የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ያለው ወታደራዊ ግጭት መባባስ እንዳሳሰበው ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, AFrican Union
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኢትዮጵያ ያለው ወታደራዊ ግጭት መባባስ እንዳሳሰባቸውና በቅርበትም እየተከታተሉት እንደሆነ አስታውቀዋል።
ህብረቱ በዛሬው ዕለት በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ ሊቀ መንበሩ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ሰሞናት ያወጡትን መግለጫም በማስታወስ የጦርነቱ ተሳታፊ ሁሉም ወገኖች የኢትዮጵያን ግዛት አንድነት፣ ብሄራዊ ሉዓላዊነት እንዲጠብቁ በድጋሚ አሳስበዋል።
በአገር ጉዳይ ላይ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲገቡም አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ ሊቀመንበሩ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የዜጎች ህይወትና ንብረት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር፣ እንዲሁም የመንግስት መሠረተ ልማት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ አክለውም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ደጋፊዎቻቸው በማንኛውም ማህበረሰብ ላይ የበቀል እርምጃ እንዳይወስዱ እንዲሁም ከጥላቻ ትርክቶች፣ ክፍፍልንና ግጭቶችን ከሚያበረታቱ ሁኔታዎች እንዲቆጠቡ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የጦርነቱ ተዋናዮች ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ህግጋትን በማክበር በተለይም የሲቪሎችን ጥበቃ እና በችግር ላይ ያሉ ህዝቦች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው በማድረግ ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን መወጣትም አለባቸው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአፍሪካ ህብረት ከጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ጋር የጋራ ስምምነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ ቁርጠኝነት እንዳለውም የድርጅታቸውን አቋም አሳውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከህብረቱ አፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ውይይት እንዲጀመርም ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።












