አሜሪካ የህወሓት አማጽያን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጠብቁ አሳሰበች

ላሊበላ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የህወሓት አማጽያን ሐሙስ ዕለት በተቆጣጠሯት ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ውስጥ ለሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበቃ እንዲያደርጉ አሜሪካ አሳሰበች።

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የዓለም ቅርሶች መካከል የሚጠቀሱት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ወደሚገኙበት የላሊበላ ከተማ የህወሓት አማጽያን ትላንት መግባታቸው ተዘግቧል።

የህወሓት አማጺያን ትላንት እኩለ ቀን አካባቢ "ገነተ ማርያም ተብሎ በሚጠራው በኩል ወደ ከተማዋ ገብተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ያረጋገጡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ፤ ከፌደራል እና ከክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ኃይል ወደ ከተማው እንዲገባና ቅርሱን እንዲጠበቅ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "የትግራይ ኃይሎች ላሊበላን በቁጥጥራቸው ሥር እንዳደረጉ ሪፖርቶች ተመልክተናል። ህወሓት ታሪካዊውን ቅርስ እንዲጠብቅ እንደጠይቃለን" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ለመገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ግጭቱን ለማቆም ከስምምነት እንዲደርሱና ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እድል እንዲሰጡም በድጋሚ የአሜሪካ መንግሥት ጠይቋል።

ካለፈው ጥቅምት አንስቶ ለዘጠኝ ወራት በዘለቀው ጦርነት ከሞቱ ሰዎች፣ ከተፈናቀሉ ዜጎች እና ከወደመው ንብረት ባሻገር ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በትግራይ ከውቅሮ ከተማ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ በሚገኘው ጥንታዊው የአል ነጃሺ መስጅድ ላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቆ ነበር።

በመስጅዱ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን በይፋ ባይገለጽም መንግሥት በመስጅዱ ላይ ጉዳት ያደረሱት የህወሓት አማጺያን ናቸው ሲል ህወሓት ደግሞ የመንግሥት ኃይሎችን ይከሳል።

የአሜሪካ መንግሥት ያነሳቸው ተጨማሪ ነጥቦች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት ሕፃናትን በወታደርነት አሰልፏል መባሉ እንዳሳሰባቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆችን በዘፈቀደ እያሰሩ እንዲሁም እያንገላቱ መሆኑ አሜሪካን እንዳሰጋት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው እንግልት በትግራይ ክልል እንዲሁም በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ጭምርም እንደሆነ ተመልክቷል።

"ብሔርን መሠረት ያደረግ እስር እና እንግልት ተቀባይነት የለውም" ብለዋል ኔድ ፕራይስ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከዚህ ቀደም ባወጧቸው መግለጫዎች በአዲስ አበባ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ የዘፈቀደ እስር እየተፈጸመ ነው ብለው ነበር።

ፖሊስ በበኩሉ ማንም ሰው በማንነቱ ብቻ ለእስር አልተዳረም ሲል ቆይቷል።

line

የፌደራል መንግሥት ከሳምንታት በፊት የትግራይ መዲና መቀለን ለቆ ወጥቶ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ አይዘነጋም።

የህወሓት አማጽያን በበኩላቸው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው በአማራ እና አፋር ክልሎች አቅጣጫ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል።

መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በሚል ምክንያት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ቢያስታውቅም፤ የህወሓት ኃይሎች ተኩስ ለማቆም የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ፣ እንደ ስልክ፣ መብራት፣ ውሃና ኢንተርኔት ያሉ አገልግሎቶች ይመለሱ የሚሉና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበዋል።