የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ላይ የተደረገ ሙከራ ከፍተኛ ውጤት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኦክስፎርድ የኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እና በቡርኪናፋሶ ሳይንቲስቶች በጋራ የተሰራ አዲስ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በተደረገለት ሙከራ ውጤታማ መሆነ ተገለጸ።
በክትባቱ ላይ በተደረጉት መጀመሪያ ሙከራዎች 77 በመቶ በሆነ ውጤት ስኬታማ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ ይህም አሁን ለህክምና ከሚውሉ መድኃኒቶች አንጻር ውጤታማነቱ በእጅጉ የላቀ ነው ተብሏል።
የህክምና ጉዳዮች መጽሔት በሆነው 'ላንሴት' ላይ የታተመው የጥናቱ ውጤት 450 ከቡርኪናፋሶ የተወጣጡ ህጻናት የተሳተፉበት ሲሆን ከዚህ በኋላ በርከት ያሉ ሰዎች የሚሳተፉበት ሙከራ ይደረግበታል።
በቀጣዩ የሙከራ ሂደትም 4,800 ህጻናት የሚሳተፉ ሲሆን እነዚህም ከቡርኪናፋሶ፣ ከማሊ እና ከኬንያ ናቸው።
"ይህ ሙከራ በጣም አስደሳች የሆነ ውጤታማነት ነው ያሳየው። ክትባቱ ከዚህ በፊት ከነበሩ ህክምናዊች አንጻር የተሻለ የመከላከል ብቃት አሳይቷል።
"በመቀጠል የምናካሂዳቸውን ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ሙከራዎች እየተጠባበቅን ነው። በእነዚህ ሙከራዎች በርከት ያሉ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን በስፋት ቢመረት ምን አይነት ውጤት እንደሚኖረው ለማወቅ ይረዳናል" ብለዋል በቡርኪናፋሶ የጤና ሳይንስ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሃሊዶ ቲንቶ።
ለወባ በሽታ የሚሆን ክትባት ማግኘት በህክምና ምርምር ውስጥ እግጅ ትልቅ ዜና ነው የሚሆነው። ሙከራው በስኬት የሚጠናቀቅ ከሆነ ትልቅ ግኝት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የወባ በሽታ በዓመት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን የሚገድል ሲሆን አብዛኛዎቹ ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ህጻናት ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ለወባ በሽታ የሚሆን አንድ ክትባት ያለ ሲሆን ውጤታማነቱ ደግሞ 50 በመቶ ብቻ ነው።
በአዲሱ ክትባት የመጀመሪያ ዙር ሙከራ ላይ 77 በመቶ ውጤታማነት የታየ ሲሆን በሌሎች አገራትም ላይ ለመሞከር ታቅዷል። በጊዜ ብዛት ደግሞ ቢያንስ በአራት የአፍሪካ አገራት ውስጥ ይሞከራል።
በሙከራው የሚሳተፉት 5 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ደግሞ እድሜያቸው ከሦስት ዓመት በታች የሆኑ ናቸው።
አሁን በሙከራ ላይ የሚገኘው አዲሱ ክትባት ሙሉ ፈቃድ አላገኘም። ነገር ግን ውጤታማነቱ በሙከራዎች በተገቢ ሁኔታ የሚረጋገጥ ከሆነ የበርካቶችን ህይወት የማትረፍ ትልቅ አቅም አለው ተብሏል።















