መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወሙ ሱዳናውያን በአደባባይ ድምጻቸውን ማሰማት ቀጥለዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን ጦር ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን ተከትሎ የአገሪቱ ዜጎች ለሁለተኛ ቀን አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።
በመዲናዋ ካርቱም እንዲሁም በሌሎችም ከተሞች መንገድ ዘግተው የሱዳንን ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ተቃውሟቸውን ገፍተውበታል።
መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም ለሁለተኛ ቀን አደባባይ ከወጡት ዜጎች መካከል ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መጎዳታቸው ተዘግቧል።
ፖሊሶች በተቃዋሚዎች ላይ እንደተኮሱ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ተሰማርቶ ካርቱምን ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች እንደተዘጉም ተገልጿል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሲቪል አመራሩን በትነው፣ አመራሮቹን በቁጥጥር ስር አውለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገጉት ትናንት ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ በሱዳን ጉዳይ ላይ እንደሚመክር የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
ጄነራል ቡርሐን ፖለቲካዊ ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት መፈንቅለ መንግሥቱ እንደተካሄደ ተናግረዋል።
ወታደሮች ካርቱም ውስጥ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የሕዝባዊ ተቃውሞ መሪዎችን እያሰሩ ይገኛሉ። የካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመዘጋቱም ባሻገር አብዛኛው የስልክ መስመር እና ኢንተርኔት ተቋርጧል።
የሱዳን ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ እንደመቱ የተዘገበ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎች በወታደራዊ ኃይሉ በሚመሩ ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት አንሰጥም ማለታቸውም ተሰምቷል።
እአአ በ2019 የቀድሞው መሪ ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሲቪል የሚመራው እና ወታደራዊው የሽግግር አስተዳደር መካከል እምብዛም ስምምነት አልነበረም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ወታደራዊ ኃይሉ የወሰደውን እርምጃ "የሱዳንን ሰላማዊ አብዮት የከዳ" ሲሉ ገልጸውታል።
አሜሪካ 700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለሱዳን ላለመስጠት ወስናለች።

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED
ትናንት ለሊቱን በሙሉ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሱዳናውያን ዛሬም የሲቪል አመራሩ እንዲመለስ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
"ሕዝቡ የሚፈልገው የሲቪል አመራር ነው" "ወታራዊ አስተዳደር አንፈልግም" ሲሉ መፈክር አሰምተዋል። ከተቃዋሚዎቹ መካከል በርካታ ሴቶችም ይገኙበታል።
ፖሊሶች ተቃዋሚዎች ላይ ቢተኩሱም እንኳን ሕዝቡ ድምጹን ማሰማቱን ቀጥሏል።
አንድ ጉዳት የደረሰበት ተቃዋሚ ለሮይተርስ የዜና ወኪል በወታደራዊው አስተዳደር ጽህፈት ቤት አቅራቢያ በወታደሮች እግሩን በጥይት መመታቱን ገልጸዋል።
ወታደሮች መጀመሪያ ላይ የፕላስቲክ ጥይት ቆየት ብለው ግን እውነተኛ ጥይት መተኮስ እንደጀመሩ ሌላ ተቃዋሚ ተናግሯል።
አልታይብ ሞሐመድ አሕመድ የተባለ ግለሰብ "ሁለት ሰዎች ሞተው አይቻለሁ" ብሏል።
የሱዳን የሐኪሞች ማኅበር እና የማስታወቂያ ሚንስቴር ከወታደራዊ አስተዳደር ዋና መቀመጫው ቅጥር ጊቢ ውጪ ተኩስ እንደነበር በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
ከሆስፒታሎች የወጡ ምስሎች ሰዎች የተለያየ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው እና ልብሳቸው በደም ተነክሮ ያሳያሉ።
የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የተባበሩት መንግሥታት የሲቪል አመራሮች ከቁም እስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክን ጨምሮ እነዚህ በቁም እስር ላይ ያሉት አመራሮች አሁን ላይ የት እንደታሰሩ አይታወቅም።
ሐምዶክ መፈንቅለ መንግሥቱን ለመደገፍ ባለመስማማታቸው ትላንት ከመኖሪያ ቤታቸው ጦር ኃይሉ ልዩ ኃይል መወሰዳቸው ይታወሳል።
እአአ 2019 ላይ በወታደራዊው እና በሲቪሉ አመራር መካከል የተደረሰው ስምምነት ሱዳንን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለማሸጋገር ያለመ ነበር።
ነገር ግን የአመራሮች አለመስማማት እና የመፈንቅለ መንግሠት ሙከራን ጨምሮ ብዙ መሰናክሎች ገጥመውታል።
የሽግግር ወቅት ሥልጣን የመጋራት ሉአላዊ ምክር ቤትን ይመሩ የነበሩት የአሁኑ የመፈንቅለ መንግሥት መሪ ጄነራል ቡርሐን ናቸው።
ሱዳንን ወደ ሲቪል አመራር ለማሸጋገር ቁርጠኛ እንደሆኑ ሲናገሩም ተደምጠዋል።
በሱዳን እአአ በሐምሌ 2023 ምርጫ ይደረጋል ተብሏል።












