ሩሲያ እና ዩክሬን: የዩክሬን ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የዩክሬን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለጊዜው ፍልሚያው ተጀምሯል፣ ማስመሰል ቆሟል፣ ዲፕሎማሲው ሞቷል። ዩክሬን በሩሲያ ተወራ ለህልውናዋ እየተዋጋች ነው።

ታዲያ ቀጥሎ ምን ይሆናል?

የሩሲያ ትልቁ ሽልማት ኪዬቭ ናት። የዩክሬን መዲና እና የፕሬዚዳንት ዜለንስኪ መናገሻ። ውጊያው እዚህች ከተማ ደጃፍ ደርሷል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ለምዕራቡ ያደላችውን የስላቭ ጎረቤታቸውን ተረክበው ወደ ሞስኮ ምህዋር ለማስገባት የመከላከያ አለቆቻቸው ያወጡትን ዕቅድ በር ዘግተው ሲያጤኑ ዋል አደር ብለዋል።

የወረራ ዕቅዱ ሦስት አቅጣጫን የተከተለ ነው። ከሰሜን፣ ከምስራቅ እና ከደቡብ የማጥቃት መስመርን ያቀፈ ነው። እግረኛ ወታደሮች እና ታንከኞች ከመግባታቸው በፊት መንገዱን እንዲቃናላቸው የመድፍ እና የሚሳኤል ጥቃቶች ይደረጋሉ።

ፑቲን የዜለንስኪ መንግሥት በፍጥነት ስልጣኑን አስረክቦ እና እጅ እንዲሰጥ ይፈልጋሉ። ቀጥሎ ደግሞ ለሞስኮ የሚወግን አሻንጉሊት መንግስት እንዲተካቸው።

ዓላማው ደግሞ በከተሞች የተራዘመ ብሄራዊ የተቃውሞ ዘመቻ እንዳይቀጣጠል ለመከላከል ነው።

የአለም አቀፍ የስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ብሪግ ቤን ባሪ "በአጭር ጊዜ ውስጥ ሩሲያ ተሳክቶላት ኪዬቭን መያዝ ከተቆጣጠረች ተፅዕኖ ያለው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ስኬት ነው" ይላሉ።

"ሆኖም የዩክሬንን መንግሥት ላያጠፋው ይችላል። ምከንያቱ ደግሞ አዲስ የመንግሥት መቀመጫ በሃገሪቱ ምዕራብ አቅጣጫ ለማቋቋም ዕቅድመውጣቱ ነው።"

የሩስያ የወረራ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ በዕቅዱ መሠረት አልሄደም። የብሪታንያ የመከላከያ ደህነነት እንዳለው በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩስያ ወታደሮች መገደላቸውን እና ጠንካራ ተቃውሞው ገጥሞታል። ሆኖም ግስጋሴው እንደቀጠለ ነው። የሩሲያ ጦር ከዩክሬን በቁጥር ይበልጣል። ብልጫው ሦስት ለአንድ ያህል ነው። የዩክሬን ወታደራዊ አመራር ጥራት እና ጦሩ ለምን ያህል ጊዜ እየተዋጋ ሊቆይ ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች አሉ።

መከላከል

መከላከሉ እየተቀጣጠለ ነው። ሃገር አቀፍ ጥሪም ቀርቧል። እድሜያቸው የደረሰ ሁሉ ትግሉን እንዲቀላለቀሉ ጥሪ ተደርጓል። 18 ሺህ አውቶማቲክ የጦር መሳሪያዎች ለኪዬቭ ነዋሪዎች ተከፋፍለዋል።

በዚህ ላይ ጦሩ እና ተጠባባቂው ኃይል ደግሞ ጠንካራ የመከላከል ሥራ እያከናወኑ ነው።

የፑቲን ዓይን ተከታይ አድርጎን ይሆናል ብለው የሚሰጉት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ከሩሲያ ጋር የሚያወስኗቸውን ድንበሮቻቸውን በፍርሃት እየተመለከቱ ነው። የኢስቶኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር ቋሚ ጸሐፊ የሆኑት ኩስቲ ሳልም ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ ዕርዳታ እንዲደረግ ከሚጠይቁት አንዱ ናቸው።

"እንደ ፀረ-ታንክ ሚሳኤሎች፣ ፀረ-አውሮፕላን፣ ጥይቶች እና መከላከያ ያሉ የጦር መሣሪያዎችን ልንሰጣቸው ይገባል። ሁሉም የኔቶ ማህበረሰብ ሊረዳቸው ይገባል" ብለዋል።

ሩሲያ ከ40 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ሃገር ለማስገበር ጊዜ በፈጀባት ቁጥር ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሟት ይችላል።

በሃገራቸው የሚካሄደውን ማንኛውንም ተቃዋሚ ያፈኑት ፕሬዚዳንት ፑቲን ጎረቤት ቤላሩስ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደውን ተቃውሞ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት እንዳፈነችው ልብ ብለዋል። ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ሰብስቦ ወደ እስር ቤት ይወረውራቸዋል። በርካቶች በእስር ቤት ከፍተኛ ድብደባና እንግልት ደርሶባቸዋል። ይህም ለተጨማሪ ተቃውሞ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

እንደ ብሪግ ባሪ ከሆነ "ሩሲያ ቻይና በሺንጂያንግ ከተጠቀመችበት የስለላ መሳሪያ የተሻሻለ ፣ እጅግ በጣም ከባድ ጭቆናን ትጠቀማለች። አማፅያን በሚረዱ መንግስታትን ለመበቀልም የሩሲያ ዛቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ።"

የሩስያ ተቃዋሚ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኔቶ የት ነው?

ኔቶ ሆን ብሎ ዩክሬን አይገኝም። ምዕራባውያን እንዲረዷቸው ከኪዬቭ ተማጽኖ ቢቀርብም ኔቶ ወታደሮቹን ወደ ዩክሬን ላለመላክ ወስኗል።

ለምን? ሲጀምር ዩክሬን የህብረቱ አባል አይደለችም። ሲቀጥል ኔቶ በግልጽ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አይፈልግም።

የሩሲያ ወረራ ለረዥም ጊዜ ከዘለቀ አሜሪካ በ1980ዎቹ የአፍጋኒስታን ሙጃሂዲንን እንደደገፈችው ሁሉ ምዕራባውያን መንግስታት የዩክሬንን አማፅያን በደንብ ሊደግፉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ፑቲን በተወሰነ መልኩ የበቀል እርምጃ ሊወስድ ስለሚችል ይህደግሞ ከስጋት ነጻ አይደለም።

እስከዚያው ድረስ ግን ኔቶ የምስራቃዊ ድንበሮቹን በማጥበቅ ላይ ትኩረት አድርጓል። አስገራሚው ነገር ኔቶ ኃይሉን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ እንዲያንቀሳቅስ ሞስኮ ብትጠይቅም የፑቲን የዩክሬን ወረራ ግን ተቃራኒውን ማሳካት መቻሉ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የመከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር ቶቢያስ ኢልዉድ "ይህ ለአውሮፓ ትልቅ የማንቂያ ደውል ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ የሦስት አስርት ዓመታት ሠላም የተለመደ አይደለም። ከአምባገነን ጋር ባለን ግንኙነት ዙሪያ እቅዳችንን ማሳደግ አለብን" ብለዋል።

ግጭቱ ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችላል?

ለዩክሬናውያን ይህ መጥፎው ደረጃ ነው።

በምስራቁ ሃገራቸው ክፍል በሩሲያ የሚደገፈውን ተገንጣይ ጦር ለስምንት ዓመታት ጦርነት ማካሄዱን ተከትሎ አሁን ደግሞ የኒውክሌር መሳሪያ የታጠቀችው ግዙፏ ጎረቤታቸው ሲደበደቡ እና ሲመቱ እያዩ ነው።

እአአ በ1991 ዩክሬን ከሞስኮ ነፃ እንድትሆን ድምጽ የሰጡ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነታቸውን የተዉ ዩክሬናውያን በድጋሚ በሩሲያ ጥላ ስር ከወደቁ ሦስት አስርት ዓመታት ወደኋላ የመመለስ ተስፋ ተጋርጦባቸዋል።

የዓለም መሪዎችን የሚያስጨንቀው ሰፊው ጥያቄ ፕሬዝደንት ፑቲን ከዩክሬን በኋላስ ምን ለመስራት አስበዋል? የሚለው ነው።

የኔቶ መከላከያ አዛዥ ከሰኔ፣ 2021 ረዥም ንግግራቸው ሲያጠቃልሉ ፑቲን እንደ ፖላንድ፣ ሊቱዌኒያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ ባሉ ሃገራት ላይ ዓይናቸውን እንዳይጥሉ ኔቶ ምስራቃዊ ድንበሮቹን በአስቸኳይ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

ፑቲንስ ይህን ያደርጉ ይሆን?

ቶቢያስ ኢልዉድ "ዕቅድ ያለው ይመስለኛል። 'አነስተኛ ጦርነት' የሆነ ችግር ለመቀስቀስ ዩኒፎርም ያልለበሱ ወታደሮችን መላክ ነው። ወደ ባልካን ሃገሮች እንዳይስፋፋ እሰጋለሁ" ብለዋል።

ኔቶ ከመዘጋጀት ውጭ ምንም እድል የለውም። ከ 100 በላይ የጦር አውሮፕላኖችን ዝግጁ አድርጎ አስቀምጧል። ብሪታንያ ተጨማሪ ሃይል ወደ ኢስቶኒያ ከላኩ የመጀመሪያዎቹ ሃገሮች አንዷ ነበረች። ኩስቲ ሳልም ምን ሊያገኙ እንደሚችሉ እርግጠኛ ናቸው።

"በዩናይትድ ኪንግደም የሚመራው ጦር [በኢስቶኒያ የሚገኘው] ብቻውን የዓለም ሁለተኛውን ኃያል የኒውክሌር ባለቤት ይከላከላል ብሎ የሚያስብ የለም "ሲሉ ተናግረዋል። "ይህ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ የሁሉንም ኔቶ ኃይል የሚቀሰቅስ ጉዳይ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የሩስያ ጦር ወደ ኔቶ አባል ሃገር የመግባቱ ጉዳይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የማይታሰብ ነበር። ይህ ከሆነ ኔቶ እና ሩሲያ እርስበርስ ጦር ሊማዘዙ የሚችሉበት ሁኔታ ነው።

ይህ እስካሁን አልሆነም። የምዕራባውያን መሪዎች በጋራ የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች በመጨመር ጠበቅ ያለ መልዕክት ለሞስኮ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ይደርሳል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ ።