የህወሓት አማጺያን ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማ መቆጣጠራቸው ተነገረ

ላሊበላ ካርታ

የህወሓት አማጺያን ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎችና አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በከተማዋ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች የአማጺያኑ እንቅስቃሴ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች አማጺያኑ ዛሬ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰም የህወሓት አማጺያን ሐሙስ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ "ገነተ ማርያም ተብሎ በሚጠራው በኩል ወደ ከተማዋ ገብተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪልም የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ከትግራይ ክልል የተነሱት ኃይሎች በተባበሩት መንግሥታት በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባትን የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን ዘግቧል።

የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሐሙስ ምሽት ላይ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በሳንቃ፣ በአለውሃ እና በሀራ አካባቢዎች ውጊያ እንደነበር አመልክክቶ፤ ወደ ላሊበላ የገባው የህወሓት ኃይል ከአለውሃ የሸሸ መሆኑን ገልጾ ከዚህ ውስጥም ከፊሉ "እየፈረጠጠ ለመውጣት እየሸሸ" ነው ብሏል።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር 310 ኪሎ ሜትሮች እንዲሁም የህወሓት አማጺያን መቀመጫ ከሆነችው መቀለ በስተደቡብ 348 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት።

አማጺያኑ ወደ ከተማዋ ሲገቡ ምንም አይነት ውጊያም ሆነ ተኩስ እንዳልነበረ ከንቲባው ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን አማጺያኑ "ከተማዋን ይዘዋል" በማለት በርካታ ለደኅንነታቸው የሰጉ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

ጨምረውም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተኩስ ድምጽ እንደማይሰማ የተናገሩት ከንቲባው፤ "የህወሓት ታጣቂዎች በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ያወድማሉ የሚል ስጋት" መፈጠሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከላሊበላ ከተማ ውጪ እንደሚገኙ የተናገሩት ከንቲባው፤ "ከፌደራል እና ከክልል መንግሥት ጋር ኃይል እንዲገባ እና ቅርስ እንዲታደግ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

"ይህ የመላው ዓለም ሕዝብ ቅርስ ስለሆነ የዚህ ቅርስ ደኅንነት እንዲረጋገጥ ግፊት መደረግ አለበት" ሲሉ ምክትል ከንቲባው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

line

ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው የላሊበላ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ትልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶችን የምታስተናግድ ከተማ ናት።

ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ በህወሓት ኃይሎች እጅ መግባቷን በተመለከተ የፌደራሉ መንግሥት አስካሁን ያለው ነገር የለም።

በትግራይ ክልል ውስጥ ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት ከአንድ ወር በፊት የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ያስወጣ ቢሆንም የህወሓት ኃይሎች የጥቃት አድማሳቸውን ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል በማስፋት የተለያዩ ቦታዎችን መያዛቸው ይታወሳል።

አማጺያኑ ጥቃት ከሰነዘሩባቸውና ከተቆጣጠሯቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ200 ሺህ በላይ እንዲሁም በአፋር ክልል ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ የክልሎቹ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

የህወሓት ኃይሎች አመራር ናቸው የሚባሉት ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ያሉት የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የፌደራሉ መንግሥት እንዲቀበል ጫና ለማሳደር መሆኑን ተናግረው ነበር።

በአገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ኃይሎችን ጥቃት ለመመከት የአማራና የአፋር ክልሎች ለሕዝባቸው የክተት ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን ወደ ጦርነቱ አካባቢ ልከዋል።