 1998 ታሊባን የአፍጋኒስታንን 90 ከመቶ ይቆጣጠር ነበር። በዚያን ጊዜ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችሎ ነበር።

ይህም የሆነው ምናልባት አፍጋኒስታዊያን በሙጃሂዲኖች የርስበርስ ሽኩቻ ተሰላችተው ስለነበር ይሆናል።

ታሊባኖች በተለይም ሙስናን በማጥፋትና ሥርዓት አልበኝነትን በመቀልበስ ስማቸው ይወደሳል።

በአፍጋኒስታን ዋና ዋና መንገዶችን በመቆጣጠርና የእንቅስቃሴ ደኅንነትን በማረጋገጥ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረጋቸው በአጭር ጊዜ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችለው ነበር።

የታሊባን ታጣቂዎች በአፍጋኒስታን ጎዳናዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታሊባን ታጣቂዎች በአፍጋኒስታን ጎዳናዎች

ጥብቅ የሸሪዓ ሕግጋት

ታሊባን ጥብቅ የሸሪዓ ሕግጋት ተግባር ላይ እንዲውሉ ይደግፋል ተግባራዊም ያደርጋል።

ለምሳሌ ሴቶች ቡርቃ የሚባለውንና ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ሙሉ የሴት ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ እንዲለብሱ ማስገደድ እንዲሁም ወንዶች ፂማቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይገኝበታል።

ዝሙት ፈጻሚዎች በአደባባይ እንዲሰቀሉና የሰረቁ እጆችም እንዲቆረጥ አድርገዋል።

ታሊባኖች ቴሌቪዥንን፣ ሙዚቃን እና ሲኒማን ሙሉ በሙሉ ያገዱ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ትምህርት እንዳይማሩ መከልከላቸውም ለውግዘት ዳርጓቸው ነበር።

ታሊባኖች በከፍተኛ የሰብዊና ቁሳዊ ጥሰት የሚከሰሱ ሲሆን ከዚህም መሀል በ2001 ዓ.ም በማዕከላዊ አፍጋኒስታን ይገኝ የነበረውን እጅግ ዝነኛውን የባሚያ ቡድሃን ሐውልት ማፍረሳቸው ይጠቀሳል። ይህ ድርጊታቸው ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ታሊባንን ማን ፈጠረው?

የታሊባን ቡድን በፓኪስታን መንግሥት ስለመፈጠሩ የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው። ታሊባንን የፈጠረችው ፖኪስታን ናት የሚባልባቸው አንዱ ሁለት ምክንያቶችን እንጥቀስ።

ምንም እንኳ ፓኪስታን ይህን የማትቀበል ቢሆንም ብዙዎቹ የታሊባን አባላት ግን በፓኪስታን ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች (መድረሳ) የተማሩ ናቸው።

እንቅስቃሴያቸውን ያፋፋሙትም በፓኪስታን ሳሉ እንደሆነ ይነገራል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመጣ ዕውቅና ከሰጡ ሦስት አገራት የመጀመርያዋ ፖኪስታን ነበረች።

ሁለቱ ቀሪ አገራት ደግሞ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ነበሩ።

ፓኪስታን የታሊባን ፈጣሪ ሳትሆን አትቀርም ካስባሏት ሌሎች ምክንያቶች አንዱ ለታሊባኖች ቀድማ እውቅና መስጠቷ ብቻ ሳይሆን ነገሮች ከፍተው ታሊባን ቅቡልነትን እያጣ ሲመጣም ከታሊባን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማቆም የመጨረሻዋ አገር መሆኗን ጭምር ነው።

የታሊባን የስልጣን መዋቅር

የታሊባን ከስልጣን መባረር

የታሊባን ስም ወደ ትልቅ አጀንዳነት የተቀየረው ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ወዲህ ነው።

ታሊባን የኒው ዮርክ መንትዬዎቹን ሕንጻዎች ጥቃት ላደረሰው የአል-ቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ከለላ በመስጠቱ ሁኔታዎች መልካቸውን ሊቀየሩ ቻሉ።

በጥቅምት 7፣ 2001 የአሜሪካ መራሹ ጦር በአፍጋኒሰታን ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ።

በታኅሣሥ የመጀመርያው ሳምንት 2001 ዓ.ም የታሊባን አስተዳደር በይፋ ፈራረሰ።

የቡዱን የወቅቱ መሪ የነበሩት ሙላ ሞሐመድ ኦማር እና የአል-ቃኢዳው መሪ ቢን ላደን ግን ለማምለጥ ቻሉ።

በወቅቱ ሁለቱን መሪዎች ለመያዝ የተደገው አሜሪካ መራሹ የጦር አደን በዓለም ታሪክ ከትልልቅ ወታደራዊ አሰሳዎች የሚመደብ ነበር።

አፍጋኒስታን በውጭ ኃይሎች ሥር መውደቋን ተከትሎ በርካታ ባዕድ ወታደሮች በካቡል መርመስመስ ጀመሩ።

የውጭ ወታደሮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ታሊባን የደፈጣ ጥቃትን እንደ አዲስ ስትራቴጂ መውሰድ ጀመረ።

ባለፉት ሁለት ዐሥርታት ካቡል ላይ ለቁጥር የሚታክቱ የደፈጣ ጥቃቶች የተሰነዘሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው በኔቶ የጦር ካምፕ ላይ በመስከረም 2012 የደረሰው ፍንዳታ ነው።

የታሊባን መልሶ ማንሰራራት

በመጋቢት 2015 ታሊባን የመሪውን ሙላህ ኦማርን ሞት ለ2 ዓመት ድረስ መደበቁን አመነ።

በቀጣዩ ወር ቡድኑ በሙላህ መንሱር አመራር ስር መሰባሰቡን ገለጸ።

በዚያው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ኩንዱዝ የምትባለውን ቁልፍ ከተማ ተቆጣጠረ።

በ2016 ሙላህ መንሱር በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ተገደለ። ምክትሉ መውላዊ ሂባቱላህ አኩንዛዳ የቡድኑ መሪ በመሆን ተሰየመ።

በየካቲት 2020 - የታሊባንና የአሜሪካ የፊት ለፊት ንግግር ተጠናቀቀ ተባለ። ታሊባን ይህን ተከትሎ የውጊያ ስልቱን ቀየረ።

ወታደራዊ ቀጣናዎችን ከማጥቃት ይልቅ ታዋቂ ጋዜጠኞችን፣ ዳኞችን፣ መሪዎችን በተቀነባባረ ሁኔታ መግደል ጀመረ።

ይህም ታሊባን ጽንፈኛ አመለካከቱ እንዳልተቀየረ አመላከተ።

በሚያዚያ 2021 አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ የሽብር ጥቃት በደረሰባት መስከረም 11 ቀን በአፍጋኒሰታን የነበራት የ20 ዓመታት ቆይታ ያበቃል ሲሉ አስታወቁ።

ከዚህ በኋላ ታሊባን በቁጥጥር የሚያውላቸውን ግዛቶች እያሰፋ መጣ። የወታደሮቹ ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። ኔቶ እንደሚለው ታሊባን በአሁኑ ጊዜ 85ሺህ ወታደሮች ይኖሩታል።

የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒሰታንን በሚለቁበት ቅጽበት ታሊባን ቁልፍ ከተሞችን ያለምንም ውጊያ ሰተት ብሎ ሲገባ ነበር።

የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ግምገማ እንሚያሳየው ግን የአፍጋኒስታን መንግሥት የአሜሪካ ጦር ከወጣ ከስድስት ወራት በኋላ ነው ቢወድቅ እንኳ ሊወድቅ የሚችለው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በአየር መንዶች ተገኝቶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በአየር መንዶች ተገኝቶ ነበር።

ይህ የአሜሪካ የስለላ መሥሪያ ቤት ግምት ትናንት ፉርሽ ሆኗል።

አሜሪካ በቢሊዮን ዶላር ወጪ አውጥታ ገንብታዋለች የተባለው የአፍጋኒስታን ጦር ታሊባንን ለ6 ወራት ቀርቶ ለ6 ሳምንታትም ማቆም አልቻለም።

ትናንት ቀትር ለይ ታሊባን ካቡልን ያዘ። በሰዓታት ውስጥ ደግሞ ቤተ መንግሥት ሰተት ብሎ ገባ።

የአፍጋኒሰታን ፕሬዝዳንት አሽረፍ ጋኒም ከአገር ሸሹ።

አሜሪካንን ጨምሮ 60 አገራት ዜጎቻቸውን በሰላም ከካቡል ለማስወጣት አየር ማረፊያውን አጨናንቀዋል።

በርካታ ተንታኞች የትናንቱን ፖለቲካዊ ትዕይንት አሜሪካ ቬትናምን በሽንፈት ከለቀቀችበት የሳይጎን ኩነት ጋር ያነጻጽሩታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ግን ይህን ንጽጽር ክፉኛ ተችተውታል።

"ከ20 ዓመት በፊት አፍጋኒስታን የገባነው አንድ ዓላማ ለማሳካት ነበር። እሱንም አሳክተናል" ብለዋል።