ጦርነት ካገረሸባቸው አካባቢዎች የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, MELAKU AMBAW
በትግራይ ክልል ውስጥ ለወራት የቆው ጦርነት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸው ሁለቱም ክልሎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ለጥቂት ሳምንታት በአንጻራዊነት ጋብ ብሎ የነበረው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና የህወሓት አማጺያን ጦርነት ከሳምንት በፊት መልሶ ካገረሸ በኋላ፣ ከሁለቱ ክልሎች ተጨማሪ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑን የክልሎቹ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ውጊያ እየተካሄደባቸው ባሉት በአማራ ክልል በሚገኙት እንደ ውጫሌ እና ሀብሩ በመሳሰሉ ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እንደሸሹ ተገልጿል።
በአፋር ክልል ደግሞ ከጭፍራ መጋሌና ሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሚመለከታቸው የክልሉ ባለሥልጣኖች አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ አበበ ገብረመስቀል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ደሴ የሚገባው ተፈናቃይ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
"ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያንን ጨምሮ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 500 ሺህ ይገመታል። በእርግጥ አሁን ያለው የተፈናቃይ ቁጥር በትክክል አልታወቀም" ብለዋል።
በተለይም ባለፉት ጥቂት ቀናት እየተባባሰ በመጣው ጦርነት ሳቢያ የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አቶ አበበ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ከወልዲያ፣ ቆቦ እንዲሁም ከሌሎችም አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በደሴ ከተማ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎችም መጠለያዎች ውስጥ ነበሩ። አሁን የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ሌሎች ስፍራዎችን ለመጠለያነት እያዘጋጁ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።
"አሁን ድንኳን፣ መጋዘኖችም እና አዳራሾች እያዘጋጀን ነው። በተጨማሪም የግለሰብ እና የመንግሥት ሼዶችም እየተዘጋጁ ነው። ተፈናቃዮቹን መንግሥት፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ማኅበረሰቡም የሚችለውን እየደገፋቸው ይገኛል" ሲሉ አብራርተዋል።
የፌደራል እንዲሁም የክልሉ መንግሥትም ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ እና የተፈናቃዮች ቁጥር ቢጨምርም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን አክለዋል።
በሌላ በኩል በአፋር ክልል በተለይም ከጭፍራ እና ከመጋሌ ወረዳዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከጭፍራ ወረዳ ከ35 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሏል። ከመጋሌ ወረዳ ደግሞ ወደ 10 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሏል። ከዚህ ወረዳ የሁለት ቀበሌ ሕዝብ ነው የተፈናቀለው። ከዚህ በፊት ከነበረው 150 ሺህ ተፈናቃይ ጋር ሲደመር አሁን ያለው የተፈናቃዮች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ይሆናል" ብለዋል።
ጭፍራ ወረዳ ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፤ መጋሌ ወረዳ ከትግራይ ክልል ጋር ይዋሰናል።
ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ መሐመድ፤ ውጊያው በከፍተኛ ሁኔታ በቀጠለባቸው እንደ ጭፍራ ያሉ አካባቢዎች ግን ሰዎች አሁንም እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
"በርካታ ሰዎች በየጫካው፣ በየጥሻው ተበትነው ይገኛሉ። አሁን የጠፉ እና ከቤተሰብ የተለያዩ ሰዎችን አግኝቶ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው" ብለዋል።
መጠለያ፣ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የጀመሩትን ጥረትም አክለዋል።
መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ እንደ አዲስ ተጠናክሮ የቀጠለውን ጦርነት የከፈተው ህወሓት እንደሆነና "በሁሉም ውጊያ በከፈተባቸው ግንባሮች ከባድ ጉዳት እየደረሰበት" እንደሆነ ገልጿል።
በሌላ በኩል ህወሓት የፌደራል ሠራዊት በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት እንደከፈተ ገልጾ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እርምጃ እንዲያውግዝ መጠየቁ ይታወሳል።
እንደ አዲስ ተጠናክሮ በተጀመረው ውጊያ ሳቢያ ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ፣ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የንብረት ውድመት እንደደረሰም እየተገለጸ ነው።
አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት ሳቢያ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ለረሃብ ተጋልጠዋል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ የመሠረተ ልማት ውድመትም ገጥሟል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የፌደራል መንግሥት እንዲሁም ህወሓትም ያለ ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ማሳሰቡን ቀጥሏል።














