ሩሲያ እና ዩክሬን: ፑቲን የኒውክሌር ቁልፉን ይጫኑት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የኒውክሌር ቁልፉን ይጫኑት ይሆን? የሚለው ጥያቄ እና ስጋት በርካቶችን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።
በሞስኮ የሚገኘው የቢቢሲው ስቲቭ ሮሰንበርግ ከዚህ ቀደም ፑቲን አያደርጉትም የተባለን ነገር ሲፈጽሙት አይተናል ይላል።
ፑቲን ክሪሚያን በጭራሽ አይነኩም ሲባል ክሪሚያን በሩሲያ ቁጥጥር ስር አደረጉ።
ዶንባስ ውስጥ ጦርነት አይጀምርም ብለው በርካቶች ሲከራከሩ፤ ፑቲን ግን ጦርነቱን አስጀምረው በተግባር አሳዩ።
አሁን ዩክሬንንማ ዓይናችን እያየ አይነኩም ሲሉ ለነበሩ የምዕራቡ ዓለም አገራት፤ ፑቲን 'እስቲ ምን ትሆኑ' በሚመስል መልኩ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ አውጀዋል።
'ይህማ አይሆንም' የሚባል ነገር ፑቲን ጋር እንደማይሰራ ደምድሚያለሁ ይላል ስቲቭ ሮዝንበርግ።
የፑቲን ድፍረት የተሞላባቸው ውሳኔዎችን ለተመለከተ ሰው ፑቲን የኒውክሌር ቁልፉን አይጫኑትም ብሎ ለመገመት ከባድ ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ነገር አይደለም።
የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ "ተገቢ ያልሆነ" እርምጃ እና "ሕገ ወጥ'' ማዕቀብ እየጣሉ ነው በማለት የአገራቸው ሠራዊት የኑክሌር ኃይል 'በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ' እንዲቆም አዘዋል።
ባለፈው ሐሙስ ፑቲን ጦራቸውን ወደ ዩክሬን 'ልዩ ለሆነ ተልዕኮ' ለምን እንደሚልኩ ሲያብራሩ በመሀል አንድ አስፈሪ ነገር ተናግረዋል።
ፑቲን በንግግራቸው የትኛውም አገር የሩሲያን እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚሞክር ከሆነ በታሪካቸው አይተውት የማያውቁት የአጸፋ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው ተናግረው ነበር።
በርካቶችም ይህንን ንግግር የኒውክሌር መሳሪያን ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር ለማገናኘት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም።
የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው እና የኖቫያ ጋዜጣ ዋና አርታኢ ዲሚትሪ ሙራቶቭ በዚህ ሀሳብ ይስማማል።
"ፑቲን በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ሲናገሩ የክሬምሊን መሪ ሳይሆነ የምድራችን ገዢ እንደሆነ ነበር ሁኔታው። ልክ በጣም ቅንጡ መኪና የገዛ ሰው ለሰዎች ለማሳየት ቁልፉን ይዞ በእጆቹ እንደሚያደርገው አይነት ነበር ማስፈራሪያው። ሩሲያ ከሌለች ምድር ለምን ታስፈልጋለች? ይህን በተደጋጋሚ ብሎታል ማንም ግን ትኩረት አልሰጠውም" በማለት ስጋቱን ገልጿል።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ በተሰራ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ላይ ፑቲን እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር። ". . . አንድ ሰው ሩሲያን አላፈናፍን ካለ ምላሽ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ አለብን። አዎ ይህ (ምላሽ) ምናልባት ለሰው ልጅ እና ለዓለም ከፍተኛ ጥፋት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እኔ የሩሲያ ዜጋ እና ርዕሰ ብሔር ነኝ። ሩሲያ የሌለችበት ዓለም ምን ያደርግልናል።''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሁን 2022 ላይ እንገኛለን። ፑቲን ዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ አካሂደዋል።
የዩክሬን ወታደሮች ድንበራቸውን ላለማስደፈር የሞት የሸረት ትግል በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ ፑቲን ቀድመው ያሰቡት ነገር በቶሎ እንዳያሳኩ እንቅፋት የሆነ ይመስላል። በሌላ በኩል የምዕራቡ ዓለም አገራት በመተባበር ሩሲያ ላይ ጠንከር ያሉ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
እነዚህ ማዕቀቦች ደግሞ የሩሲያን ምጣኔ ሃብት እንደሚያንኮታኩቱትና የአገሬው ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ እንዲነሱ የሚያደርግ እንደሆነ ታምኖበታል።
ምናልባት እነዚህ ውሳኔዎች ፑቲን የሁላችን ስጋት የሆነውን ኒውክሌር ስለመጠቀም ያሳስቡ ይሆን? አሁን ላይ በእርግጠኝነት መናገር ከባድ ነው።
"ፑቲን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል" ይላል መቀመጫው ሞስኮ ያደረገው ወታደራዊ ተንታኙ ፓቬል ፌልገንሃውር።
"አሁን ላይ ብዙ አማራጮች የሉትም። ሁሉም የሩሲያ ባንኮች ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴያቸው ሲቆም ሥርዓቱ ይቆማል'' ይላል።
አክሎም "ሌላኛው አማራጭ ለአውሮፓ የሚያቀርበውን ጋዝ ማቆም ነው። ምናልባት አውሮፓውያን የሚደነግጡ ከሆነ። በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜናዊ ባሕር ብሪታኒያ እና ዴንማርክ መካከል የኒውክሌር ቦንብ አፈንድቶ ቀጥሎ የሚሆነውን ማየት ነው።"
ፑቲን እውነትም የኒውክሌር ቁልፉን ለመጫን የሚወስኑ ከሆነ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሀሳቡን ለማስቀየር ይሞክሩ ይሆን? ወይስ ለፑቲን ድጋፍ ይሰጣሉ?
"የሩሲያፖለቲከኞች በታሪካቸው አንድም ጊዜ ከሕዝቡ ጎን ቆመው አያውቁም። ሁሌም ቢሆን ከመሪው ጎን ናቸው'' ይላል የኖቤል አሸናፊው ዲሜትሪ ሙራቶቭ።
ፑቲን በሩሲያ እጅግ ጉልበተኛው ፈላጭ ቆራጭ ናቸው። አገሪቱ ውስጥ የትልልቅ ፖለቲከኞች ተጠያቂነት እምዛም የተለመደ አይደለም።
ክሬምሊን ሁሉንም ውሳኔ ይወስናል፤ ሕዝቡ ደግሞ ይከተላል።
"አሁን ላይ ፑቲንን የሚገዳደረው አንድም ሰው የለም። በጣም አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው" የሚለው ደግሞ ፓቬል ፈልገንሃውር ነው።
ክሬምሊን ይህንን ወረራ ካሳካና ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ፣ ዩክሬን እንደ ሉአላዊ አገር የመቀጠሏ ነገር አጠራጣሪ ይሆናል።
ምናልባት ደግሞ ሩሲያ ያላሰበችው ሽንፈት ቢገጥማት ፑቲን የመጨረሻ አማራጭ አድርገው የሚወስዱት እርምጃ የዓለምን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን ይችላል።












