ምርጫ 2013፡ በአማራ ክልል እነማን፣ የት ይወዳደራሉ?

ደሴ
የምስሉ መግለጫ, ደሴ

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነገ ይደረጋል።

ድምጽ ለመስጠት በአገር ደረጃ ወደ 38 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተመዝግቧል።

ከዚህ አሐዝ ውስጥ በአማራ ክልል የተመዘገቡ ድምጽ ሰጪዎች ከ7 ሚሊዮን ይልቃሉ።

በአማራ ክልል ከጠቅላላ ድምጽ ሰጪዎች ውስጥ 46 ከመቶ መራጮች ሴቶች ናቸው።

በአማራ ክልል ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች ብዛት 18 ነው።

ከእነዚህ መካከል ብልጽግና፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የመላውኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዲኃን)፣ እናት፣ ኅብር ኢትዮጵያ ይወዳደራሉ።

በተጨማሪም የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ አዲስ ትውልድ፣ ራያ ራዩማ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ነጸናትና እኩልነት ፓርቲ፣ ቅማንት ዲሞክሲያዊ ፓርቲና ሌሎች 6 ፓርቲዎች ዕጩ አቅርበዋል።

በአማራክ ክልል 138 የምርጫ ክልሎች ይገኛሉ።

ከእነዚህ መሀል 10 የሚሆኑት የምርጫ ክልሎች ላይ ነገ ምርጫ አይካሄድባቸውም።

ከአስሩ ውስጥ ዘጠኙ ላይ ምርጫው የማይካሄደው በአንድም በሌላም ምክንያት ከጸጥታና ከሰላም ጋር በተያያዘ ነው።

የተቀረው አንዱ ምርጫ ክልል ላይ ምርጫው ነገ የማይካሄደው ደግሞ ከድምጽ መስጫ ወረቀት የኅትመት ችግር ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ስህተት ነው።

ከእነዚህ ውጪ በተቀሩት 128ቱ የምርጫ ክልሎች ግን ነገ ምርጫ ይደረግባቸዋል።

ለጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም ምርጫ ቀጠሮ የተያዘላቸው አስሩ የአማራ ምርጫ ክልሎች የሚገኙት በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ 5፣ ማዕከላዊ ጎንደር 3 እና ደቡብ ወሎ 1 የምርጫ ክልሎች ናቸው።

እነዚህም ኤፌሶን፣ አንኮበር፣ አርጎባ ልዩ፣ ማጀቴ፣ ሸዋሮቢት፣ ጭልጋ ቁጥር አንድና ጭልጋ ቁጥር ሁለት፣ ሰቆጣ፣ ላይ አርማጮህና አምባሰል ናቸው።

ከአምባሰል በስተቀር ሌሎቹ ምርጫ ክልሎች በሙሉም ሆነ በከፊል ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ወደ ጳጉሜ 1 የተገፉ ናቸው።

ከኅትመት ጋር በተያያዘ የመራጮች ቅጽ በትክክል ሳይታተም ስለቀረ ወደ ጳጉሜ 1 የተዘዋወረው ምርጫ ክልል ደግሞ አምባሰል ነው።

ማን የት ይወዳደራል?

የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር እና አካባቢው በሦስት የምርጫ ክልል የተዋቀረ ነው።

እነዚህም ባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል፣ ዘጌ መሸንቲ ምርጫ ክልል እና ጢስ አባይ ዘንዘልማ ምርጫ ክልል ናቸው።

ፓርቲዎች በያንዳንዱ ምርጫ ክልል ውስጥ አንድ ተወካይ ለተካዮች ምክር ቤት፣ ሌሎች ሁለት ተወካዮች ደግሞ ለክልል ምክር ቤት አቅርበዋል።

በባሕር ዳር ምርጫ ክልል የአብን የቀድሞ ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለተወካዮች ምክር ቤት ይወዳደራሉ።

አብን ከዶ/ር ደሳለኝ ሌላ በዘጌ መሸንቲ ምርጫ ክልል አቶ ህሩይ ባዩን፣ በጢስ አባይ ምርጫ ክልል ደግሞ ዘመነ ኃይሉን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ኢዜማ የአብኑ ዶ/ር ደሳለኝ በሚወዳደሩበት ምርጫ ክልል አቶ ጸጋዬ ፈጠነን አቅርቧል።

የባህርዳር ከተማ

አብን በአገሪቱ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት በድምሩ 513 ዕጩዎችን ያቀረበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብላጫውን የሚይዙት ግን ከፍተኛ ድጋፍ አለኝ በሚለው የአማራ ክልል ነው የሚገኙት።

አብን በጠቅላላ ካቀረባቸው 513 እጩዎች 419 እጩዎችን በአማራ ክልል ልዩ ልዩ ምርጫ ክልሎች ውስጥ ቀርበዋል።

በይበልጥ ከሚታወቁት ዕጩዎች መካከል አቶ ክርስቲያን ታደለን፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ቋሪት ምርጫ ክልል ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸዋል።

አቶ ጣሒር መሐመድን ደግሞ በእንፍራንዝ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

የአብን ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በለጠ ሞላ በቆቦ፣ ምክትላቸው አቶ ዩሱፍ ኢብራሒም በደሴ፣ እንዲሁም አቶ ጋሻው መርሻ በእስቴ ይወዳደራሉ።

ብልጽግና የቀድሞውን የገቢዎች ሚኒስትር፣ የአሁኑን የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታን በጎንደር ከተማ ምርጫ ጣቢያ-1 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን በጎንደር ከተማ ለክልል ምክር ቤት ብልጽግናን ወክለው ይወዳደራሉ።

ኢዜማ እማዋይሽ ዓለሙን በዚሁ ምርጫ ክልል አቶ አገኘሁን እንዲገዳደሩ አቅርቧቸዋል።

ኢዜማ በ128ቱም የአማራ ክልል ምርጫ ክልሎች ውስጥ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት ሙሉ ዕጩዎችን ያቀረበ ፓርቲ ነው።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ለክልል ምክር ቤት በደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ ብልጽግናን ወክለው ይወዳደራሉ።

የታሪክ ተመራማሪው ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ማቻከል ወረዳ ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ። የወከሉት ብልጽግናን ነው።

ዶ/ር ድረስ ሳህሉ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ናቸው። ብልጽግናን ወክለው ለክልል ምክር ቤት በባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ካሳው በደብረታቦር ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ናቸው። የወከሉትም ብልጽግናን ነው።

የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን በአዊ ዞን፣ ቻግኒ ከተማ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግናን ወክለው ቀርበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የደሀና ወረዳ ውስጥ ለክልል ምክር ቤት ብልጽግናን ወክለዋል።

ብልጽግና፣ በአማራ ክልል፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም አለኸኝን- በደብረ ማርቆስ፣ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለምን በፍኖተሰላም ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።

እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን በደቡብ ወሎ ደላንታ ዳውንት፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን በፎገራ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለውን በሰሜን ወሎ ዞን፣ ዋድላ ወረዳ አሰልፏል፡፡

አቶ ላቀ አያሌው የገቢዎች ሚኒስትር ናቸው። ብልጽግናን ወክለው ደጋዳሞት ላይ ይወዳደራሉ።

አቶ ስዩም መኮንን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ነበሩ። ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰቆጣ ምርጫ ክልል ዕጩ አድርጎ አቅርቧቸዋል።

የአሁኑ የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ንጉሤ ምትኩ በአዊ ብሔረሰብ ዞን፣ በቲሊሊ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግናን ወክለው ይወዳደራሉ።

ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ናቸው። ብልጽግናን ወክለው ለክልል ምክር ቤት በምዕራብ ጎጃም፣ መርአዊ ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ-2 ምርጫ ክልል ብልጽግናን ወክለው ቀርበዋል።

አቶ አበረ አዳሙ ደራሲና ኪነጥበብ ባለሙያ ናቸው። ምሥራቅ ጎጃም ዞን ረቡዕ ገበያ ምርጫ ክልል ብልጽግናን ወክለው ይወዳደራሉ።

በአማራ ክልል የሚሳተፉት 18 ፓርቲዎች በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል አንድ-አንድ የተወካዮች ምክር ቤት እጩና ሌሎች 2 ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል።

ምርጫ 2013