ምርጫ 2013፡በምርጫው መዳረሻ የደሴ ከተማ ዝግጅት ምን ይመስላል?

የደሴ ፖሊስ ጣቢያ

6ኛው አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። የተለያዩ ከተሞችም ምርጫውን ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።

ነዋሪዎችም የምርጫውን ቀን ተስፋና ስጋት በተቀላቀለበት ሁኔታ እየተጠባበቁ ነው። ለመሆኑ በምርጫው መዳረሻ የአንዳንድ ከተሞች ዝግጅት ምን ይመስላል?

ደሴ

በአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች አንዷ በሆነችው ደሴ ከተማ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ በተለያየ መልኩ የሚከወኑ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች አልተሰሙም። ይሁን እንጅ ቀደም ብለው የተሰቀሉና የተመራጮችን ፎቶ የያዙ ፖስተሮች አልተነሱም። በከተሞቹ ዋናዋና የመንገድ አካፋዮችና አደባባዮች ላይ ተሰቅለው ይታያሉ።

በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ እንደወትሮው ነው። ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ደሴ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችም የተለመደው እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። በከተማዋ ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንቅስቃሴ ይታያል።

ንግድ ቤቶች ሻጭና ገዥን እያገናኙ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ምርጫውን ተከትሎ የጸጥታ ችግር ይኖራል የሚል ስጋት የላቸውም። ይሁን እንጅ በነዋሪዎች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ "ምርጫው በሠላም ይለፍና . . . " የሚሉ ስጋት አዘል ንግግሮች ይሰማሉ።

የደሴ ከተማ ፖሊስ በከተማዋ ምርጫውን ተከትሎ የጸጥታ ችግር ያጋጥማል የሚል ስጋት ቢኖርም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል።

የደሴ ከተማ ፖሊስ መመሪያ ማሕበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ጌታቸው ሙህየ እስካሁን ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።

በምርጫው ዕለትና ከምርጫው በኋላ የጸጥታ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት አለ ያሉት ምክትል ኮማንደሩ፤ የኬላ ፍተሻዎች፣ የምሽት ቅኝት እና ሌሎች ክትትሎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

"እንደ ጸጥታ አካል ችግር ሊያጋጥም ይችላል ብለን ነው የምንሰራው፤ በቅርቡ በአጎራባች ዞንና ወረዳዎች ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ለከተማችን ሕዝብ ስጋት እንደሚሆን ታሳቢ አድርገን እየሰራን ነው" ብለዋል ምክትል ኮማንደር ጌታቸው።

ምክትል ኮማንደር ጌታቸው ወደ 500 የሚጠጉ የከተማው ፖሊስ ተሰማርቶ እንደሚገኝም አክለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፌደራል ፖሊስ፣ አድማ ብተና እና ሚሊሻዎች ጨምሮ በርካታ የጸጥታ አካላት ተሰማርተዋል ብለዋል። በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ሁለትና ከዚያ በላይ የምርጫ አስፈፃሚ የጸጥታ አካላት መመደባቸውንም ኮማንደሩ አክለዋል።

ምርጫ 2013

በደሴ ከተማ 104 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን 82 ሺህ 177 ነዋሪዎች ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በከተማዋ 11 ፓርቲዎች ይወዳደራሉ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መጨረሱን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ምርጫ ህዝብ በሃገሩ ላይ የስልጣን ባለቤትነቱን በድምፁ የሚያረጋገጥበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ የፖሊስ ኃላፊነት እንደሆነ አስታውሰዋል።

በክልሉ ውስጥ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅም ከምርጫው በፊት፣ በምርጫው እለት እና ከምርጫ በኋላ ፖሊስ ስለሚሰራቸው ተግባራት በቂ ዝግጅት መደረጉንም ኃላፊው አስረድተዋል። በዚህም መሰረት ሁሉም የፖሊስ ኃላፊነቱን ከመወጣቱ በተጨማሪ ኮማንድ ፖስት መቋቁሙንም አስታውቀዋል።

እስካሁንም ባለው ሂደት ከጥቃቅን ችግሮች ውጭ የጎላ ነገር አለመከሰቱንም በዚሁ እለት አስረድተዋል።