የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክን በቤታቸው እንዳስጠለሏቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሥልጣናቸው በመፈንቅለ መንግሥት ተወግደው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስተር አብደላ ሐምዶክ በመንግሥት ግልበጣው መሪ ጄነራል ቤት ውስጥ መሆናቸው ተነገረ።
የመፈንቅለ መንግሥት አካሂደው የሽግግር መንግሥቱን ካፈረሱ በኋላ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከሥልጣን የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር በእርሳቸው ቤት ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
ጄነራሉ ጨምረውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በእራሳቸው ቤት ቆይተው ቢሆን ኖሮ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችል እንደነበር አመልክተዋል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ሰኞ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ በመላዋ ሱዳን አውጀዋል።
በማለዳ በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት የሽግግር መንግሥቱ ሲቪል አባላት የነበሩ በርካታ ባለሥልጣናት በወታደሮች ቁጥጥር ስር መግባታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ግን በቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ መሆናቸው ተገልጾ ነበር።
ከአገሪቱ የጦር ሠራዊት ወገን የሱዳን የሽግግር መንግሥት ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር የነበሩት ጄነራል አልቡር ሐን በሲቪሎች የሚመራውን መንግሥት በትነው ነው ሥልጣን የተቆጣጠሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የት እንዳሉ አስካሁን ሳይታወቅ ቆይቶ ዛሬ በጄነራሉ መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ቡርሐን አስታውቀዋል።
የአገሪቱ ከፍተኛው ጄነራልና በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት አል ቡርሐን የጦር ሠራዊቱ የመሪነቱን መንበር ለመያዝ የተገደደው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይከሰት በሚል መሆኑን ተናግረዋል።
ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ሲቪሎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ ሲያነሳሱ ነበር ብለዋል።
ጨምረውም ከሥልጣን የተወገዱት የአገሪቱ ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሚገኙት "ለደኅንነታቸው ሲባል" በጄነራሉ ቤት ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ ዛሬ ወደ እራሳቸው ቤት እንደሚመለሱ አመልክተዋል።
ጄነራሉ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግሥት ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከባድ ውግዘት የገጠማቸው ሲሆን አሜሪካ ለሱዳን ልትሰጥ ያቀደችውን የ700 ሚዮን ዶላር ድጋፍ ማዘግየቷን አስታውቃለች።
ነገር ግን ጄነራል ቡርሐን የሚመሩት አስተዳደር ሲቪሎች የሚሳተፉበት ሽግግር ሂደት እንደሚኖርና አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ቃል ገብተዋል።
ሰኞ ዕለት የታጠቁ ወታደሮች በርካታ የአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ሲቪል ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክም አንዱ መሆናቸው የተነገረ ቢሆንም ያሉበት ሳይታወቅ ቆይተዋል።
በአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ ላይ ሰኞ የወጣ መግለጫ፤ ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ስር የማዋል ድርጊት የተፈጸመው "በጥምር ወታደራዊ ኃይሎች" መሆኑን እና የተያዙት ሰዎች ያሉት "በማይታወቅ ስፍራ" መሆኑን አመልክቷል።
ጨምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ መፈንቅለ መንግሥቱን እንዲደግፉ ግፊት ቢደረግባቸውም መቃወማቸውን ገልጾ፤ ሕዝቡ በሰላማዊ ተቃውሞ "አብዮቱን እንዲከላከል" ጥሪ አቅርበዋል ብሏል።
ከዋና ከተማዋ ካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ ያለውን የአገሪቱን የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤትን ወታደሮች ጥሰው እንደገቡ የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ በቆየችው ሱዳን ከአሁኑ መፈንቅለ መንግሥት በተጨማሪ በመስከረም ወር ላይ ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተካሂዶ ከሽፎ ነበር።
መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ከተሰማበት ሰኞ ማለዳ ጀምሮ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በሌሎችም ስፍራዎች ድርጊቱን በመቃወም ሱዳናውያን ድምጻቸውን እያሰሙ ሲሆን ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ለሁለተኛ ቀን በቀጠለው ተቃውሞ በካርቱም ውስጥ የሚገኙ በርካታ መንገዶች፣ ድልድዮች እና ሱቆች የተዘጉ ሲሆን የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነቶች ተቋርጠዋል።














