ጆ ባይደን በአፍጋኒስታን ጉዳይ "አቋሜ ጽኑ ነው" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Pool
በከፍተኛ ሁኔታ እየተብጠለጠሉ የሚገኙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከአፍጋኒስታን ወታደሮቼን በማውጣት ውሳኔዬ ሸብረክ የምልበት አይደለም፤ አሁንም የጸና ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
ጆ ባይደን ጨምረውም፣ ‹ታዲያ መቼ ነበር መውጣት የነበረብን? ለመውጣት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ካልነበረ መቼ ነው ታዲያ?› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹አንድም የአሜሪካ ወታደር በአፍጋኒሰታን ምድር ሊሞት አይገባም› ያሉት ባይደን በአወጣጥ ላይ መዝረክረክ እንደነበረ ግን አምነዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ እሑድ ታሊባን ወደ ካቡል መገስገሱን ተከትሎ ፕሬዝደንት አሽራፍ ጋኒ አገሪቱን ለቀው መሄዳቸው አይዘነጋም፡፡
ጆ ባይደን ማስተባበያ በሰጡበት በዚህ ንግግራቸው እንዳብራሩት፣ የአፍጋኒሰታን ጦር ታሊባንን ለመዋጋት ፍላጎት እንዳልነበረው፣ የአፍጋኒሰታን መንግሥትም ወዲያውኑ ተስፋ እንደቆረጠ ከገለጹ በኋላ ታሊባን ካቡልን ይቆጣጠራል ብለን ከገመትንበት ጊዜ ቀድሞ መምጣቱ ነገሮችን እንዳመሰቃቀለ አመላክተዋል፡፡
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ታሊባን ቢያንስ ካቡልን ለመያዝ ስድስት ወራት ሊወስድበት እንደሚችል ተንብዮ ነበር፡፡
ባይደን ከሜሪላንድ ካምፕ ዴቪድ የፕሬዝዳንታዊ ሽርሽር ወደ ዋይት ሐውስ የተመለሰት ገና ትናንት ሰኞ ነበር፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ስለሆነው ነገር ለመጀመርያ ጊዜ አስተያየት የሰጡት ባይደን ‹ባለፈው ሳምንት በአፍጋኒስታን የሆነው ነገር አንድ ያረጋገጠልን ጉዳይ ቢኖር ከዚያች አገር ለመውጣት መወሰናችን ትክክል እንደነበረ ነው› ብለዋል፡፡
"አንድም የአሜሪካ ወታደር በአፍጋኒስታን መዋጋት የለበትም፣ መሞትም የለበትም፣ አፍጋኒስታን ወታደሮች ለማይዋጉለትና ለማይሞቱለት ጦርነት ለምን ብሎ አሜሪካዊ ወታደር ተዋግቶ ይሞታል?" ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒስታንን እንዲወሩ ያደረጉት ጆርጅ ቡሽ በበኩላቸው ‹በአፍጋኒስታን እየሆነ ያለውን ነገር በታላቅ ሐዘን ነው እየታዘብኩ ያለሁት› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጆ ባይደን የአሜሪካ በአፍጋኒስታን ተልእኮ አገር ግንባታ አልነበረም ያሉ ሲሆን በ2009 ባራክ ኦባማ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አፍጋኒስታን ሲልኩ ተቃውመዋቸው እንደነበረ፣ ትራምፕ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በግንቦት ወር እቅድ ይዘው እንደነበረና፣ እሳቸው የ20 ዓመት የአፍጋኒስታን ቆይታን እንዲቋጭ ለመወሰን 4ኛው ፕሬዝዳንት እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡
‹ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለ5ኛው ፕሬዝዳንት ማስተላለፍ አይገባኝም› ሲሉም በውሳኔያቸው ቁርጠኝነት በጽኑ እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ሚዲያ ጆ ባይደንን በከፍተኛ ሁኔታ እያብጠለጠላቸው ይሁን እንጂ የሕዝብ ሐሳብ መመዘኛዎች እንደሚጠቁሙት አብዛኛዎቹ አሜሪካዊያን በጆ ባይደን ውሳኔ ደስተኞች ናቸው፡፡
እሑድ ዕለት በካቡል የአሜሪካ ኤምባሲ ሔሊኮፕተር ስታንዣብብና የአሜሪካዊያንን ሕይወት ለመታደግ የሞከረችበት ኩነት አሜሪካ ድሮ በቪየትናም ሳይጎን በአሳፋሪ ሁኔታ ተሸንፋ ከወጣችበት ሁኔታ ጋር መመሳሰሉ ታሪክ ራሱን ደግመ እያስባለ ይገኛል፡፡
በካቡል አየር ጣቢያ በርካታ ሰዎች አፍጋኒስታንን ለመልቀቅ የአውሮፕላን ጎማ ላይ እስከመንጠልጠል ደርሰው ታይተዋል፡፡
በአየር ጣቢያው ብቻ በድምሩ ሰባት አፍጋኒስታናዊያን ተገድለዋል፡፡
ከሟቾቹ ውስጥ ከአሜሪካ ወታደራዊ ጄት ተንጠላጥለው የነበሩና በኋላም ወድቀው የሞቱ ይገኙበታል፡፡












