ምርጫ 2013፡ በአዲስ አበባ ማን፣ የት፣ ከማን ጋር ይፎካከራል?

አዲስ አበባ ለዘመናት የአገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ማዕከል ሆና ቆይታለች። በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አዲስ አበባን ማዕከል ባደረገ መልኩ ፖሊሲዎችን ቀርፀው ሲንቀሳቀቁ ይታያሉ።
ይህንን ሁኔታም በዘንድሮው ምርጫም የሚታይ ሲሆን ውድድሩም በአዲስ አበባ ጠንከር ሊል እንደሚችል የሚወደዳሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር ጨምሮ፣ ስመ ጥር ፖለቲከኞች በዕጩነት መቅረባቸው ማሳያ ነው።
ለመሆኑ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወከል የሚወዳደሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን እና ፖለቲከኞችን እነማን ናቸው።
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የሚከተሉትን ፖለቲከኞች ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዕጩነት አቅርበዋል።

ቂርቆስ
ጠንካራ ፉክክር ከሚጠበቅባቸው ስፍራዎች አንዱ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፓርቲ በቂርቆስ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የምጣኔ ሃብት ባለሙያውንና የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ክቡር ገናን በዕጩነት አቅርቧል።
ብልጽግና በበኩሉ የመከላከያ ሚንስትሩን ቀነኣ ያደታ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩን ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጀነር) እና የቀድሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ የአሁኑ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሸነር አቶ ንጉሡ ጥላሁንን ለከተማው ምክር ቤት በዕጩነት አቅርቧል።
ንፋስ ስልክ
ብልጽግና ፓርቲ በንፋስ ስልክ ላፍቶ የመዲናዋን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በእጩነት አቅርቧል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ በእስር ላይ ያሉት አቶ ስንታየሁ ቸኮልን በንፋስ ስልክ ላፍቶ የምክትል ከንቲባዋ ተፎካካሪ አድርጎ አቅርቧል።
ቦሌ
በቦሌ ብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ዣንጥራር አባይን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልነት በእጩነት አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን መኮንን አምባዬን እንዲሁም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ በበኩሉ በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) አቅርቧል።
የካ
በየካ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በእስር ላይ ያሉትንና የፓርቲውን ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ለከተማዋ ምክር ቤት ወንበር አቅርቧል።
አራዳ
በአራዳ ከፍለ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳባ ደበሌ የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በዕጩነት ቀርበዋል። ከአቶ ዳባ በተጨማሪ አቶ ነብዩ ባዬ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
ኮልፌ ቀራኒዮ
በኮልፌ ቀራኒዮ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ብልጽግናን ወክለው ቀርበዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ ሄኖክ አክሊሉን የኮልፌ ቀራኒዮ ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።
አዲስ ከተማ
ፕ/ሮ ጣሰው ወልደሃና፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ብልጽግናን በመወከል ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ይወዳደራሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስት በ23 ተወካዮች ይወከላል። በዚህም የተለያዩ ፓርቲዎች በ23 የምርጫ ክልሎች ይፎካከራሉ።
በከተማዋ የምርጫ ክልል 3 ብልጽግና የጤና ሚንስትሯን ዶ/ር ሊያ ታደሰን፣ በእጩነት ሲያቀርብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ዶ/ር ጥላሁን ገብረሕይወትን በዚሁ ምርጫ ክልል ያወዳድራል።
በምርጫ ክልል 6 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን በመወከል አቶ ግርማ ሰይፋ የሚወዳደሩ ሲሆን ብልፅግና ፓርቲ ደግሞ በምርጫ ክልል 6 ዶ/ር ኢ/ር ወንድሙ ተክሌን አቅርቧል።
ብልጽግና በምርጫ ክልል 7 በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ አቋም ለአረቡ ዓለም በማንጸባረቅ የሚታወቁት መሐመድ ከማል አሊ አል-አሩሲ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ደግሞ ናርዶስ ስለሺን ተወዳዳሪ አድርጓል።
የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ደግሞ ብልጽግናን በመወከል በምርጫ ክልል 8 በዕጩነት ቀርበዋል።
በምርጫ ክልል 11 ፕ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ብልጽግናና በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ሲሆኑ፣ ሰለሞን ተሰማ (ዶ/ር) ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሁም የጁአልጋው ጀመረ ደግሞ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ቀርበዋል።
የኢዜማ ምክትል መሪ አንዱዓለም አራጌ የምርጫ ክልል 12 እና 13 ዕጩ ሲሆኑ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ደግሞ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ቀርበዋል።
የውሃ፣ መስኖ እና ኢንርጂ ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 17 የብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ዕጩ ሆነዋል።
ከስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ጋር ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በቃሉ አጥናፉ ተጠቃሽ ናቸው።
በምርጫ ክልል 18 ዛዲግ አብርሀ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን በምርጫ ክልል 20 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነዋል።
ከአምባሳደር ዲና ጋር ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገለታዉ ዘለቀ ይገኙበታል።
በምርጫ ክልል 21 እና 22 የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ/ር ይነገር ደሴ የብልፅግና ፓርቲን ሲወክሉ፤ በተመሳሳይ የምርጫ ክልል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓቲው ኢ/ር አንተነህ በለው እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ አባይ ብርሀኑ ወ/ጊዮርጊስ ዕጩ ናቸው።
በምርጫ ክልል 23 ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ሲሆኑ፣ የብልጽግናው የአገር አቀፍ ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዲላሞ ኦቶሬ ደግሞ ብልጽግናን በመወከል ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ይፎካከራሉ።
ብልጽግና ፓርቲ ወኪሉን ባለቀረበበት ምርጫ ክልል 28፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በግል ተወዳዳሪነት ቀርበዋል።
አማሃ ዳኘው ደግሞ በምርጫ ክልል 28 ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲን ወክለው ይወዳደራሉ።
















