ወደ ደቡብ ወሎ እየተስፋፋ ያለው ጦርነትና የመከላከል ጥሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ ተጠናክሮ እንደቀጠለ የተዘገበውን ጦርነት ተከትሎ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ሁሉም ነዋሪ በተቻለው አቅም የህወሓት ኃይሎችን እንዲዋጋ ጥሪ አቀረበ።
የዞን አስተዳደሩ ትናንት ባወጣው የክተት ጥሪ ላይ፤ "መሳሪያ ያለው በመሳሪያው፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ሐብት ያለው በሐብቱ፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከሚሊሻና ፋኖ ጎን በመሰለፍ የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለምና ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ ያድርግ" ብሏል።
የዞኑ አስተዳደር ይህን ያለው በደቡብ እና አፋር አካባቢዎች ጦርነት እንደ አዲስ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ከተነገረ በኋላ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ትናንት ባወጣው የክተት ጥሪ አማጺያኑ በውጫሌ፣ በተሁለደሬ፣ በወረባቦ እና ደላንታ ግንባሮች ጦርነት ከፍተዋል ብሏል።
በሌላ በኩል የአማጺያኑ ጦር ዋና አዛዥ ናቸው የተባሉት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፤ የሚመሩት ጦር የፌደራሉ ጦር የከፈተውን መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ "በብቃት በመመከት እና በወሰደው የጸረ ማጥቃት እርምጃ ሙሉ ለሙሉ አክሽፏል" ብለዋል።
የትግራይ ኮሚኒኬሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ሌተናንት ጀነራል ታደሰ፤ የፌደራሉ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 5 2014 ዓ.ም. በአራት ግንባሮች መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ ከፍተው ነበር ስለማለታቸው ጽፏል።
በተጨማሪም በአፋር ክልል ጭፍራ ከተማ በአማፂያን እጅ ስለመወደቋ የዘገበ ሲሆን ቢቢሲ ይህንን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
"ሁሉም ነገር ወደ ግንባር"
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ጥቅምት 7 ባወጣው "አስቸኳይ የህልውና ማረጋገጫ ህዝባዊ ጥሪ" ላይ "ሁሉም ነገር ወደ ግንባር" ብሏል።
አብን "በመንግሥት ፍላጎት፣ በውሳኔ ሰጭነት፣ በትጥቅና ስንቅ አቅርቦት እንዲሁም በማስተባበር ረገድ የታዩበትን ጉልህ ክፍተቶች በማረም፣ . . . ህዝብንና ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ" ማናቸውንም የአዘቦት ሥራና የትምህርት እንቅስቃሴዎች በማቆም በሙሉ ኃይል ወረራውን ለመቀልበስ ርብርብ ይደረግ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
አብን በመግለጫው፤ አማጺው ቡድን "የአመራር ክፍተቶችንና ደካማ ጎኖችን በመጠቀም ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ አካባቢውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል" ብሏል።
ከሁለት ቀናት በፊት የአማራ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ደግሞ አማጺ ቡድኑ በተቆጣጠራቸው ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ከፊል ደቡብና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ሲል አስታውሷል።
የክልሉ መንግሥት በመግለጫው "የአማራ ህዝብ ህልውናም ሆነ የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጠው በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ" በመሆኑ የሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ህዝብ ከወራሪው ቡድን ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ሁሉም የበኩሉን ይወጣል ሲል ጠይቋል።
እንደ አዲስ የቀጠለው ጦርነት
ከቀናት በፊት ህወሓት ፌደራል ሠራዊት በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱን እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እርምጃ እንዲያውግዝ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እየተሰነዘረበት ያለው ጥቃት "በከባድ ጦር መሳሪያ፣ በታንክ፣ በሮኬቶች፣ በድሮኖች እና በተዋጊ ጀቶች" የታገዘ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቶ ነበር።
በሌላ በኩል ባሳለፍነው ሐሙስ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር እንደ አዲስ ተጠናክሮ ቀጥሏል የተባለውን ጦርነት የከፈተው የህወሓት አማጺ ቡድን ነው ብሎ ነበር።
የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው አማጺው ህወሓት በሁሉም ግንባሮች ከሰኞ ጀምሮ ውጊያ በከፈተባቸው ግንባሮች ከባድ ጉዳት እየደረሰበት ነው ሲል ገልጿል።
መከላከያ ሚንስቴር በመግለጫው "በጀመሩት ውጊያ አይቀጡ ቅጣት እየደረሰባቸው ይገኛል" ብሎ ነበር።













