'የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች' 11ኛው ክልል በመሆን ሊቋቋም ነው

የፎቶው ባለመብት, NEBE
የኢትዮጵያ አስራ አንደኛው ክልል እንዲዋቀር የሚያስችል ድምጽ በቅርቡ ከተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
መስከረም 20/2014 ዓ.ም ከተካሄደው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ጋር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን ለማወቀር በተሰጠው የሕዝበ ውሳኔ ድምጽ መሠረት በአብላጫ ድምጽ ክልል የመሆን ድጋፍ አግኝቷል።
በዚህም መሠረት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በተለያየ የአወቃቀር ደረጃ ላይ የነበሩት የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች በአንድነት የአገሪቱ አስራ አንደኛ ክልል ሆነው ይመሠረታሉ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅዳሜ መስከረም 28/2014 ዓ.ም ከአንድ ሳምንት በፊት የተካሄደውን የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ባሳወቀበት ውቅት እንደገለጸው፤ በሕዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ ለመስጠት ከ1.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተመዝግበው 1.2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ድምጽ ሰጥተዋል።
ድምጽ ከሰጡት መካከልም አምስቱ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ቤሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ስር ወጥተው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመባል መዋቀራቸውን በመደገፍ 1ሚሊየን 221 ሺህ 92 ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል።
በዚህም ከ50 በላይ ብሔረሰቦች ከሚገኙበት የደቡብ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት በመውጣት በሕዝበ ውሳኔ የራሱን ክልል የመሠረተውን የሲዳማ ክልልን በመከተል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሁለተኛው ሲሆን የአገሪቱም 11ኛ ክልል ይሆናል።
የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርባና 11ኛው ክልል እንደሚዋቀር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዞኖች በክልልነት ለመዋቀር ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ለረጅም ጊዜ በክልልነት የመዋቀር ጥያቄን ሲያነሳ የነበረው የሲዳማ ክልል በቀዳሚነት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ሕዝበ ውሳኔ ተዘጋጅቶለት ነበር ክልል ሆኖ ለመደራጀት የበቃው።
በደቡብ ክልል ለቀረቡ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በፌደራል መንግሥቱና በክልሉ አማካይነት ጥናቶች መካሄዳቸው የተነገረ ሲሆን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲቋጭ ተደርጓል።
ከዚህ ውጪ ያሉና ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች ጉዳይን በተመለከተ አስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
የደቡብ ምዕራን ኢትዮጵያ ብሔሮች ክልል እንዲመሰረት በሕዝበ ውሳኔ አስፋለጊው ድምጽ በመገኘቱ ክልሉን ለማደራጀት የሚያስፈልጉ ሥራዎች በደቡብ ክልልና በዞኖቹ አማካይነት እንደሚከናወን ይጠበቃል።














