የሱዳን ጦር ሥልጣን የተቆጣጠረው የእርስ በርስ ጦርነትን ለመከላከል ነው - የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ወታደራዊ ኃይሉ ሰኞ ዕለት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው "የእርስ በርስ ጦርነትን" ለመከላከል ነው አሉ።
አክለውም ከሥልጣን የተነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በጄኔራሉ ቤት "ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ" ተጠልለው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
በዋና መዲናዋ ካርቱም መንገዶች፣ ድልድዮች እና ሱቆች ተዘግተው ሕዝባዊው የአደባባይ ላይ ተቃውሞ ቀጥሏል። የስልክ እና የኢንተርኔት መስመሮችም ተቋርጠዋል።
በአገሪቱ የተነሳውን ቀውስ ተከትሎም በትንሹ 10 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
"ባለፈው ሳምንት ያየናቸው አደጋዎች አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊመሯት ይችሉ ነበር" በማለት ጄኔራል ቡርሐን ማክሰኞ ጥቅምት 16/2014 ዓ.ም በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
"በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እቤታቸው ነበሩ ነገር ግን ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሰግተን ነበር" ሲሉም አክለዋል።
"ትላንትና ማታ አብሬው ነው ያመሸሁት። ህይወቱንም በተለመደ መልኩ ቀጥሏል። የተፈጠረው ቀውስ ሲቀረፍ እና ሁሉም ስጋቶች ሲወገዱ ወደ ቤቱ ይመለሳል።"
ጄኔራሉ የአገሪቱን የሲቪል አስተዳደር ማፍረሳቸውን፣ የፖለቲካ መሪዎች ማሰራቸውንና የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በፀጥታ ኃይሎች ላይ ሰላማዊ ዜጎችን አነሳስተዋል በሚልም የአስቸኳይ ጊዜ ማወጃቸውን አስረድተዋል።
በካርቱም የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ መሐመድ ኡስማን ጄኔራል ቡርሐን ረዘም ያለ የሚኒስትሮችን ዝርዝር ማዘጋጀታቸው እና በሁለት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ሹመቶችን እንደሚያሳውቁ ቃል መግባታቸው ከመፈንቅለ መንግሥቱ በፊት ሰፊ እቅድ መጠንሰሱን ያሳያል ብሏል።
ከሰሞኑ የተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት ዓለም አቀፍ ውግዘትን አስከትሏል። አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ እንዲሁም ሱዳን አባል የሆነችባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት የሐምዶክ የካቢኔ አባላትን ጨምሮ የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ሱዳን አፍሪካን እና እስያንን ከሚጎዱ "የመፈንቅለ መንግሥት ወረርሽኞች" አካል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ የዓለም "ታላላቅ ኃያላን" በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኩል "ውጤታማ የሆነ እርምጃ ወይም ቅጣት" እንዲሰነዝሩ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ለሱዳን የምትሰጠውን 700 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ያገደች ሲሆን የአውሮፓ ሕብረትም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ሁለቱም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሲቪል መንግሥት ወደነበረበት እንዲመለስ ጠይቀዋል።
ከሰኞ ጀምሮ ወታደሮች በመዲናዋ ካርቱም ቤት ለቤት አሰሳና ፍተሻ እያደረጉ የተቃውሞ አስተባባሪዎች እያሰሩ መሆኑ ተዘግቧል።
በዋና ከተማው በተለይም በመሀል ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ የመኖሪያ ሰፈሮች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰልፈኞች ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።
የካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተዘግቷል፣ እንዲሁም ሁሉም በረራዎች እስከ መጪው ቅዳሜ ተሰርዘዋል።
የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በሱዳን ያሉ ዶክተሮች ከድንገተኛ ህመም በስተቀር በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ባሉ ሆስፒታሎች ውስጥ ለመስራት ፈቃደኛ አይደሉም ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2019 ለአስርት ዓመታት ሱዳንን አንቀጥቀው የገዙት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሲቪል መሪዎች እና በወታደራዊ አቻዎቻቸው መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።
በሲቪል እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል የተደረገው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ሱዳንን ወደ ዲሞክራሲ ለመምራት የተነደፈ ቢሆንም ከባለፈው አንድ ወር በፊት የተደረጉ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ግን በተፃራሪው አገሪቷ በተቃራኒው አቅጣጫ እየሄደች እንደሆነ ያመላከተ ነው።
የስልጣን መጋራት ምክር ቤት መሪ የነበሩት ጄኔራል ቡርሐን ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀው ምርጫው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023 ሐምሌ ወር ሊካሄድ እንደታቀደም ተናግረዋል።












