ሱዳን መፈንቅለ መንግሥት፡ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ በሕዳሴው ግድብ ድርድርና በሰሜኑ ጦርነት ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል?

የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water and Energy/fb

ሲንገዳገድ የቆየው የሱዳን የሽግግር አስተዳደር ለይቶለት በጦር ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶበት ከኃላፊነቱ ተወግዶ የሽግግሩ መንግሥት አባል የነበሩት ጄነራል አል ቡርሐን መሪነቱን ጠቅልለው ይዘዋል።

የአፍሪካ ሕብረትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም መፈንቅለ መንግሥቱን ያወገዙ ሲሆን ዓለም አቀፍ ተቋማትም ለሱዳን የሚሰጡትን እርዳታ ከማገድ በተጨማሪ የመንግሥት ግልበጣውን ላደረጉት መሪዎች እውቅና ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ኦማር ሐሰን አልባሽር ከስልጣን መባረር በኋላ በአገሪቱ ጦር ሠራዊትና በሲቪል ፖለቲከኞች መካከል የነበረው ውዝግብ ሰላም ነስቷት የቆየችው ሱዳን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ሰላም የማግኘቷ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

የመንግሥት ግልበጣ ዜናው ከተነገረበት ሰዓት አንስቶ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር የሚፈልገው ሕዝቧ፣ የሙያ ማኅበራትና ፖለቲከኞች በየእለቱ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

በሱዳን ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣን መቆጣጠሩና በአገሪቱ የተከሰተው አከመረጋጋት በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በድንበር ይገባኛል ምክንያት እየተወዛገበቻት ካለችው ኢትዮጵያ አንጻር ምን ውጤት ይኖረዋል?

Short presentational grey line

የሱዳንን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሱዳኑ አልሲሲ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለ። ጄነራሉ ከግብፁ መሪ አልሲሲ ጋርም መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ አብዱራህማን ሰኢድ አቡሃሽም የጄነራል አል ቡርሐን የሱዳን መንግሥትን ሥልጣን መጠቅለል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይናገራሉ።

"ባለፉት ሁለት ዓመታት የአልቡርሐን መንግሥት ከግብፅ ጋር የጋራ ስምምነት ተፈራርሞ በአባይ ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት ፖሊሲ ሲያራምዱ ቆይተዋል" ይላሉ አቡሃሽም።

በዚህም የተነሳ የድንበር ውዝግቦችን እያስነሱ ኢትዮጵያን ሲተናኮሱና ወደ ጦርነት እንድትገባ ሲገፋፉ መቆየታቸውን አጥኚው ጠቅሰዋል። "ይህም በኢትዮጵያ መንግሥት ትዕግስት ነው የታለፈው" ይላሉ።

አቡሃሽም እንደሚሉት የሱዳን መንግሥት ሲቪል አባላት ጄነራል አል ቡርሐን በሚያደርጓቸው ትንኮሳዎች አይስማሙም ነበር። ሱዳናውያንም ቢሆኑ ኢትዮጵያን እንደ ባለውለታና ወንድም ሕዝብ ስለሚያዩ ውዝግቡን አይደግፉትም።

በመሆኑም ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረና በአገሪቱ ዲሞክራሲ ከጠፋ ጄነራል አልቡርሐን ለሥልጣናቸው ሲሉ ወደ አሉታዊ አማራጮች ሊያዘነብሉ እንደሚችሉ አቡሃሽም አስረድተዋል።

"ይህ ከሆነም በቀጥታ ወደ ጦርነት ሊያመራ ስለሚችል ኢትዮጵያን ያሰጋታል" በማለት፤ ይህ ካልሆነም አልቡርሐን ከግብፅ ጋር በሚኖራቸው ቅርበት የተነሳ ኢትዮጵያን ለጦርነት ሊገፋፉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

የሱዳኑ ቀውስ ሰሜ ጦርነት ላይ የሚኖረው አንድምታ

እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አቡሃሽም ከሆነ የአልቡርሐን ኃይል አይሎ በቀጥታ ወደ ጦርነት ካልገባ በስተቀር የሱዳን ቀውስ በሰሜኑ ጦርነት ላይ ብዙ ለውጥ አያመጣም።

ምክንያታቸው የሱዳን ኃይል የህወሓት ኃይሎችን ለመደገፍ ሲሞክር በመቆየቱ አዲስ ነገር አይፈጠርም የሚል ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን በሚገኝ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የህወሓት ኃይሎች እንደተደራጁ እና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክሩ እንደቆዩ ክስ ሲያቀርብ እንደነበርም ተንታኙ አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሱዳን መንግሥታት ስትራቴጂያዊ የሆነ አቋም ስለሌለው በኢትዮጵያ ላይ ተቃዋሚ ኃይሎች በሚመጡበት ጊዜ እንደየ ሁኔታው አቋማቸውን ሊለዋውጡ እንደሚችሉ አቡሃሺም ያስረዳሉ።

በመሆኑም "ህወሓትን እንደ አንድ ስትራቴጂያዊ ተባባሪ አድርጎ ሲሸነፍ የሚያግዘው፤ ሲወድቅ የሚያነሳው ሊሆንለት የሚችል አይመስለኝም" ብለዋል አጥኚው።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር

ግንባታውና በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል የሚካሄደው ድርድር አስር ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከስምምነት ሳይደርሱ አስካሁን ቆይቷል።

ጉዳዩ ወደ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ አምርቶም ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ምክር ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ በሕዳሴው ግድብ ላይ መክሮ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት መፍትሔ እንዲያገኝ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ድርድሩ ሳይጀመር በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ የአገሪቱ ካቢኔ መበተኑ የሕዳሴው ግድብ ድርድርን ወዴት ይወስደው ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

የምሥራቅ ናይል ቴክኒካዊ አህጉራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሁኔታ፤ በተለይ ደግሞ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ተፅእኖ በመፍጠሩ ድርድሩ እስካሁን አለመጀመሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት በሁለተኛው ስብሰባው አገራቱ በተወሰነ የጊዜ ገደብ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ውሳኔ አስቀምጦ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፈቅ አሕመድ፤ ይህንን ግን ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።

ድርድሩን ለማመቻቸት ኃላፊነት የወሰደው የአፍሪካ ሕብረትም ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከአባልነት ማገዱን አስታውቋል።

ጄነራል ቡርሐን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ካቢኔውን ሲበትኑ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ የሱዳን ተደራዳሪ የሚባሉት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የውሃና መስኖ ሚኒስትርም እንቅስቃሴያቸው ታግዷል።

በመሆኑም "የተደራዳሪዎቹ የወደፊት እጣ ፋንታ ባልታወቀበት ሁኔታ ስለድርድር ማውራት አስቸጋሪ ነው" ይላሉ አቶ ፈቅ አሕመድ።

"የፖሊሲ ለውጦችም ይኖራሉ፤ ሱዳን በአሁኑ ሰዓት የምትከተለው ፖሊሲም ምን እንደሆነ አልታወቀም። የአፍሪካ ሕብረት ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ ላይም ሱዳን አትሳተፍም። በመሆኑም የሕዳሴው ግድብ ድርድር ተንጠልጥሎ የሚቆይ ይመስለኛል" ብለዋል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል ቡርሐን እና ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል ቡርሐን እና ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ

የሱዳን ወታደራዊ ኃይልና የግብ መንግሥት ግንኙነት በሕዳሴው ግድብ ላይ

አልባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወታደራዊውና ሲቪል መሪዎች ሥልጣን ተጋርተው አገሪቱን ሲመሩ ቢቆዩም በይበልጥ ሥልጣኑን የያዘው ወታደራዊው ኃይል እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፈቅ አሕመድ፤ ወታደራዊው ኃይል ከካይሮ ጋር እንዳበረ ተናግረዋል።

በመሆኑም ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ላይ ቢቆይም ባይቆይም እስከ አሁን የነበራቸውን አቋም ይለውጣል የሚል እምነት የላቸውም።

"ብቸኛው አማራጭ ድርድር በመሆኑም ድርድሩ ይቀጥላል። ይህንንም እነርሱም ጠንቅቀው ያውቁታል" ብለዋል።

አቶ ፈቅ አሕመድ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ላይ እየፈጠሩ ያሉት ጫና ውጤት እያሳየ መሆኑን ይናገራሉ።

በቁጥጥር ስር የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንም ለዚህ እንደ አብነት ጠቅሰዋል።

ጫናው ከበረታበት ወታደራዊ ኃይል የሲቪል መንግሥቱን ወደ ሥራው ይመልሳል አሊያም በአጭር ጊዜ ምርጫ አካሂዶ ሌላ የሲቪል አስተዳደር ያቋቁማል የሚል ግምት እንዳለ የተናገሩት አቶ ፈቅ አሕመድ፤ ይህ ከሆነ ቶሎ ወደ ድርድር የመመለስ ሁኔታ ይኖራል ብለዋል።

ካልሆነስ?

"ይህ የማይሆን ከሆነ አገራቱ ሌላ አማራጭ የሚፈልጉ ይመስለኛል" ይላሉ አቶ ፈቅ አሕመድ።

የሱዳን መንግሥት ተዳራዳሪዎቹን [የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የውሃና መስኖ ሚኒስትር] ወደ ሥራ መልሶ ወደ ድርድሩን እንዲመለሱ ማድረግ ባለሙያው ያስቀመጡት አንደኛው አማራጭ ነው።

ከዚህም ባሻገር ሌላ ጊዜያዊ ተደራዳሪ በመሰየም ሦስቱ አገራት የሚደራደሩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል።

በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች የሚወዛገቡ አገራት ድርድር የሦስተኛ አገር ጣልቃ ገብነት ባይደገፍም፤ የተሻለ፣ የተለየ ፍላጎት እና ወገንተኝነት የሌለው ሦስተኛ አካል በማስገባት መደራደርም ሌላኛው አማራጭ ነው ብለዋል።

አቶ ፈቅ አሕመድ እንደሚሉት የአፍሪካ ሕብረት በድርድሩ አልቀጥልም ቢል እንኳን አገራቱ ፍላጎት ካላቸው ተነጋግረው ልዩነቶቻቸውን መፍታት ይችላሉ።

ግብፅ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አማራጮችን ስትሞክር እንደቆየች የሚናገሩት አቶ ፈቅ አሕመድ "ሙርሲ ፕሬዝዳንት እያሉ ለውዝግቡ ስድስት የመፍትሔ ሃሳቦችን አቅርበው ነበር። ከስድስቱ ተግባራዊ ያልተደረገው 'ቀጥተኛ ጦርነት መክፈት' የሚለው ብቻ ነው" ይላሉ።

ይሁን እንጂ ወደ ቀጥታ ጦርነት መግባት ራሳቸውንም ሰለባ ስለሚያደርጋቸው አሁን ባሉበት ይቀጥላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ፈቅ አሕመድ አክለዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኙ አቡሃሽምም ይህንኑ ሃሳብ ይጋሩታል።

"የአባይ ጉዳይ በይበልጥ ሊፈታ የሚችለው በኢትዮጵያና በግብፅ ነው" ያሉት አቡሃሽም፤ ግብፆችም ሆኑ ሱዳኖች የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች ለመደገፍ ወይም ላለመደገፍ የሚወስኑት ለአባይ ሲሉ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከ80 በመቶ በላይ ተገንብቶ ያለቀ በመሆኑና የሚቀለበስ ጉዳይ ባለመሆኑ በተለይ ግብፆቹ ምን ዓይነት መፍትሔ ነው የሚፈልጉት የሚለው ጉዳይ እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን አቡሃሽም ተናግረዋል።

"ግብፅ ግድቡን አፈርሳለሁ ብትል እንኳን በራሷ ላይ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ከባድ በመሆኑ፤ ይህም ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በድርድር መቀጠሉ ጥሩ ነው የሚሉት አቶ ፈቅ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ የሌሎችንም ጥቅም ሳትነካ፤ በአሜሪካ ተጀምሮ የነበረውን የስምምነት መርሆዎችና ይዘቶችን በመተው በአዲስ ስልት ድርድር በማካሄድ ወደ ተሻለ ስምምነት መምጣት እንደምትችል ተናግረዋል።

ቀጠናው ውስብስብ ችግር ውስጥ ይገባ ይሆን?

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሰሜኑ ጦርነት፣ የአልፋሽቃ ድንበር ውዝግብ፣ የግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ውዝግብ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ፍላጎቶች፣ የአረብ አገራት ሚና ቀጠናውን ወደ ውስብስብ ችግር ያመሩታል የሚል ስጋት አለ።

የፖለቲካ ተንታኙ አቡሃሽም ግን ይህ የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ወይም በወታደራዊ መንገድ በቶሎ መጠናቀቁ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው ጠቃሚ ነው ይላሉ።

"የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን የውስጥ ጉዳዩ አድርጎ ሊጨርሰው እየሞከረ ነው" የሚሉት ተንታኙ ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቁ ለሌሎች አገራት ጣልቃ መግባት በር ሊከፍት ይችላል ብለው ያምናሉ።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ እየተተራመሰች የአባይና የግድቡ ጉዳዮችን የሚያዘናጉ እና የሚያደናቅፉ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለግብፆች አመቺ ይሆናል ይላሉ።

በሌላ በኩል ኤርትራ ህወሓትን እንደ ጠላት እንደምታይ የጠቀሱት ተንታኙ፤ የህወሓት ጥንካሬ እያየለ ከሄደ ኤርትራ በቀጥታ ጦርነቱ ውስጥ ልትገባ የምትችልበት ዕድል እንዳለ ይጠቅሳሉ።