በኦስካር የተካተተው በኢትዮጵያዊ-ሜክሲኳዊቷ ጀሲካ በሽር የተሠራው ‘የሐረር’ ፊልም- ፈያ ዳኢ

የፎቶው ባለመብት, Janus Films
ፈያ ዳኢ የተሰኘው የጀሲካ በሽር ዘጋቢ ፊልም በኦስካር ለሽልማት የሚወዳደሩ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር ተካተተ።
በኢትዮጵያዊ-ሜክሲኳዊቷ ፊልም ሠሪ ጀሲካ የተዘጋጀው ፈያ ዳኢ በ94ተኛው የኦስካር ሽልማት በዘጋቢ ፊልም ዘርፍ ነው የተካተተው።
የኦስካር ሽልማት (አካዳሚ አዋርድስ) በ10 ዘርፎች የሚያወዳድራቸውን ፊልሞች ይፋ ሲያደርግ የጀሲካ ፊልምም መካተቱ ታውቋል።
ጀሲካ በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገችበት ወቅት ዘጋቢ ፊልሙን ለማጠናቀቅ 10 ዓመታት እንደወሰደባት ገልጻለች።
ቢቢሲ ከወራት በፊት ስለ ፈያ ዳኢ እና ጀሲካ በሽር ያስነበበው ዘገባ እነሆ፦

የጫት ማሳ ውስጥ ናቸው። ንግግራቸው ዝግ ያለ ነው።
ታዳጊው መሐመድ ከወጣት ጓደኛው ጋር የሐረር እርሻ ውስጥ ጫት ይለቅማሉ።
ወጣቱ ወደ አውሮፓ ስደት ጀምሮ ነበር። እናቱ በጣም ስትናፍቀው ግን ጉዞውን እርግፍ አድርጎ ትቶ ከሑመራ ወደ ሐረር ተመለሰ።
የመሐመድ እናት አረብ አገር ሄዳለች። ለመሐመድ ደብዳቤ አትጽፍም። ድምጿ ከጠፋ ሰነባብቷል። መሐመድ በእናቱ ናፍቆት ክፉኛ ይሰቃያል። ረስታኝ ይሆን ብሎ ዘወትር ይጨነቃል።
መሐመድ ባሕር ተሻግሮ እናቱ ጋር መሄድ እንደሚፈልግ ለጓደኛው ይነግረዋል። ጓደኛው ግን "አንተ ገና ልጅ ነህ። ምን ታደርጋለህ?" ይለዋል።
"አገር ቤትን ማስታወስ ስትጀምር ወፎቹ፣ ንጹሕ አየሩ፣ ተፈጥሮው ይናፍቅሀል። የምትጓዘው ከትውስታዎችህ ጋር ነው. . . "

ይህ ንግግር የተቀነጨበው ከ'ፈያ ዳኢ' ዘጋቢ ፊልም ነው። ፊልም ሠሪዋ ኢትዮጵያዊ-ሜክሲኳዊቷ ጀሲካ በሽር ናት። ለ10 ዓመታት ኑሮ በሐረርን በካሜራዋ መዝግባለች።
ሜክሲኮ ሲቲ ነው የተወለደቸው። ያደገችው ደግሞ ሐረር። አራት ልጆች ያሉበት የሞቀ ቤት ውስጥ።
በ1987 (እአአ) ቤተሰቧ ከኢትዮጵያ ሲሰደድ ጀሲካ 16 ዓመቷ ነበር። ከሁለት አሥርታት የስደት ሕይወት በኋላ በእድሜ የገፉትን አያቷን ልትጠይቅ አገር ቤት ተመለሰች፤ አያቷ የተወለዱት ኤጀርሳ ነው።
የ98 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ አያቷን ልታይ ስትመጣ ትንሽ ካሜራ ገዝታ ነበር። ከአያቷ ለአባቷ የሚላክ መልዕክት በካሜራዋ ትቀርጽ ጀመር።
አያትየው ለልጃቸው፣ ለጀሲካ አባት እንዲህ አሉ "አንተ ሁሴን አትመጣም ወይ? እኔ እንደሆነ እያረጀሁ ነው። ሰውነቴ ግን አልለቅ አለኝ። አልሞት አለኝ። አንተን ማየት እፈልጋለሁ። ስለዚህ ናና ገላግለለኝ።"
ይህንን በጣም ግላዊ እና ስሜታዊ መልዕክት ስትቀርጽ ነው ፈያ ዳኢ የተጠነሰሰው።
ከአያቷ ጋር ዳግመኛ ከተገናኘች፣ ዳግመኛ ከተቆራኘች በኋላ ያደገችበትን ማኅበረሰብ ዳግመኛ ትቀርብ ጀመር።
"መልሼ መተሳሰር ጀመርኩ። ሁሌም አገር ቤት እንድመለስ ከውስጤ የሚያባብለኝ ስሜት አለ። ያንን የሚያባብለኝን ነገር ነው ለ10 ዓመት ስቀርጽ የነበረው።"


የፎቶው ባለመብት, Dia Dipasupil
ጀሲካ የዩሲኤልኤ የፊልም ምሩቅ ናት። አዘጋጅ፣ ፕሮዲውሰር እና ሲኒማቶግራፈሯ ጀሲካ ኒው ዮርክ ነው የምትኖረው።
'He Who Dances on Wood' እና 'Hairat' የተባሉ አጫጫር ዘጋቢ ፊልሞችን ከዚህ በፊት ሠርታለች።
ሁለት ሰዓት ገደማ የሚወስደው 'ፈያ ዳኢ' ለዕይታ የበቃው አምና ነው። በፊልሙ ዓለም ገናና ስም ያላቸው ሰንዳንስ እና ትሩ/ፎልስ ፌስቲቫሎችን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ታይቷል። ተደንቋል። ተወዷል።
የፊልም ሀያሲዎች እና ፊልም ሠሪዎችን ጨምሮ የፊልሙን ማኅበረሰብ እያነጋገረ ይገኛል።
በየዓመቱ ስዊዘርላንድ ውስጥ የሚዘጋጀው ታዋቂው 'ቪዥን ዱ ሪል' የዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ፈያ ዳኢ ተሸልሟል። በፉል ፍሬም እና ሆትዶክስ ፌስቲቫሎችም እንዲሁ።
ዘ ኢኮኖሚስት፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ቮግ፣ ቫራይቲ እንዲሁም ሌሎችም መገናኛ ብዙኃን ስለ ፊልሙ ዳሰሳ አስነብበዋል። በዓመቱ መታየት ካለባቸው ፊልሞች ዝርዝር ውስጥም ፈያ ዳኢን አካተውታል።

ፈያ ዳኢ ስለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ያወራል ማለት ንፉግነት ነው።
ሱስ፣ ስደት፣ ንግድ፣ ልጅነት፣ መንፈሳዊነት፣ ፍቅር፣ ተፈጥሮ፣ የፖለቲካ እስር፣ ሴትነት፣ የነጻነት ትግል፣ ሞት፣ ወጣትነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቸኝነት፣ ህልም፣ ቤተሰብ፣ ማንነት. . .
በፊልሙ የሚነሳው እያንዳንዱ ነገር ከብዙ አቅጣጫ ይታያል። ፊልሙ እውነተኛ ሕይወታቸውን የሚያስቃኘን የሐረር ሰዎች የየራሳቸው ዕይታ፣ የየራሳቸው ትግል እና ድልም አላቸው።
ፈያ ዳኢ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው። የተለመደው አይነት የአተራረክ ወጥነት የለውም። ከሀ ተነስቶ ወደ ፐ ደረሰ የሚያስብል ፍሰት አለመኖሩ የሕይወትን ቅርጽ አልባነት ያሳብቃል።
በፊልሙ የምናያቸው ሰዎች ልሙጥ አይደሉም። ዥንጉርጉር ስሜታቸው ጎልቶ ይታያል።
ሁነቶቹ ዘለግ ላሉ ሰከንዶች ስክሪኑ ላይ ስለሚቆዩ ትኩረት አለመስጠት አይቻልም። ለምሳሌ የመሐመድ እንባ ለ60 ሰከንዶች ኮለል ብሎ ሲወርድ መመልከት ስሜትን ያናውጣል።
በፊልሙ የሚነገሩት ቋንቋዎች ሐረሪ፣ አፋን ኦሮሞ እና አማርኛ ናቸው። ልክ እንደ ሐረር።
ጀሲካ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገችው 'ፈያ ዳኢ' በአሜሪካ ሲኒማ ቤቶች መታየት በጀመረበት ቀን ነው።
ጀሲካ ነገሮችን በጥልቀት የምትመረምር፣ በጥልቀት የምትገልጽም ፊልም ሠሪ ናት። ለማዋራት የማትከብድ፣ ተጫዋች እና ግልጽም ነች።
የሐረር ሰው ቅለት፣ የኒው ዮርክ ሰው ፍጥነት፣ የሜክሲኮ ሰው ተግባቢነት አላት።
"ፈያ ዳኢን የሠራሁት ለእኛ ነው" ትላለች። 'እኛ' የምትለው ጥቁር እና ቡናማ ሕዝቦችን ነው።
"ፊልሙን የሠራሁት ለእኛ ነው። ለእኛ በእኛ ነው የተሠራው። እያወራሁ ያለሁት ከእኛ ጋር ነው። እንድንነጋገር ነው የምፈልገው። ፊልሙ የተሠራው ለፈረንጆች ሳይሆን ለእኛው ነው።"


የፎቶው ባለመብት, Janus Films
ጫት - በ'በረከት' እና እርግማን መካከል
አዙኸርላይኒ የተባሉ የሱፊ ኢማም ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጥ ውሃ (ማኡል ሀየት) ለማግኘት ፍለጋ ላይ ሳሉ አላህ ጫት እንደሰጣቸው በአፈ ታሪክ ይነገራል።
በሐረር ጫት የኑሮ መሠረት ነው። ሕይወት የሚሽከረከረው በጫት ዙርያ ነው። የሚያስከትለው ግላዊ እና ማኅበራዊ ቀውስም አይካድም።
ፈያ ዳኢ ጫት ቤተሰብ ሲያስተዳድር፣ ቤተሰብ ሲበትንም ያሳያል። ጫት ከሌለ የበርካቶች የእንጀራ ገመድ ይበጠሳል። ጫት በመኖሩ የበርካቶች ሕይወትም ተመሰቃቅሏል።
የመሐመድ አባት በጫት ምርቃና፣ ጫት ባላገኘ ቀን ደግሞ በዱካክ ይንገላታል። ልጁን ይደበድባል።
ባሏ በጫት ፍቅር ወድቆ እሷን የዘነጋት ሴት በሐዘን ተውጣለች። በሌላ ጎን የመሐመድ እኩዮች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ የግድ ጫት መሸከም፣ ማከፋፈል አለባቸው።
የጫት ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብት እና የባህል ውስብስብ ገጽታዎች በፊልሙ ይታያሉ።
ጀሲካ ልጅ ሳለች በሐረር ቡና፣ ጤፍ፣ ማሽላ እና ሌሎችም ሰብሎች ይተከሉ ነበር። አሁን ግን ምድሩን የሞላው አረንጓዴ የጫት እርሻ ነው።
"ሐረር ላደገ ሰው ከድሮውም ጫት መትከል አዲስ ነገር አይደለም። አሁን ግን ሙሉ በሙሉ የሚበቅለው ጫት ነው። ለምን የጫት እርሻ ሰፋ? ብዬ የምጠይቀው አርሶ አደሩን ነው" ትላለች።
አርሶ አደሩ "የዋጋ ንረት ሕይወትን ከባድ አድርጎታል። ቡና እያበቀልን ልንኖር አንችልም" ሲል ይመልሳል።
አርሶ አደሩ የሚከተለው የገበያውን ፍላጎት እና ሕይወቱን እንዲገፋ የሚያስችለውን መንገድ ነው።
ወጣቱም "ሥራ የለም፤ ታድያ እንሙት እንዴ!?" ይላል።
በሐረር ቡና በቅሎ በፍቅር ይጠጣ ከነበረበት ዘመን፤ 'መሄጃ ስለሌለኝ ጫት ልቃም' ወደሚል ትውልድ የተፈጠረውን ሽግግር ነው ጀሲካ የምታሳየው።
ሁሉንም የማኅበረሰቡን ድምጾች አንድ ላይ ማምጣት እፈልጋለሁ ትላለች።
አርሶ አደሩ ስለ አባቶቹ፣ እናቶቹ ዘመን ቡና ያስታውሳል። አሁን ግን የአየር ሁኔታው አልጨበጥ ብሎታል።
የሚፈልገው እና የሚያገኘው ዝናብ የሰማይ እና የምድር ርቀት አለው። ሐሮማያ እና ሌሎችም ሐይቆች ደርቀው ስለነበረ ውሃ የሚገኘው ጉድጓድ ተቆፍሮ ነው።

"ኀጢአት ስለበዛ አላህ ሐሮማያን አደረቀው"
ኀጢአት ስለበዛ አላህ ሀሮማያን አደረቀው የሚል አፈ ታሪክ ፊልሙ ላይ ይሰማል።
ድሮ ድሮ እነ ጀሲካ ለልደትም ለሠርግም ሐሮማያ ይሄዱ ነበር። የሐረር ልጅ የሆነ ሁሉ የሚያውቀው ዓሣ ቤት ይዘወተራል። የጀልባው፣ የዓሣ አጥማጁ ግርግር የጀሲካ የልጅነት ትውስታ ነው።
ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ሐረር ስትመለስ ሚኒባሱን እስኪ ሐይቁ ጋር ጣለኝ አለችው።
"እኔማ ሐይቁን አይቼ፣ ሰላም ብዬው ላልፍ ነበር። ውሃው ጠፍቶ በሬ ሳር ሲግጥ ሳይ እንዴት ክው እንዳልኩ። 'ሐይቁ የታለ? የት ሄደ?' አልኩኝ። ይህንን ማየት በጣም ያማል። ሐሮማያም፣ አደሌም፣ ሌላውም ሐይቅ እየደረቀ ነው።"


የፎቶው ባለመብት, Janus Films
ሕዝባዊ ተቃውሞ እና ወጣቱ
ፀጉራቸውን ያጎፈሩ፣ ባለ አፍሮ ወጣቶች ማሳ ውስጥ ተሰብስበው እንዲህ ያወጋሉ።
"የምንሞተው በመሬታችን፣ የምንሰደደው ከመሬታችን ነው። ይህ ሁሉ ኦሮሞ ስለሆንን ነው። ትግላችን አዲስ አይደለም። አያት ቅድመ አያቶቻችን አልፈውበታል። ትምህርት ማቋረጥ፣ መታሰር፣ መደብደብ እና መሰቃየት ለሕዝባችን የምንከፍለው ዋጋ ነው። መስዋዕትነታችን ተገቢ ነው። አናዝንም። ይህ የነጻነት ጭላንጭል ለእኛ በቂ አይደለም። ትግላችን ይቀጥላል. . ."
ጀሲካ ፊልሙን በቀረጸችባቸው 10 ዓመታት የኢትዮጵያ ፓለቲካ እና ማኅበራዊ እውነታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀያይሯል።
ሕዝቡ ለዘመናት መሬቱን እንደተቀማ፣ መብቱን በመጠየቁ እንደታሰረ፣ እንደተገደለ፣ ድምጹ እንደታፈነ እና እንደተሰደደም እሮሮውን አሰምቷል።
ኢፍትሐዊነትን በማውገዝ በዋነኛነት በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ በአገሪቱ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ብዙዎች "የለውጥ እና የሽግግር ዘመን" ወዳሉት አምርቷል።
አሁን ደግሞ አገሪቱ በጦርነት እየተናጠች፣ ማኅበራዊ ቀውስ እና የምጣኔ ሀብት መላሸቅም ገጥሟት እየተንገዳገደች ትገኛለች።
ይህ የኢትዮጵያ እሽክርክሪት ጀሲካ ላይ እንደ ሰውም እንደ ፊልም ሠሪም ተጽዕኖ አሳድሯል።
"2008 አካባቢ ሰላማዊው ተቃውሞ ሲነሳ እርሻ ውስጥ ነበርኩ። ተቃውሞውን የተቀላቀሉት የአርሶ አደሮቹ ልጆች ነበሩ። አንዳንዶቹ ተገድለዋል። ትምህርት አቋርጠው ማሳ ውስጥ ለመደበቅ የመጡት ብዙ ናቸው። ሐሮማያ ዩኒቨርስቲ የነበሩ በርካቶች ሞተዋል። ያልተመረቁት ብዙ ናቸው። ፖለቲካዊ ጭቆናውን እና ተማሪዎች የደረሰባቸውን እያየነው ነበር። የእውነት እየሆነ ያለውን እያዩ ፊልም መቅረጽ መቀጠል ከባድ ነበር።"
ያ ወቅት ለጀሲካ ፈታኝ ነበር። የፀጥታ ኃይሎች የፊልሙን ቀረጻ አስቁመዋትም ያውቃሉ።
ሰዎች ካሜራ ፊት መናገር ይፈሩ እንደነበር ታስታውሳለች። ጋዜጠኞች ወጣቶችን ካነጋገሯቸው በኋላ ሐሳባቸው በመገናኛ ብዙኃን ተጠምዝዞ ሲቀርብ ያዩ ነበር።
እኚያ ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን ዋጋ ከግምት በማስገባት "የሰዎችን ታሪክ ወደ ካሜራ ከማምጣቴ በፊት ልሰማቸው እና ልረዳቸው እየሞከርኩ ነበር" ስትል ትገልጸዋለች።
ፊልሙ የወጣቱን ቁጣ ያስተጋባል። ጓደኞቻቸውን ማጣታቸው ሰብሯቸዋል። አገሪቱ "ሽግግር ላይ ናት" ቢባሉም ከዚያ ሁሉ መስዋዕትነት በኋላ ድምጻቸው እንደተሰማ አያምኑም። ተስፋ ግን አልቆረጡም።
የጀሲካ ቤተሰብ ከኢትዮጵያ የተሰደደው ጦርነት ሸሽቶ እንደመሆኑ አሁን ላይ በአገሯ ዳግመኛ ጦርነት ማየት ይረብሻታል።
"ጦርነትን ኖረነዋል። ብዙ አሳጥቶናል። መልሰን ጦርነት ስናይ እጅግ ልብ ይሰብራል።"

ጥቁር እና ነጭ- ስደት
ፈያ ዳኢ ጥቁር እና ነጭ ፊልም ነው። ቀለሙ የመሐመድን ፍርሀት ይወክላል ትላለች ፊልም ሠሪዋ።
እናቱ ሳዑዲ አረቢያ የሄደችበት መሐመድ እናቴ ትረሳኛለች ብሎ ይፈራል። ብዙ ደብዳቤ ቢጽፍላትም ምላሽ እያገኘ አልነበረም። ስደት የተባለ ክፉ ደንቃራ እናት እና ልጅ መሀል ተሰንቅሯል።
መሐመድ የእናቱን ዱካ ተከትሎ መሰደድ ይፈልጋል። ብዙ የሐረር ልጆችም ለስደት አኮብኩበዋል።
"እኔም እናት ስለሆንኩ የእኛ ልጆች በዚያ እድሜያቸው አገር ትተው ለመውጣት ሲወስኑ ማየት ያማል። እንደ መሐመድ ያሉ ወጣቶች እያለፉበት ያለውን ችግር ማሳየት ነው የምፈልገው" ትላለች ጀሲካ።
ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ልጆችን 'በነጻ ሳዑዲ እንውሰዳችሁ' ብለው እያታለሉ የሰውነት ክፍላቸውን ይሰርቃሉ። ግለሰቦቹ በፖሊስ ቢያዙም ጉቦ ሰጥተው እንደሚለቀቁ ትናገራለች።
ፊልሙን ስትሠራ ወደ ስደት የሚወሰዱ ልጆች ማቆያ የነበረ ቤት በፖሊስ ተገኝቶ ነበር።
ስደት የሚያላላውን ማኅበራዊ ትስስር እሷም በሕይወቷ አይታዋለች። እሷ ወደ ኢትዮጵያ ብትመለስም አባቷ ግን በስደት ብዙ ቆይተዋል።
"አባቶቻችን ሌላ አገር ተሰደው ሲሄዱ ብዙ ህመም አለ። ግን አያወሩትም። ለዓመታት በሕይወትሽ ዝምታ ይፈጠራል። ሕይወት ባለሽበት ያስርሻል። ልጆች ማሳደግ አለብሽ። የተሰደድሽበትን አገር ባህል መልመድ ይጠበቅብሻል። እናም ህመሙ ለቤተሰቦቻችን ከባድ ነው።"
ቤተሰቧ የምትወዳትን ሐረር ጥሎ የወጣው 'በ24 ሰዓት ውስጥ ትሄዳላችሁ' ተብሎ እንደሆነ ታስታውሳለች። ድንገት ሐረርን ለቆ መሰደድ "ልቤ ውስጥ ክፍተት ትቶ አልፏል" ስትልም ትገልጻለች።

የ 'ራሽያ ጊቢ' ፊልሞች
የጀሲካ አባት ሜክሲኮ በቀዶ ጥገና ሐኪምነት እየሠሩ ሳለ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ተነሳ።
ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ተደውሎ "ውጪ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ ኑ! እየተወረርን ነው!" ተባሉ። ሳይውሉ ሳያድሩ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ያኔ ጀሲካ ሁለት ዓመቷ ነበር።
አባቷ የተጎዱ ወታደሮች እያከሙ ኢትዮጵያ ቆዩ። አገር ጥለው እስኪሰደዱ ድረስ።
በሐረር ካቶሊክ ትምህርት ቤት ስትማር ትዝ የሚላት የሶማሌው፣ የአደሬው፣ የአማራው እና የኦሮሞው አብሮነት ነው።
"ደስ የሚል ልጅነት ነው። ጦርነት ውስጥ ማደግ በጣም ከባድ ነው። ግን ደግሞ በጦርነት ውስጥም ልጅ መሆን ይቻላል። ጓደኞቼን ደስ እያለኝ አስታውሳቸዋለሁ።"
በጦርነቱ ጊዜ ራሽያ ጊቢ እና ኩባ ጊቢ የሚባሉ ቦታዎች ነበሩ። ወታደሮችን ለማበረታታት ማታ ማታ ሜዳ ላይ ፊልም ይከፈታል።
የሰፈሩ ልጆች ወደ ራሽያ ጊቢ ለመሄድ የሚያልፉት በእነ ጀሲካ ቤት በኩል ነበር። ተጠራርተው ራሽያ ጊቢ ይሰበሰባሉ። ከዚያማ ዛፍ ሥር ቁጭ ብለው የሩስያ እና የጀርመን የጦርነት ፊልም ይኮመኩማሉ።
"ያ ዘመን ፊልም ሠሪ እንድሆን አድርጎኝ ከሆነ አላውቅም። ግን የሆነ ነገር ውስጤ ገብቷል። ያኔ ፊልሞቹን ሳይ ፊልሞቹን የሚሠሩ ሰዎች አሉ ብዬ እያሰብኩ አልነበረም። የእውነት እንደሆነ ነበር የማስበው።"

የፎቶው ባለመብት, Raphael Segal
ለሐረር ልጆች የተጻፈ የፍቅር ደብዳቤ
ፈያ ዳኢን የሠራሁት ከሐረር ልጆች እና ወጣቶች ጋር ነው ትላለች። ካሜራዋን፣ ትራይፖዷን. . . ይዘው ከጠዋት እስከ ማታ አብረዋት ይዞሩ ነበር። ከተዋወቀቻቸው ልጆች አንዱ ደግሞ መሐመድ ነው።
ፊልሙን ለሐረር ልጆች የተጻፈ የፍቅር ደብዳቤ ማለት ይቻላል። በፊልሙ ምን ለማለት ነው የፈለግሽው? ብለን የጠየቅናት ጀሲካ እንዲህ መልሳለች።
"ማለት የምፈልገውማ. . . ወጣቶች አይቼአችኋለሁ። እወዳችኋለሁ። ጀግና ናችሁ። ስሜታችሁን እረዳዋለሁ። ድንቅ ፍጥረቶች ናችሁ። በፈታኝ ነገር እያለፋችሁ መሆኑ ያሳዝነኛል። አይዟችሁ። አይዞህ የኔ ወንድም! አይዞህ የኔ ልጅ! ማለት ነው።"

"ኢማሞቹ በቫይበር እየደወሉ 'ፊልሙ ተመረቀ?' ይሉኛል"
ፊልሙ በአሜሪካ እና በተለያዩ ፌስቲቫሎች እየታየ ቢገኝም ገና ለኢትዮጵያ ተመልካቾች አልቀረበም።
በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ፊልሙን አገር ቤት ማሳየት ከባድ ቢሆንም፤ ትልቁ የጀሲካ ሕልም ፈያ ዳኢን ቀደምቱ የሐረር ሲኒማ ቤት ማሳየት እንደሆነ ትናገራለች።
ይሄ ሲኒማ ቤት ፊልሟ ላይም ይታያል። ሲኒማ ቤቱ ልጅ ሳለች የቦሊውድ ፊልም የሚታይበት ነበር። "ምን እንደሚሉ ባናውቅም በሕንድኛ ሲዘፈን አብረው የምንዘፍንበት ዘመን" ትለዋለች።
ፊልሙን ለመቅረጽ ሐረርን ስታዳርስ ያልተዋቀችው ሰው የለም። ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከኢማም እስከ ነጋዴ።
ያኔ ባለፈች ባገደመች ቁጥር "ጀሲካ ይሄ ነገር አላለቀም እንዴ? አቦ አሁንም ተመልሰሽ መጣሽ?" የሚሏት ኢሟሞች ዛሬ ከሐረር ወደ ኒው ዮርክ በቫይበር ይደውሉላታል። ስልኩን እየተቀባበሉ በሞቅታ ያዋሯታል።
"ፊልሙ ተመረቀ?"
"በቃ ዱአ እናድጋለን!"
"ስሙ፤ ፌስቲቫል ይሄዳል ብላለች!"
እነዚህ ኢማሞች ስክነትን፣ እርጋታን አስተምረውኛል ትላለች።
"እዚያ ኒው ዮርክ 'ጊዜ የለኝም። እሄዳለሁ' የምትይውን ተይው። እዚህ መራወጥ ምናምን አይሠራም። ረጋ በይ። አሁን ላይ ሁኚ ይሉኛል። እውነታቸውን ነው" ስትል ትገልጻለች።
የኢማሞቹ ስክነት እሷም ተጋብቶባት ፊልሙ ላይ ተንጸባርቋል። ድርጊቶች የሚከናወኑበት እርጋታ በተወሰነ መጠን የፊልሙ ተመልካች ላይም ይጋባል።

"መሐመድ ከፍታዬ ነው"
በፊልም ሥራው ካገኘችው ነገር ባጠቃላይ ትልቁ ከፍታዬ የምትለው መሐመድን ነው። ወደ 12 ዓመቱ አካባቢ ሳለ ነበር የተዋወቁት። ፊልሙም ሕይወቱን ያሳያል።
ጠዋት ለቀረጻ አንደኛ የሚገኘው፣ ማታ ከሰው ሁሉ መጨረሻ የሚሄደው እሱ ነበር።
ሐረር እየተመላለሰች ፊልሙን ስትቀርጽ ልጇን ኒው ዮርክ ትታ ነው። መሐመድ ደግሞ እናቱ ሳዑዲ ሄዳበታለች።
"እናቱ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። እሱም እኔ ውስጥ እናት እየፈለገ ነበር። በፊልሙ ሥራ ያገኘኋቸው ሰዎች ባጠቃለይ ያስተማሩኝ ነገር አለ። ትምህርቱን አከብረዋለሁ። ትምህርቱን በማክበር ውስጥ አያት ቅድመ አያቶቼን አከብራቸዋለሁ።"
ፊልሙን መሥራት የጀመረቸው አያቷን ስትቀርጽ አልነበር? ታዲያ በ10 ዓመታት ውስጥ ታሪካቸውን የመዘገበቻቸው ሰዎች ውስጥ አያቷን ትመለከት ነበር። ቅድመ አያቶቿን፣ ምንጅላቶቿን እና የማንነቷን ትርጉምም አግኝታባቸዋለች።

ፈያ ዳኢ. . .
ፈያ ዳኢ ቃል በቃል ትርጉሙ 'ጤና ውለዱ' ማለት ነው። 'በጎ ነገር ይውጣላችሁ' እንደ ማለት።
ጀሲካ ይህንን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችው እርሻ ውስጥ ቁጭ ብላ ነው።
አርሶ አደሮች ጉልበትን በእጅጉ የሚፈታተን ሥራ ሲሠሩ፤ ከመካከላቸው አንዱ በዜማ ሲገጥም የተቀሩት 'ፈያ ዳኢ' እያሉ ይቀበሉታል።
"ፈያ ዳኢ ሲሉ ስሰማ ስሜቴ ተነካ። ደግሞ እኮ ኦሮምኛ አልችልም። ቋንቋውን ባላውቅም ቃሉ ልዩ እንደሆነ ተሰማኝ። አይዞን፣ በርታ! ማለት ነው ሲሉኝ አልቅሻለሁ።"
አርሶ አደሮቹ ፈያያያ ዳኢ እያሉ በዜማ ሲሠሩ ሥራው በዘፈኑ ቅርጽ ይይዛል። ዜማው ጉልበት ይሰጣቸዋል።
ለ10 ዓመታት ፊልሙን የቀረጸችው ባጠራቀመችው የግል ገንዘቧ ነው። ከኢትዮጵያም ከአሜሪካም የሚረዷት ብዙም ፊልም ሠሪዎች አልነበሩም።
"10 ዓመት ረግቶ ለመሥራት፤ ማንም ባያምንብሽም በራስሽ መተማመን አለብሽ። በሕይወቴ ሁሉን ነገር ትቼ ፊልሙ ላይ ብቻ ማተኮር ነበረብኝ። ሁሌ ብርቱ ሰው መሆን አይቻልም። መድከም፣ መውደቅም አለ። ስወድቅ አንዱ መነሻ መንገዴ ፈያ ዳኢን መስማት ነበር።"
ኃይሌ ገሪማ 'ጤዛ'ን ለመሥራት 15 ዓመታት ገደማ ወስዶባቸዋል። ጀሲካ ፈያ ዳኢን ለመሥራት ድፍን አሥር ዓመት ወስዶባታል። እንዴት ነው ነገሩ? ሰዎች የሚወዱትን ሲሠሩ ዓመታት ቅጽበት ይሆንላቸዋል ማለት ነው? ወይስ ሌላ የማናውቀው ምስጢር አለ?
ብቻ ፈያ ዳኢ የሚለው ዝማሬ ለአርሶ አደሮቹ ብቻ ሳይሆን ለጀሲካም አቅም ሰጥቷታል። 10 ዓመት በቀረጻ አዝልቋታል። የፊልሙ ርዕስ ያደረገችውም አባባሉን ለማሞገስ ነው።
ፊልሟንም የምትገልጸውም እንዲህ ነው. . .
"በሕይወቴ እጅግ ውብ የሆነው ነገር ይህ ፊልም ነው። ከምወደው አገር እና ትቼው ከሄድኩት መሬት ጋር በድጋሚ የተሳሰርኩት በፈያ ዳኢ ነው. . ."

የፎቶው ባለመብት, Janus Films












