ክትባት፡ አዲሱ የወባ ክትባት ለተጠቃሚዎች የሚደርሰው መቼ ነው ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዓለም ጤና ድርጅት በመላው ዓለም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የወባ በሽታ ክትባት ፈቃድ መስጠቱን ተከትሎ በርካታ ተመራማሪዎችና የጤና ባለሙያዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ብቻ በየዓመቱ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 260 ሺ ህጻናትን ለሚገድለው የወባ በሽታ ክትባት መገኘቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን ሕይወት እንደሚታደግ ድርጅቱ አስታውቋል።
ክትባቱ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው ከስድስት ዓመታት በፊት ሲሆን እስከ 40 በመቶ የሚደርሰውን የበሽታውን ቁጥር የሚቀንስ፣ 30 በመቶ ደግሞ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ይታደጋል ተብሏል።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ተመራማሪዎች የክትባት ፕሮግራሙን በጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ ውስጥ ሲያከናውኑ እንደነበረ ተገልጿል።
እስካሁን በተገኙ የምርምሩ ውጤቶች መሰረትም ክትባቱ ከ10 በወባ በሽታ ከሚያዙ ሰዎች መካከል አራቱን መከላከል ይችላል።
ከ8 ሺ በላይ የሚሆኑ ህጻናት እስካሁን ክትባቱን እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት አለመስተዋሉን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
አንዳንድ ተመራማሪዎች ምናልባት የውጤታማነቱ ቁጥር ከዚህ ከፍ ያለ ቢሆን ይመረጥ ነበር ያሉ ቢሆንም፣ የወባ በሽታ በየዓመቱ ከሚገድላቸው ህጻናት አንጻር ይህ ቁጥር ብቻውን የሚሊዮኖችን ህይወት መታደግ እንደሚችል ግን ግልጽ ነው ብለዋል።
ይህ ክትባት በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ የሙከራ ክትባት መርሃ ግብሮች ተደርጎ ስኬታማነቱ መረጋገጡን ተከትሎ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እና በሌሎች አካባቢዎች መጀመር አለበት ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ስራዬን የጀመርኩት በወባ ተመራማሪነት ነው። በዚህ ጥንታዊ እና አስከፊ በሽታ ላይ ውጤታማ ክትባት የምናገኝበትን ቀን ለማየት እጓጓ ነበር። ይህች ቀን ዛሬ ነች" ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም።
አክለውም ለረጅም ዘመናት ሲጠበቅ የነበረው የወባ ክትባት የተዘጋጀው በአህጉሪቷ፣ በአፍሪካውያን ሳይንቲስቶች መሆኑን ጠቅሰው "ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የህጻናት የወባ ክትባት ለሳይንስ፣ ለልጆች ጤና እና ለወባ ቁጥጥር ታላቅ ግኝት ነው" ብለዋል።
ደም በሚጠጡ ትንኞች ንክሻ የሚተላለፈው የወባ በሽታ የደም ሴሎችን በመውረር ከጥቅም ውጪ ያደርጋቸዋል።
የወባ ጥገኛ ተህዋስያንን ለመግደል መድኃኒቶችን፣ ንክሻዎችን ለመከላከል እና ትንኞችን ለመግደል ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ለዘመናት ያገለገሉ ሲሆን ሁሉም የወባ በሽታን ለመቀነስ ረድተዋል።
ነገር ግን አሁንም በዓመት ወደ 230 ሚሊዮን የሚጠጉ የወባ ታማሚዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 400 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ ።
ከዚህ አሃዝ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው የወባ በሽታ በአፍሪካ ውስጥ የሚከሰት ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊትም ከ260 ሺህ በላይ ሕፃናት ሞተዋል።
ክትባቱ ለተጠቃሚዎች የሚደርሰው መቼ ነው?
በመላው አፍሪካ ያሉ ልጆችን ገዳይ ከሆነው በሽታ ለመከላከል ታሪካዊ በተባለው ሁኔታ የወባ በሽታ ክትባት እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለብዙ ሺህ ዓመታት ከቆዩ ዋነኛ መቅሰፍቶች አንዱ ነው የተባለው የወባ በሽታ በርካታ ህፃናትንና ጨቅላዎችን ቀጥፏል።
አዲሱ የወባ በሽታ ክትባት ለመቶ ዓመታት ያህል ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በህክምና ታሪክ ታላቅ ስኬት በሚባል ሁኔታ ክትባቱ ተገኝቷል።
አርቲኤስ፣ ኤስ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ክትባቱ ፍቱንነቱ የተረጋገጠው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው።
በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ የሙከራ ክትባት መርሃ ግብሮች ተደርጎ ስኬታማነቱ መረጋገጡን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እና በሌሎች ክልሎች መጀመር አለበት ብሏል።
አዲሱ ክትባት ለአንድ ሕፃን አራት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በየወሩ እንዲሁም የመጨረሻው ከ18 ወራት በኋላ ይወሰዳል።
ክትባቱ 'ጂኤስኬ' በተባለው ትልቅ የመድሀኒት አምራች ኩባንያ የሚመረት ሲሆን ድርጅቱም ክትባቱን የማምረቻ ወጪ ላይ 5 በመቶ ብቻ ጨምሮ እንደሚሸጠው ገልጿል። ነገር ግን ትክክለኛ ዋጋው ስንት እንደሆነ አልገለጸም።
ክትባቱን ገዝቶ ስለመጠቀም በተመለከተ ደግሞ አገራትና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የሚወስኑት ይሆናል ማለት ነው።
የክትባቱ የሙከራ ፕሮግራም አሁንም በጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ የሚቀጥል እንደሆነ ተገልጿል። አምራቹ ጂኤስኬ ደግሞ 10 ሚሊየን ክትባቶችን ለምርምሩ ስራ በድጋፍ መልክ መስጠቱን የገለጸ ሲሆን እስካሁንም አንድ አራተኛው ጥቅም ላይ ውሏል።
ከዚህ በተጨማሪም አምራች ድርጅቶች፣ 15 ሚሊየን ክትባቶችን በየዓመቱ ማቅረብ እንደሚችል ገልጿል። ክትባቶቹን ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ ከአገራትም ሆነ ከድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የሚገኝ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2022 እና 2023 በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ይችላል።
ነገር ግን ይህ ቁጥር ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል። የአውሮፓውያኑ 2030 ከመድረሱ በፊት 100 ሚሊዮን ክትባቶች የሚያስፈልጉ ሲሆን አሁን በታቀደው መሰረት ግን ይህንን ማሳካት ከባድ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።















