ሩሲያ እና ዩክሬን: ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዴት ፈጠረች?

ማሊያውያነ የሩስያን ሰንደቅ አላማ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሩሲያ በቅርብ አመታት በአፍሪካ ተጽዕኖዋን እያሰፋች ነው። ከዩክሬን ወረራ በኋላ አዳዲሶቹ አጋሮቿ ድጋፍ እንዲሰጧት ወይም እንደተባበሩት መንግሥታት ባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቢያንስ ገለልተኛ ሆነው እንዲቆዩ ትጠብቃለች።

ከሊቢያ እስከ ማሊ፣ ሱዳን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሞዛምቢክ እና ሌሎችም ሃገራት ሩሲያ ይበልጥ እየተሳተፈች ነው። አብዛኛው ተሳትፎዋ ደግሞ በወታደራዊ ኃይል ሲሆን አማፂያንን ወይም የጂሃዲስት ታጣቂዎችን መዋጋትን ይጨምራል።

ኬንያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ባትሆንም ሩስያ በዩክሬን የወሰደችውን እርምጃ አስመልክቶ ተቃውሞዋን በግልፅ አሳይታለች።

ይህን የኬንያን አቋም የሚደግፉ ሌሎች ሃገራት ግን ብዙም አልታዩም። የአፍሪካ ህብረት ግጭቱ "እጅግ እንዳሳሰበው" ቢገልጽም በሩሲያ ላይ የሰነዘረው ትችት የለም።

በብሪክስ ቡድን ውስጥ የሩሲያ አጋር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ሃገሪቱ ጦሯን ከዩክሬን እንድታስወጣ ስትጠይቅ በድርድር መፍትሄ እንዳለም ጨምራ ገልጻለች።

ሩሲያ የዶኔስክ እና የሉሃንስክ ክልሎችን እንደ ገለልተኛ ሃገር ዕውቅና መስጠቷን እንደሚደግፉ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፋውስቲን-አርቻንግ ቱዋዴራ መናገራቸው ተዘግቧል።

ረቡዕ ደግሞ የሱዳኑ ምክትል መሪ መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ የልዑካን ቡድን እየመሩ ወደ ሞስኮ አቅንተዋል። ይህም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ያሳያል።

በአፍሪካ ያለው አጋርነት እየተቀየረ ስለመሆኑ ከሚያሳዩት ምሳሌዎች አንዱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ ከአንድ ሳምንት በፊት ፈረንሳይ በማሊ ጂሃዲስቶችን በመዋጋት ላይ የነበራት ተሳትፎ ማብቃቱ ነው።

የማሊው ጠቅላይ ሚኒስትር ቾጌል ማይጋ ከፍራንስ 24 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሃገራቸው ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነቶች መፈራረሟን አረጋግጠዋል። አወዛጋቢው የሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ ዋግነር ግሩፕ እጁ እንደሌለበትም ገልጸዋል።

ይህ ለማሊ የሚደረገው የሩስያ እርዳታ ለቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግሥት ከቀረበው ድጋፍ ጋር ተደምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ሩሲያ ይፋዊ እና መደበኛ ባልሆነ መልኩ በአፍሪካ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደግ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ያሳያል።

የታደሰው የሩስያ-አፍሪካ ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቶ እአአ በ2019 በደቡባዊ ሩሲያ ሶቺ ከተማ የተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከ50 በላይ የሃገራት ልዑካን ሲሳተፉ 43ቱ ርዕሳነ ብሔሮች ናቸው።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለመሪዎቹ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የነፃነት እንቅስቃሴዎችን የመደገፍ ታሪክን ለመጠበቅ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።

ሩሲያ ለበርካታ የአፍሪካ መንግሥታት ግልጽ ያልሆነ የፀጥታ ጥበቃ፣ በስልጠና፣ በስለላ፣ በመሳሪያ እንዲሁም የሩሲያ ቅጥረኞችን በአካባቢው ግጭቶች ውስጥ በማሳተፍም ትታወቃለች።

ፑቲን እንዳመለከቱት ታሪካዊ ግንኙነቱ ከሩሲያ በፊት ከነበረችው የሶቪየት ህብረት (ዩኤስኤስአር) ዘመን ድረስ የሚሄድ ሲሆን በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ካሉት በርካታ የውድድር ቦታዎች መካከል አንዷ አፍሪካ ነበረች።

እአአ በ 1991 የሶቭየት ህብረት ስትፈራርስ ጀምሮ እስካለፉት ጥቂት ዓመታት ድረስ ሩሲያ የሽግግር ጊዜ ውስጥ እያለፈች የነበረ ሲሆን ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነትም ዋነኛ አጀንዳ አልነበረም ።

በድጋሚ የልዕለ ኃያልነት ደረጃን እንደገና ማግኘት ለሩሲያ ፕሬዚዳንት የውጭ ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጡት ሆነ።

እአአ በ 2014 ሩሲያ የክሬሚያን ሰርጥ ወደ ግዛቷ መቀላቀሏን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ተበላሽቷል።

ከዓለም አቀፍ መገለል ስጋት ጋር በተያያዘ ሞስኮ አዳዲስ አጋሮችን መፈለግ ጀመረች።

በሩሲያ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ የአፍሪካ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ኢሪና አብራሞቫ "በእገዳው ምክንያት ሩሲያ ወደ ውጭ ለሚላከው ምርቷ አዲስ ገበያ መፈለግ አለባት" ብለዋል።

ሩሲያ የምትፈልገው ገበያ ብቻ አይደለም። እየጨመረ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ትፈልግ ነበር

እአአ በ 2014 በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተሳተፈችው ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድን ደግፋ ምዕራባውያን እያደረጉ ያሉትን ትርምስ ለማጉላት እና ሩሲያ እንዴት ማስተካከል እንደምትችል ለማሳየት ነው።

ቭላድሚር ፑቲን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሶሪያ በኋላ ደግሞ ወደ አፍሪካ አህጉር አቀናች።

በደቡብ አፍሪካ የኩዋዙሉ-ናታል ዩኒቨርሲቲ የክብር ፕሮፌሰር ኢሪና ፊላቶቫ እንደሚሉት ሩሲያ በአፍሪካ ውስጥ የነበራት ቁልፍ ተግባር እንደሶሪያ ሁሉ የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ማቃለል ነበር።

ለምሳሌ አውሮፓውያን በሳህል ያለውን የጂሃዲስት ስጋት መቆጣጠር እንዳልቻሉ ለማሳየት ፈልጋ ነበር።

ይህንንም በአፍሪካ ውስጥ ለማሳካት ሁለት ፖሊሲ ተጠቀመች። የመጀመሪያው በአንዳንድ ሃገራት ይፋዊ ወታደራዊ ስልጠናዎችን መስጠት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ መደበኛ ያልሆኑ እንደ ዋግነር ግሩፕ ያሉ ድርጅቶች ደግሞ በመዋጋት ጭምር እየተሳተፉ ነው።

በ2017 ከዋግነር ግሩፕ የሩስያ ቅጥረኛ ገዳይ ቡድን የታየባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ነበረች።

በኋላም እነሱን ተከትሎ ኦፊሴላዊ የሩሲያ ወታደራዊ አማካሪዎች ቡድን ገባ። ዓላማቸው ፕሬዝደንት ቱዋዴራን በስልጣን እንዲቆዩ መርዳት ነበር።

በቅጥረኞቹ የሚፈጸሙት የጭካኔ ወንጀሎች እየተለመደ መጣ። ሩሲያ ግን አንድም ዜጋዋ በጦር ወንጀሎች እና በሠላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ውስጥ እንዳልተሳተፉ በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የሩስያ ቅጥረኞች በሊቢያ፣ ሱዳን፣ ሞዛምቢክ እና ማሊ የተለያዩ በተለያዩ ደረጃዎችን ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

ሌላው የአህጉሪቱ ጠቀሜታ እያደገ መሄዱን የሚያመለክተው አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪ ዋና ገበያ መሆኗ ነው። ወደ አፍሪካ ከሚገባው የጦር መሳሪያ ግማሽ ያህሉ ከሩሲያ መሆኑን የሀገሪቱ የመንግስት የጦር መሳሪያ ላኪ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ዋና መሣሪያ ገዢዎች አልጄሪያ እና ግብፅ ናቸው። ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ካሜሩንም አዲስ ደንበኞች ሆነዋል።

በዲፕሎማሲው ግንባርም ለጠበቀው ግንኙነት የቀረበ ሽልማት አለ። አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከሩብ በላይ ድምጽ ያላት ሲሆን በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ድምጽ ልትሆን ትችላለች።

በሞስኮ ከፍተኛ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የታተመውና ስለ አፍሪካ እና ሩሲያ ትብብር የሚገልጸው የ 2021 ዘገባ እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም የሩሲያ ድርጊትን በተመለከተ የአፍሪካ ሀገራት ገለልተኛ የመሆን አዝማሚያ አሳይተዋል።