የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስልጣን አስረከበ

የፎቶው ባለመብት, FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አዲስ ለተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዛሬው ዕለት ስልጣን አስረክቧል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 24፣ 2014 ዓ.ም በስድስተኛው ዙር 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ነው የስልጣን ርክክቡን አዲስ ከተቋቋመው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር ያደረገው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኢትዮጵያ 11ኛው ክልል በመሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅናን ያገኘው በባለፈው ሳምንት መስከረም 20፣ 2014 ዓ.ም ነው።
11ኛውን ክልል ያቋቋሙት የምዕራብ ኦሞ ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ ፣ የዳውሮ ፣ የሸካ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ አፈ ጉባኤዎችም በስልጣን ርክክቡ ወቅትም ተገኝተው ነበር።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በምክር ቤቱ ተገኝተው ባደረጉትም ንግግር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመሆን ጥያቄ ሂደት ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መካሄድ እንዲችል ክልላቸው ሲሰራ መቆየቱን መናገራቸውም ተዘግቧል።
ርእሰ መስተዳድሩ አዲስ የተቋቋመው ክልል በፍጥነት አዲሱ ክልል በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርድ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበትና ከፋይናንስ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በኮሚቴ የሚታይና ለመንግስት የሚቀርብ መሆኑንም አስረድተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ድምጽ ለመስጠት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመዝግበው ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል።
በምርጫው ከተሳተፉት መካከልም አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል ሥር ወጥተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመባል መዋቀራቸውን በመደገፍ 1 ሚሊዮን 221 ሺህ 92 ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል።












