የደሴ ከተማ የዕለተ አርብ ውሎና የከሰዓት በኋላው ተኩስ

የፎቶው ባለመብት, Dessie city communication/fb
ጦርነት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች በቅርበት የምትገኘው ደሴ ከተማ አርብ ተረጋግታ አርፍዳ የነበረ ቢሆንም፣ ከሰዓት በኋላ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ በተሰማ ከባድ ተኩስ ልውውጥ ምክንያትም ስጋት ተፈጥሮ እንደነበረ የከተማዋ ባለሥልጣንና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሐሙስ ዕለት ወደ ከተማዋ በተተኮሱ አምስት የመድፍ አረሮች አንድ ሰው የሞተባትና ሦስት ሰዎች የቆሰሉባት ደሴ አርብ ዕለትም በከባድ መሳሪያ ጥቃት አንድ ተጨማሪ ነዋሪዋ መሞቱ ተነግሯል።
በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ በሚነገረው የደሴ ከተማ ላይ ከህወሓት ኃይሎች በኩል ዛሬ አርብ እንደተተኮሰ በተገለፀ ከባድ መሳሪያ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ለቢቢሲ ገለፀዋል።
ምክትል ከንቲባው አቶ ሠይድ የሱፍ እንደተናገሩት ወደ ከተማዋ ከህወሓት ኃይሎች በሚተኮስ የከባድ መሳሪያ እስካሁን ድረስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ አስር ያህል ሰዎች ደግሞ የተለያዩ ጉዳት አጋጥሟቸው ሕክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ከአማጺያኑ በተደጋጋሚ የሚተኮሱ የከባድ መሳሪያ አረሮች የሚያርፉት በጦርነቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የተጠለሉ ሰዎች ባሉበት አካባቢ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሠይድ፣ ዛሬም በተመሳሳይ በተፈናቃዮች መጠለያ አካባቢ የከባድ መሳሪያ ጥይት መውደቁን ተናግረዋል።
አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ተተኮሰ ባሉት በዚህ ከባድ መሳሪያ ከአንድ ሰው ሞት ውጪ ሌላ ጉዳት ስለመድረሱ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በፌደራል ኃይሎችና በህወሓት አማጺያን መካከል ባለፉት ቀናት በዙሪያዋ ውጊያ ሲካሄድ በቆየችው ደሴ ዛሬ [አርብ] ስምንት ሰዓት አካባቢ "ወደ ከተማዋ የህወሓት ኃይሎች ገብተዋል የሚል ወሬ ተሰራጭቶ እንደነበር" የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ በከተማው ነዋሪ ዘንድም መደናገጥ ተፈጥሮ እንደነበር ጨምረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አርብ ከሰዓት በኋላ በከተማዋ አንድ ክፍል በሚገኘው የወሎ ዩኒቨርስቲ አካባቢ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መስማታቸውን ገልጸው ይህም በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ነበር ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ምን እንደተከሰተ እንዳላወቁና ነገር በግን የህወሓት ተዋጊዎች ወደ አካባቢው ገብተው ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ያደረጉት የተኩስ ልውውጥ እንደሆነና ወደ ከተማው ገብተዋል ተብሎ እንደነበር ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባውም በከተማዋ የሚገኙ የመከላከያ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ያዩ እና "በሐሰተኛ ወሬ የተደናገጡ" ያሏቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ መሸሽ ጀምረው እንደነበር፤ ነገር ግን ኋላ ላይ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ መረጋጋታቸውን ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ስለክስተቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በጣት የሚቆጠሩ ያላቸው የህወሓት ታጣቂዎች. . . የተኩስ እሩምታ በመክፈት የአካባቢውን ሕዝብ ለማደናገር ሞክረዋል ብሏል።
ጨምሮም አማጺያኑ "የወሎ ዩኒቨርስቲ አካባቢን እንደተቆጣጠሩ በማስመሰል የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ይገኛሉ።. . . መከላከያና መላው የጸጥታ ኃይል . . . ርምጃ እየወሰደ ነው" በማለት ኅብረተሰቡ የሐሰተኛ ወሬ ፈጣሪዎችንም ሆነ አስተላላፊዎችን ለሕግ እያቀረበ አካባቢውንና ቀዬውን በንቃት እንዲጠብቅ ጽህፈት ቤቱ አሳስቧል።
ሐሙስ ከተፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በኋላ አርብ ከማለዳ ጀምሮ የከተማዋ እንቅስቃሴ ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንደነበር የተናገሩት አቶ ሠይድ የንግድ ቤቶች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ክፍት እንደነበሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባው አቶ ሰይድ ከደሴ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኝ ነበር ያሉት የህወሓት አማጺ ኃይል "ተደምስሷል" ያሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት "ተቆርጦ የቀረው ኃይል ብቻ እዚህም እዚያም የተኩስ ድምጽ እንደሚያሰማ" ይናገራሉ።
ህወሓት በበኩሉ አርብ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ኃይሎቹ "የደሴ ከተማን መቆጣጠር ጀምረዋል" በማለት ውጊያውን ከከተማዋ ውጪ ለመጨረስ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ነገር ግን በከተማዋ በቂ የመከላከያ ሠራዊት መኖሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው አቶ ሰይድ "ከተማዋ እጅግ በጣም በአስተማማኝ ጥበቃ ላይ ነው ያለችው" ሲሉ ተናግረዋል።
ከመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪም የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እንዲሁም ነዋሪው ከተማውን በነቂስ ወጥቶ እየጠበቀ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ከቀናት በፊት መንግሥት ሽብርተኛ የሚለው የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ደሴ እና ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ የከተማዎቹ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ተዋጊዎችም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት መልሶ ያገረሸው ውጊያ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተካሄደ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ቀናት ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች ይጠቀሙባቸዋል ያላቸው ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ በተከታታይ ተዘግቧል።
በዚህም ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የህወሓት ኃይሎች ቢገልጹም መንግሥት ግን ዒላማዎቹ የተመረጡና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ የተካሄዱ የአየር ጥቃቶች መሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል።















