የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት፡ ቢያንስ ሦስት ተቃዋሚዎች ሲገደሉ በርካቶች ለጉዳት ተዳረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሱዳን ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣን መቆጣጠሩን ተቃውመው አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ ወታደሮች በተኮሱት ተኩስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 80 የሚሆኑ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው ተዘገበ።
ተቃዋሚዎቹ አደባባይ የወጡት ወታደራዊ ኃይሉ የሲቪል አስተዳደሩን ከበተነ፣ የፖለቲካ መሪዎችን ካሰረ እና በአገሪቷ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ በኋላ ነው።
ወታደሮች የተቃውሞውን አስተባባሪዎች ለመያዝ በዋና መዲናዋ ካርቱም የቤት ለቤት አሰሳ እያደረጉ እንደሆነም ተነግሯል።
በሱዳን የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በዓለም ዙሪያ የተወገዘ ሲሆን አሜሪካ ለእርዳታ የምትሰጠውን 700 ሚሊየን ዶላር አቁማለች።
መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት ጀነራል አብደል ፈታህ ቡርሃን በአገሪቷ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ተጠያቂ ተደርገዋል።
የሲቪል መሪዎችና አቻቸው የወታደራዊ መሪዎች ከሁለት ዓመት በፊት አገሪቷን ለረዥም ጊዜ ሲመሩ የነበሩት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።
ሰኞ ምሽት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች በካርቱምና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ በመውጣት የሲቪል አስተዳደሩ እንዲመለስ መጠየቃቸውን የቢቢሲ አረብኛ ዘጋቢ መሀመድ ኦስማን ዘግቧል።
አንድ ጉዳት የደረሰበት ተቃዋሚ ከወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ እግሩ ላይ መመታቱን ለቢቢሲ የተናገረ ሲሆን ሌላኛው ተቃዋሚም ጦሩ መጀመሪያ ላይ ቦንብ እንደወረወረ እና ከዚያም በቀጥታ ጥይት መተኮሱን ተናግሯል።
" ሁለት ሰዎች ሞተዋል ፤ ይህንንም በዐይኔ ተመልክቻለሁ" ብሏል አል ታይብ መሀመድ አህመድ።
የሱዳን ሐኪሞች ማሕበር እና የማስታወቂያ ሚኒስቴር የተተኮሰው ከጦሩ መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ መሆኑን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በከተማዋ ካሉ ሆስፒታሎች የወጡ ምሥሎችም ሰዎች ልብሳቸው በደም ተነክሮ እና በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸው ያሳያሉ።
ተቃዋሚዎች የመኪና ጎማዎችን በማቃጠልና ድንጋይ በማስቀመጥ መንገድ ዘግተዋል። በርካታ ሴቶችም "ወታደራዊ አገዛዝ አንፈልግም" በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የከተማዋ አውሮፕላን ማረፊያም የተዘጋ ሲሆን ዓለም አቀፍ በረራዎችም ታግደዋል። ኢንተርኔትና የስልክ መስመሮችም ተዘግተዋል።
የሴንትራል ባንክ ሰራተኞች በመላ አገሪቷ አድማ መትተዋል። ሒሞችም በጦሩ በሚመሩ ሆስፒታሎች ከድንገተኛ ሕክምና በስተቀር አንሰራም ብለዋል።
የዓለም መሪዎች ጦሩ አገሪቷን መቆጣጠሩን ተከትሎ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ በሱዳን በቁም እስር ላይ ያሉና የት እንዳሉ የማይታወቁ የፖለቲካ መሪዎች እንዲፈቱ በመጠየቅ ዩናይትድ ኪንግደምን፣ አውሮፓ ሕብረትን ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ሱዳን አባል የሆነችበትን የአፍሪካ ሕብረትን ተቀላቅላለች።
በቤት ውስጥ እስር እንደሚገኙ ከተነገረው የፖለቲካ መሪዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና ባለቤታቸው እንዲሁም የካቢኔ አባላቶቻቸው እና ሌሎች የሲቪል መሪዎች ይገኙበታል።
የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው ሰኞ ጠዋት ልዩ የደህንነት አባላት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት በመሄድ ሃምዶክ በመፈንቅለ መንግሥቱ እንዲስማሙ ሞክረው የነበሩ ቢሆንም እርሳቸው ግን ሳይስማሙ ቀርተዋል።
ሱዳን እአአ 2019 አገሪቷን ለረዥም ጊዜ የመሩት ኦማር አል ባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የሲቪልና የወታደራዊ መሪዎች ሥልጣን በመጋራት ስምምነት አገሪቷን እየመሩ ነበር።
ስምምነቱ አገሪቷን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ያለመ ቢሆንም ቀደም ብሎ በርካታ መፈንቅለ ሙከራዎች ተደርገዋል። ለመጨረሻ ጊዜ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተካሄደውም ከአንድ ወር በፊት ነበር።
የሥልጣን መጋራት ስምምነቱን መሪ የነበሩት ጀነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን የአሁንን መፈንቅለ መንግሥት የመሩ ሲሆን መፈንቅለ መንግሥቱ በፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት የተፈጠረውን "የአብዮቱን አካሄድ ለማስተካከል" አስፈላጊ ነበር ብለዋል።













