አፍጋኒስታን ጦርነት፡ ባይደን በሠራዊታቸው መውጣት እንደማይቆጩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ታሊባን ግስጋሴውን መቀጠሉን ተከትሎ ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት በመወሰናቸው እንደማይቆጩ ተናገሩ።
ባይደን የአፍጋኒስታን መሪዎች አንድ እንዲሆኑ እና "ለአገራቸው እንዲታገሉ" አሳስበዋል።
በአሜሪካ የሚመራው ጦር ከ20 ዓመታት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኋላ መልቀቁን ተከትሎ በመላው አገሪቱ አመጽ ተባብሷል።
ታሊባን ከ34ቱ የአገሪቱ ዋና ከተማዎች ቢያንስ ስምንቱን የተቆጣጠረ ሲሆን የበለጠ እንደሚይዝም አስፈራርቷል።
ማክሰኞ በኋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉት ባይደን፤ አሜሪካ ለአፍጋኒስታን የገባችውን ቃል ኪዳን እየጠበቀች ነው ብለዋል። የአየር ድጋፍ መስጠት፣ ወታደራዊ ደሞዝ መክፈል እና ለአፍጋኒስታን ኃይሎች ምግብ እና መሣሪያ ማቅረብን በምሳሌነት አንስተዋል።
"ለራሳቸው ግን መዋጋት አለባቸው" ብለዋል ባይደን።
ዋሽንግተን ፖስት ስማቸው ያልተገለፀ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዋና ከተማዋ ካቡል በ90 ቀናት ውስጥ በታሊባን እጅ ሊወድቅ ይችላል ሲሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ግምገማዎችን መሠረት አድርገው ተናግረዋል።
ባለፈው ወር በታሊባን እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በተደረገ ከባድ ውጊያ ከ1,000 በላይ ንጹኃን ሰዎች ተገድለዋል። ዩኒሴፍ በበኩሉ በልጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ "ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ" ነው ሲል በዚህ ሳምንት አስጠንቅቋል።
የታሊባን ታጣቂዎች ግስጋሴዎች ጨምሮ በቅርቡ ሁለት ተጨማሪ የክልል ዋና ከተማዎችን ማለትም ፋራህ ከተማን እና ፑል -ኩምሪን ማክሰኞ ዕለት ተቆጣጥረዋል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ታጣቂዎቹ የባግላን ግዛት ዋና ከተማ ፑል-ኩምሪ አደባባይ እና በአስተዳዳሪው ጽህፈት ቤት ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን ሰቅለዋል። ከተማው ከካቡል 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የአካባቢው ጋዜጠኛ እና የክልል ምክር ቤት አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምዕራባዊው የፋራ ከተማም በታሊባን እጅ ወድቋል።
ታሊባን በዚህ ሳምንት ካገኛቸው ሌሎች ቁልፍ ስኬቶች የሰሜን ኩንዱዝ ከተማን መቆጣጠሩን ያካትታል። ከተማው በማዕድን ወደ በለፀጉ አውራጃዎች እንደ መተላለፊያ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ለኦፒየም እና ለሄሮይን ኮንትሮባንድ አገልግሎት ከሚውለው ከታጂኪስታን ድንበር አቅራቢያ ያለ አስፈላጊ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው።
በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከባድ ውጊያ የቀጠለ ሲሆን የአሜሪካ እና የአፍጋኒስታን ጄቶች የአየር ድብደባ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ውጊያው እየተባባሰ በሄደ ቁጥር በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።
"እስር ቤቱ አቅራቢያ አስከሬኖችን አየን ... አጠገባቸው ውሾች ነበሩ" ሲሉ ታሊባን ኩዱዝን መያዙን ተከትሎ አካባቢው ለቀው የወጡ አንዲት ግለሰብ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
የታሊባን ታጣቂዎች ትኩረታቸውን ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ያፈገፈጉ የመንግሥት ኃይሎች ላይ በመሆኑ በከተማው የቀሩ ነዋሪዎች ሱቆች መከፈት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
"ሰዎች ሱቆቻቸውን እና የንግድ ቦታዎቻቸውን ቢከፍቱም አሁንም ዐይኖቻቸው ውስጥ ፍርሃት ይታያል" ብለዋል አንድ ግለሰብ።
ታሊባን የቀረበለትን ዓለም አቀፍ የተኩስ አቁም ጥሪዎች ውድቅ አድርጓል።
የእንግሊዝ የመከላከያ አዛዥ ጄኔራል ሰር ኒክ ካርተር "አገሪቱ ከተያዘች ለዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት እና ለኃይለኛ አክራሪነት ተስማሚ ሁኔታዎች ሊኖር ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












