የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች 11ኛ ክልልነት በፌደሬሽን ምክር ቤት ጸደቀ

የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክልልነት ሕዝበ ውሳኔን አጽድቆታል።
11ኛው የኢትዮጵያ ክልል የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልነት የጸደቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 20/ 2014 ዓ. ም. ባካሄደው 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ 11ኛው ክልል እንዲሆን መስከረም 20/ 2014 ዓ. ም. ድምጽ መሰጠቱ ይታወሳል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማስተላለፉን ተከትሎም የዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ተካሂዷል።
በቀጣይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቀድሞ ከነበረበት የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጋር የሥልጣን ርክክብ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በ11ኛው ክልል ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል በተለያየ አወቃቀር ሥር የነበሩት የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች በአንድነት ክልል ይሆናሉ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ድምጽ ለመስጠት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመዝግበው ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል።
በምርጫው ከተሳተፉት መካከልም አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል ሥር ወጥተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመባል መዋቀራቸውን በመደገፍ 1 ሚሊዮን 221 ሺህ 92 ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል።














