ማዕቀቦችን ተከትሎ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር በ30 በመቶ ቀነሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራባውያኑ ሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀቦችን ተከትሎ የሩሲያው መገበያያ ገንዘብ ሩብል ከአሜሪካ ዶላር አንጻር 30 በመቶ ዋጋው መቀነሱ ተገለጸ።
የምዕራቡ ዓለም አገራት አንዳንድ የሩሲያ ባንኮች ስዊፍት የተሰኘውን ዓለማ አቀፍ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ስርዓት እንዳይጠቀሙ ማገዳቸውን ተከትሎ ነው የሩሲያው ሩብል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ደረጃ ዋጋው የወረደው።
እሁድ ዕለት የሩሲያው ማዕከላዊ ባንክ ከዚህም በኋላ የአገሪቱ ባንኮች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል በመጠቆም ዜጎች እንዲረጋጉ አሳስቧል።
የዩክሬን ቀውስን ተከትሎ ያልተጣራ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋው ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል።
የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ እንዲሁም አጋሮቻቸው በርካታ የሚባሉ የሩሲያ ባንኮችን ከስዊፍት ያገዱ ሲሆን ይህ እርምጃ ከዩክሬን ወረራ በኋላ እስከዛሬ ከታዩ ማዕቀቦች ከባዱ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ እገዳ የሚጣልበት ሲሆን ይህ ደግሞ አገሪቱ በሌሎች አገራት ያላትን ንብረት ማንቀሳቀስ እንዳትችል ያደርጋታል።
ይህ እርምጃ ሩሲያን ከተቀረው ዓለም የንግድና ገንዘብ ነክ እንቅስቃሴዎች ማግለል እንደሆነ ምዕራባውያን አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ሩሲያ የነዳጅና የጋዝ ምርቶቿን የምትሸጠውና ሌሎች አገልግሎቶችን የምታገኘው በዚሁ ስዊፍት በተሰኘው የገንዘብ ማዘዋወሪያ ስርዓት በኩል ነው።
"ከተቀረው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው የተደረጉት የሩሲያ ግዙፉ ባንክ እና ማዕከላዊው ባንክ ተጨማሪ የገንዘብ ማንቀሳቀሻ አማራጭ ካላገኙ በቀር ሩሲያ ልክ እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ከዓለም ኢኮኖሚ የተገለለች ትሆናለች'' ሲል የዘርፉ ባለሙያ የሆነው አሪ ሬድቦርድ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከቀናት በፊት በዩክሬን ላይ በተፈጸመው ወረራ ምክንያት ምዕራባውያን አገራት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ላይ የተለየ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረት፣ በዩናይትድ ኪንግደምና በካናዳ ያለ የሁለቱ የሩሲያ ከፍተኛ መሪዎች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ የተጋደ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ የጉዞ እገዳ ጥላባቸዋለች።
ምዕራባውያን በዩክሬን ላይ ለተፈጸመው ወረራና ከሚከተለው ደም መፋሰስ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ ፕሬዝዳንቱ ግን አገራቸው ይህንን እርምጃ የወሰደችው ምሥራቅ ዩክሬን ያሉ ሰለማዊ ሰዎችን ለመከላከል እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከአሜሪካ ተለይቶ ለጊዜው የጉዞ እገዳን በሩሲያ መሪዎች ላይ ከመጣል ተቆጥቧል።
አሁን ላይ ደግሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው ሠራዊት የኑክሌር ኃይል 'በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ' እንዲቆም አዘዋል።
ፕሬዝዳንቱ የአገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉን ጨምሮ ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት፤ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ "ተገቢ ያልሆነ" እርምጃ እና "ሕገ ወጥ ማዕቀብ" መጣላቸውን ተናግረዋል።












