የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ያፀደቀው ኤች አር 445 ውሳኔ ሐሳብ

የፎቶው ባለመብት, Congressmember Karen Bass/FB
ባለፈው ዓመት በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውና አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት ተከትሎ በተፈጸሙ ጥቃቶችና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አንጻር በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የቀረበው የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ጸድቋል።
ይህ ተሻሽሎ መቅረቡ በተነገረው የውሳኔ ሐሳብ በአገሪቱ ያለው ጦርነት መፍትሔ እንዲገኝ መንግሥት "ከሕግ ውጭ የታሰሩ የተቃዋሚ መሪዎችን እና ደጋፊዎችን፣ ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን እንዲፈታ" እና ከትጥቅ እንቅስቃሴ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲያደርግ ይጠይቃል።
በተጨማሪም የውሳኔ ሐሳቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያወገዘ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ግጭቶችን እንዲያቆሙ፣ ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እና የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ ከገለልተኛ መርመሪዎች ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ ኤችአር 445 የተሰኘው የውሳኔ ሐሳብን ተከትሎ የካሊፎርኒያ 37ኛው ኮንግሬሽናል ዲስትሪክት ተወካይና በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ፣ የዓለም ጤና እና የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ካረን ባስ ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል።
ውሳኔውን የመሩት ሰብሳቢዋ "በብሔረሰብ፣ በፖለቲካ እና በታሪክ ለተወሳሰበ ለዚህ ሁለገብ ግጭት ሠላማዊ የድርድር መፍትሄ ማየት ስለምፈልግ ነው" ብለዋል ባስ።
"በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ በጀመረው ጥቃት ሠራዊቱ ምላሽ መስጠቱትን" ጠቅሰው ግጭቱ ሌሎች ኃይሎችንም አካቶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተስፋፍቷል ብለዋል።
"ለውጥ ሳይደረግ እና በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይኖር ግጭቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ይዘልቃል የሚል ስጋት አለኝ" ብለዋል።
ባለፈው መስከረም ወር ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን እና ጠቅላይ ሚንስት ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ማነጋገራቸውን ገልጸዋል። "ሰብዓዊ ቀውሱን በሚፈታበት ጊዜ ብቸኛው መንገድ በሠላም መደራደር መሆኑን ለመግለጽ" መጓዛቸውንም ጠቅሰዋል።
"ውይይቶቹ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በሰብዓዊ ጥረቶች ውስጥ ጣልቃ ገብተው ችግር ከማስከተል ባሻገር ሁከት ፈጥረዋል የሚሉ ሪፖርቶችን አረጋግጠዋል" ብለዋል።
የኤችአር 445 የውሳኔ ሐሳብ በኢትዮጵያ ያለው ሁከት እንዲቆም እና በመከላከያ ሠራዊት መራሹ ኃይሎች እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ባስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲቆም ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል።
"በጅምላ ግድያ፣ ጾታዊ እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ መዝረፍን ጨምሮ እጅግ በጣም ብዙ በደሎችን እና አሰቃቂ ድርጊቶችን የሚፈጽሙትን የሁሉንም ወገን ወታደሮችን፣ አማጻያን እና ሌሎች ተዋናዮችን ያወግዛል። የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ እንዲተባበር አጥብቆ ይጠይቃል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት እና የኤርትራ መንግሥት የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለመውጣት የገቡትን ቃል እንዲፈጽም ጥሪ አቅርበዋል።
"ህወሓትም የህጻናት ወታደሮችን መጠቀሙን ማቆም፣ ኃይሉን ከአማራ ክልል ማስወጣት እና ከታጣቂው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር 'ሸኔ' ጋር ያለውን ጥምረት ማቆም አለበት" ብለዋል።
የውሳኔ ሐሳቡ የተፈናቀሉትን እና በረሃብ አፋፍ ውስጥ የሚገኙትን ግማሽ ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ስቃይ ለማስታገስ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጭ ሠራተኞችን እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን በአስቸኳይ እና ያለገደብ እንዲደርሱ ጠይቋል።
"በተጨማሪም መከላከያ ሠራዊት በቀን ቢያንስ 100 የጭነት መኪናዎችን ወደ ትግራይ መላክ አለበት። የህወሓት መራሹ ኃይሎች ጦርነቱን ለማስቀጠል የጭነት መኪናዎችን ወይም የእርዳታ ዕቃዎችን ሊዘርፉ አይገባም። ተጨማሪ እርዳታ ይዘው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲመለሱም ሁሉም የእርዳታ መጓጓዣ መኪናዎች እንዲገቡና እንዲወጡ ማረጋገጥ አለባቸው" ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተኩስ አቁም እና ለሠላም ድርድር አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
"ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ የለም ብዬ አምናለሁ። አገሪቱ ካለ ብሔራዊ ውይይት የባሰ ችግር እንደሚገጥማት አስባለሁ። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከባይደን አስተዳደር የሚመጣ ማዕቀብ ስጋት ላይ መሆኗን እንዲሁም ሁከቱ ከቀጠለ በአጎዋ ተሳታፊነት ልትወጣ እንደምትችል አሳስቦኛል። ይህ ግጭት እና የሰብዓዊ ቀውሱ ውጤት ኢትዮጵያ የአህጉሩ ምሰሶ ሆና የመቀጠል አቅሟን እየሸረሸረ በመሆኑ መቀየር አለብን" ብለዋል።












