በታሊባን ቁጥጥር ሥር በወደቀችው አፍጋኒስታን የታዩ ዋና ዋና ክስተቶች

የታሊባን ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የታሊባን ታጣቂዎች

አፍጋኒስታናውያን ቀናቸውን ከዓመታት በኋላ በታሊባን አገዛዝ ሥር ዳግም ጀምረዋል።

ታሊባን በከፍተኛ ፍጥነት በርካታ የአፍጋኒስታን አካባቢዎችን በመቆጣጠር ትናንት እሁድ በመዲናዋ ካቡል የሚገኘውን ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ወርሷል።

ነገሮች በፍጥነት በሚቀያየሩባት አፍጋኒስታን ጉልህ ክስተቶች የሚከተሉት ናቸው።

የአፍጋኒስታን ፕሬዝደንት ከአገር መሸሽ

የአፍጋኒስታን ፕሬዝደንት አሽራፍ ጋኒ ታሊባን መዲናዋን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወደ ጎረቤት ታጃኪስታን ሸሽተዋል የሚሉ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ አልጀዚራ አሽራፍ ጋኒ፣ ባለቤታቸው እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው ኡዝቤኪስታን እንደሚገኙ ሪፖርት አድርጓል።

ፕሬዝደንቱ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት ደም መፋሰስን ለማስቀረበት በሚል ከባድ ውሳኔ በመወሰን አገር ጥለው መውጣታቸውን ለአፍጋን ሕዝብ ተናግረዋል።

አሽራፍ ጋኒ አገሪቱን ጥለው መሸሻቸው በበርካቶች እያስተቻቸው ይገኛል።

ካቡል ዛሬ ንጋት ላይ

የአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ከትናንት ጀምሮ በታሊባን ቁጥጥር ሥር ትገኛለች።

የአፍጋኒስታን ዜጎችም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ዳግም በታሊባን አስተዳደር ሥር ወድቀዋል።

የታሊባን ቡድን ትናንት እሁድ መዲናዋን ሲቆጣጠር የአፍጋኒስታን መንግሥት ፈርሷል። ፕሬዝደንት አሽራፍ ጋኒም አገር ጥለው ተሰደዋል።

የታሊባን ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የታሊባን ታጣቂዎች

ቁጥራቸው በርከት ያሉ የታሊባን ታጣቂዎች ጦር መሳሪያቸውን እንደታጠቁ በካቡል ጎዳና ላይ ታይተዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በመዲናዋ የሚገኘውን አየር ማረፊያ አጨናንቀዋል።

ቻይና እና ሩሲያ ኤምባሲዎቻችን አይዘጉም አሉ

ታሊባን ካቡልን መቆጣጠሩን ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸውን እና የኤምባሲ ሰራተኞቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ሩሲያ እና ቻይና ኤምባሲዎቻቸውን ከፍት አድርገው፤ ዜጎቻቸውም በካቡል እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።

ቻይናውያን በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ቻይና ያሳሰበች ሲሆን፤ የቻይና መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ በአፍጋኒስታን ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት ጥያቄ ማቅረቡ ተስምቷል።

የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በተመሳሳይ ዜጎቹን ከካቡል የማስወጣት እቅድ እንደሌለው በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው አስነግሯል።

የታሊባን ተወካዮች ሐምሌ ወር ላይ ወደ ቻይና ተጉዘው ከቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ሊ ጋር ተገናኝተው ነበር።

በወቅቱ ቻይና የታሊባን ተወካዮችን ተቀብላ ማነጋገሯ ታሊባን እንደ ፖለቲካ ኃይል ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እንዳገኘ ማሳያ ነው ተብሏል።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በአፍጋኒስታን ውስጣዊ ጉዳይ "ጣልቃ ያለመግባት" ፖሊሲን አራምዳለሁ ሲል ቆይቷል።

የታሊባን ተወካይ ከቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ሊ ጋር።
የምስሉ መግለጫ, የታሊባን ተወካይ ከቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ሊ ጋር።

የታሊባን ተዋጊዎች በቤተ-መንግሥት

የታሊባን ተዋጊዎች ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ሆነው የሚያሳይ ምስል ለቀዋል።

አልጀዚራ የታሊባን ታጣቂዎች ከቤተ-መንግሥቱ አስተዳዳሪዎች ጋር ተገናኝተው የቤተ-መንግሥት ርክክብ ሲያደርጉ አሳይቷል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በርካታ ታጣቂዎች ጦር መሳሪያቸውን እንዳነገቡ በፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥቱ ውስጥ ሲዘዋወሩ አሳይቷል።

በካቡል አየር ማረፊያ ያለው ትዕይነት

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከካቡል ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት በሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከፍተኛ ግርግር እና ግራ መጋባት ተፈጥሯል።

በአየር ማሪፈያው በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ቢገኙም በሥፍራው የነበሩት አየር መንዶች እና የኢሚግሬሽን ሠራተኞች ቁጥር ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች አውሮፕላን ለመሳፍር በሚያደርጉት ግፊያ በርካቶች መጎዳታቸው ተገልጿል።

አሜሪካ የኤምባሲ ሠራተኞችን ወደ አየር ማረፊያ ስለማሸሿ

የአሜሪካ መንግሥት በካቡል ኤምባሲ የሚሰሩ ሠራተኞችን ወደ ሃሚድ ካራዛይ አየር ማረፊያ ማንቀሳቀሱን አስታውቋል።

ትናንት ቀን ላይ የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተሮች ከኤምባሲው ወደ አየር ማረፊያው ሲመላለሱ ታይተዋል።

አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ወደ 6ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ልካለች።

የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት የአሜሪካ ወታደሮች የአየር ማረፊያውን ዙሪያ እየጠበቁ ነው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት አየር ማረፊያ ተገኝተዋል።
የምስሉ መግለጫ, በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት አየር ማረፊያ ተገኝተዋል።

የአፍጋኒስታን ዜጎች ከአገር እንዲወጡ ፍቃድ እንዲሰጥ መጠየቁ

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ ከ60 በላይ አገራት የአፍጋኒስታን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ከአፍጋኒስታን መውጣት ከፈለጉ ፍቃድ እንዲሰጣቸው በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።

አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣት ለሚፈልግ ለየትኛውም አገር ዜጋ ፍቃድ እንዲሰጥ ታሊባን ተጠይቋል።

የጋራ መግለጫው የአፍጋኒስታን ዜጎች በደኅንነት እና በክብር የመኖር መብት አላቸው ብሏል።

ዩኬ ዜጎቼን ከአፍጋኒስታን እንደማስወጣ እምነት አለኝ አለች

የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር በአፍጋኒስታን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንግሊዛውያንን በቀጣይ ቀናት እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

መከላከያ ሚንስትሩ ቤን ዋለንስ በመካከለኛው ምስራቅ በምትገኝ አገር በኩል ዜጎቻችንን ማስወጣት እንዲቻለን በካቡል የሚገኘው አየር ማረፊያ በሥራ ላይ እንደሚቆይ ከታሊባን የጦር አመራር ማረጋገጫ ደርሶናል ብለዋል።

ቤን ዋለንስ ትናንት 300 የዩናይትድ ኪንግደም & ኖርዘርን አየርላንድ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸውን አረጋግጠው በቀጣይ 24-48 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ 1ሺህ 500 ሰዎችን ለማስወጣት ታቅዷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 4ሺህ የሚገመቱ የእንግሊዝ ዜጎች በአፍጋኒስታን እንደሚገኙ ይገመታል።

አየር መንገዶች የአፍጋኒስታን የአየር ክልል መጠቀም ማቆማቸው

በርካታ አየር መንገዶች የአፍጋኒስታን የአየር ክልልን ላለመጠቀም የበረራ አቅጣጫቸውን እየቀየሩ ይገኛሉ።

አየር መንገዶች የአፍጋኒስታንን የአየር ክልል በመተው በፓኪስታን እና ኢራን የአየር ክልሎች በረራ እያደረጉ ነው።

ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ብርቲሽ ኤርላይንስ እና ቨርጅን አትላንቲክ የበረራ አቅጣጫቸውን እየቀየሩ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

ከአሜሪካ ወደ ሕንድ የሚደረጉ በረራዎች በዚህ እርምጃ እክል ካጋጠማቸው አየር መንገዶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤሜሬትስ አየር መንገድ ወደ ካቡል የሚያደርጋቸውን በረራዎች ሙሉ በሙሉ ሰርዣለሁ ብሏል።

ጀርመን ዜጎቿን ለማስወጣት የጦር አውሮፕላኖችን መላክ

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የጀርመን ዜጎችን እና ተባባሪ የነበሩ የአፍጋኒስታን ዜጎችን ለማስወጣት የጦር አውሮፕላኖች መላኩን አስታውቋል።

የጦር አውሮፕላኖች ትናንት ምሽት ወደ አፍጋኒስታን የበረሩ ሲሆን የጀርመን እና የአፍጋኒስታን ዜጎችን "ወደ ጎረቤት አገር ከተወሰዱ በኋላ በሲቪል አውሮፕላን ወደ ጀመርን ይመጣሉ" ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ።

ጀርመን ቁጥራቸው አነስተኛ የሚሆኑ ዜጎቿ ካቡል በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ በመቆየት ሰዎችን ለማስወጣት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋሉ ብላለች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ቁጥራቸው ከ100 የማይዘል የጀርመን ዜጎች አፍጋኒስታን ውስጥ እንደሚገኙ ዘግቧል።

የዩኬ ፓርላማ በአፍጋኒስታን ጉዳይ ሊመክር ነው

የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ በአፍጋኒስታን ጉዳይ እንዲመክር ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የፓርላማ አባላትን መጥራታቸው ተገልጿል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የታሊባንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ የተሳሳት ስሌት ላይ ደርሰዋል በሚል እየተወቀሱ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ከሦስት ሳምንታት በፊት ታሊባን ወታደራዊ ስኬት የሚደርስበት ሁኔታ የለም ሲሉ ተናግረው ነበር።