ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመች በኋላ ሞስኮ በኢትዮጵያዊው ዓይን ስትቃኝ

የፎቶው ባለመብት, Tefera Yehual
አቶ ተፈራ የኋላ በሩሲያ ዋና መዲና ሞስኮ ከ35 ዓመታት በላይ ኖረዋል። እአአ በ1991 የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ስትፈራርስም እዚያው ሞስኮ ነበሩ።
ከዚያ በኋላም በሩሲያ የተፈራረቁ አራት መንግሥታትን አይተዋል። የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ስትፈርስ የነበሩትን ሰርጌየቪች ጎርባቼቭን ጨምሮ ሩሲያን በመሩት በቦሪስ የልሲን፣ የዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፣ በቭላድሚር ፑቲን አስተዳዳር ሥር ኑሯቸውን መርተዋል፤ ፖለቲካውን ታዝበዋል።
አቶ ተፈራ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ያቀኑት በደርግ ዘመነ መንግሥት የትምህርት ዕድል አግኝተው ነበር። ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ከሩሲያዊት ጋር ትዳር መሥርተው እዚያው ሞስኮ ጎጆ ቀልሰዋል።
ከ30 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ትዳራቸውም ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።
አቶ ተፈራ ላለፉት አስርተ ዓመታት በሩሲያ እየኖሩ በመሆናቸውና ባለቤታቸውም ሩሲያዊት በመሆኗ የአገሪቷን ፖለቲካ በቅርበት ነው የሚከታተሉት። አሁን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ስላለው ጦርነትም ከመገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን ያገኛሉ።
ጦርነቱ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ተቆጣጥሮታል። የሩሲያ መገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ እየዘገቡ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት ግን ጦርነቱ ምዕራባውያንን ቢያርበደብድም ሩሲያውያን ግን መደበኛ ሕይወታቸውን ቀጥለው የተለመደ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። እምብዛም የመደናገጥ ስሜት አይታይባቸውም።
ከቀናት በፊት ጦርነቱን የሚቃወሙ ቡድኖች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ተፈራ፤ "ይህ ግን በምርጫ ወቅት ከተቃዋሚዎች በኩል ከሚደረግ ሰልፍ የተለየ አይደለም፤ ጥቂት ሰዎች ናቸው የወጡት" ብለዋል።
ለመሆኑ ፕሬዚደንት ፑቲን በሕዝባቸው እንዴት ይታያሉ?
አቶ ተፈራ አንድ መሪ ለአገሩ በሚቆምበት ጊዜ "የሁሉንም ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም" ይላሉ። ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
ቢሆንም ግን ፑቲን ለሩሲያ እንደ ትልቅ ባለውለታ፣ አገሩን በሥነ ሥርዓት እንደሚንከባከቡ እና የአገሪቷን ደኅንነት እንደሚያስጠብቁ መሪ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። በእርግጥ በሌላ በኩል 'ዲሞክራት ነን' በሚል የሚቃወሟቸው ወገኖች አሉ።
"ፕሬዚደንት ፑቲን የአውሮፓ አገራትን፣ አሜሪካንና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅትን [ኔቶ] ሲለማመጡ ቆይተዋል" የሚሉት አቶ ተፈራ፤ "የአገራቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ አሁን የወሰዱት እርምጃ በሕዝቡ ከፍተኛ ድጋፍ" እንዳለው ይናገራሉ።
ሩሲያውያን ጥያቄያቸው እንዴት ዜሌንስኪ ወንድሞቹን ለመውጋት ከምዕራባውያን ጎን ይሰለፋል የሚል እንደሆነ አቶ ተፈራ ይጠቅሳሉ።
"አሜሪካ ባመጣችው ጣጣ ለምን ዜሌንስኪ ይሸወዳል? ምዕራባውያን ሊቢያ፣ የመን፣ ኢራቅና ሶሪያ ገብተው ነገር ሲፈተፍቱ ምን እንዳስከተሉ እንዴት ጠፋው? ይህንን ለምን አይረዳም? ለምንድን ነው የአሜሪካ ቡችላ የሚሆነው?" በማለትም ፑቲን ስለወሰዱት እርምጃ ተገቢነት ይሟገታሉ።
ይሁን እንጂ እስካሁን ፑቲንን ደግፎ ወደ አደባባይ የወጣ የለም። ይልቁንም በተለያዩ የሩሲያ ከተሞች ጦርነቱን የሚቃወሙ ሩሲያውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
እንዲሁም ፑቲን በዩክሬን ላይ ሠራዊታቸውን ማዝመታቸውን ተከትሎ ምዕራባውያን በእጅጉ ተቆጥተዋል። ጉዳዩንም ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወስደው ተወያይተውበታል።
ሩሲያውያንና ዩክሬናውያን በአንድ አገር ሥር የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። ራሳቸውንም እንደ አንድ ሕዝብ ነው የሚቆጥሩት። የሚናገሩት ቋንቋ መሠረቱ ሩስኪ ነው። የሩስኪን ቋንቋም ይናገራሉ። ዘራቸውም አንድ ነው ይላሉ አቶ ተፈራ።
"በተለይ ደግሞ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያዋ ንግሥት ካትሪን ሁለተኛ የተቆረቆሩ ናቸው፤ ተዋልደዋል። ስላቭ የሚል ዘር ያላቸውም እነርሱ ናቸው።"
ሕዝቡ የተዋለደ ፣ በባህልም፣ በዘርም፣ በቋንቋም የተሳሰረ ነው፤ ችግሩ የፖለቲከኞች ነው በማለት በሩሲያና በዩክሬን መካከል የሆነው በእነዚሁ በፖለቲከኞች ውድድር እና ፉክክር የተከሰተ መሆኑን አቶ ተፈራ ይናገራሉ።
በዩክሬን ያለው ሕዝብም "ከወንድሞቻችን ጋር አታጣሉን" በሚል ሰልፍ እየወጡ እና በአገሪቷ በሚያገኙት መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ መቆየታቸውን አቶ ተፈራ አስታውሰዋል።
በእርግጥ በዩክሬን ውስጥ የናዚን መንግሥት ሲረዱ ነበሩ የተባሉ ቡድኖች አሉ እንደሚባል የሚጠቅሱት አቶ ተፈራ፣ ቢሆንም ግን በሁለቱ አገራት መካከል ያሉት ሕዝቦች ጦርነቱን የሚያዩት እንደ ፉክክር ነው።
አገራቱ ያጣላቸው በሕዝብ መካከል የተፈጠረ ጉዳይ ሳይሆን የፖለቲካ እና የድንበር ጉዳይ ነው።
አቶ ተፈራ እንደሚሉት ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እንኳን በርካታ ዩክሬናውያን የሸሹት ወደ ቤላሩስ እና ሩሲያ ነው። "ወደ ፖላንድ የሄዱት የናዚ ተከታይ የነበሩት ናቸው" ይላሉ።
በሩሲያ እየተማሩ ሳለ ወደ ዩክሬን ለሥራ ይመላለሱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተፈራ፤ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የፖለቲካ እና የአመለካከት ልዩነት ቢኖርም አንድ ሕዝብ መሆናቸውን መታዘባቸውን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Tefera Yehual
ከወረራው በኋላ የሞስኮ ድባብ ምን ይመስላል?
ነዋሪው እንደገለፁት ሞስኮ በተለመደው እንቅስቃሴዋ ላይ ናት። በከተማዋ ምንም የሚታይ የተለየ ነገር የለም። የንግድ ተቋማት፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆች፣ መሥሪያ ቤቶች በተለመደው ሥራቸው ላይ ናቸው።
በከተማዋ ውስጥ ስለጦርነቱ የሚያመለክቱ ወይም መሪውን የሚያወድሱ ነገሮች አይታዩም። የተሰቀለ ሰንደቅ ዓላማም ሆነ የፑቲንን ምሥል የሚያሳይ ፖስተር የለም።
"ሱቅም ስሄድ፣ በመኪናም ስሄድ፣ በመንገድ ላይ የተለጠፈ የፑቲን ፎቶ የለም። እኔ ፑቲንን የማየው በቴሌቪዥን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳቦችን ሲሰጥ ነው" ይላሉ።
ሩሲያ ጦርነት ውስጥ መግባቷን ያወቁትም ሆነ የሚከታተሉት በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው።
አገሪቱ ጦርነት ውስጥ የገባች አትመስልም። ምንም ጭንቅ የለም።
የአገሬው ሰው በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ እንዲኖር ያደረገው "ጦርነቱ አውሮፓውያን ያመጡት የፖለቲካ ጨዋታ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው" ይላሉ። በመሆኑም በከተማዋ 'ጦርነት ሊመጣብን ነው፤ ስንቅ እናዘጋጅ' በሚል የሚደረግ ጥድፊያ የለም።
እርሳቸው እንደሚሉት የአገሬው ሰው አሁንም ቢሆን ከፖለቲካው ይልቅ ኳስ ማየትን ነው የሚያዘወትረው።
"የሩሲያ ሕዝብ ከብዙ ታሪኮች በጦርነት ብዙ የተማረ ነው። ሁሉም ነገር ወዴት እንደሚያመራ አስቀድሞ ያውቃል" ይላሉ አቶ ተፈራ።
የዩክሬንን ፕሬዚደንት "አብዷል ወይ?! የአሜሪካ እና የአውሮፓውያንን ድምጽ እየሰማ እንዴት ከወንድሞቻችን ጋር እንደዚህ ዓይነት ግጭት ውስጥ እንገባለን' እያሉ ከመነጋገር የዘለለም ሌላ ወሬ አለመኖሩን ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 23 የወንዶች ቀን እንደነበር የተናገሩት አቶ ተፈራ የእርሳቸውም ካፍቴሪያ ሙሉ እንደነበርና እንቅስቃሴው ከወትሮው የሚለይ እንዳልነበርም አስረድተዋል።
"ጦርነቱ የፖለቲካ ጦርነት እንጂ ሕዝቦችን የሚያጣላ አይደለም። አሜሪካ እና አውሮፓ የሩሲያን ኃይል ለማዳከም፤ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበርና መሣሪያዎችን ለመሸጥ አስበው የቆሰቆሱት እሳት ነው ብሎ ሕዝቡ ያስባል።"
ጨምረውም አሁን ሕዝቡ የሚጠብቀው የሩሲያ ኃይሎች "የዩክሬኑን ፕሬዚደንት ዜሌኒስኪን ይዘው የራሳቸውን ሰው እንደሚያስቀምጡ ነው" ብለዋል ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሩሲያ ዜጋ።

የፎቶው ባለመብት, Tefera Yehual
"የከፋ ነገር ከመጣ እኔም ልዘምት እችላለሁ"
አቶ ተፈራ ኢትዮጵያ ተወልደው ይደጉ እንጂ ዜግነታቸው የሩሲያ ነው።
የፓስፖርት ለውጥ ብቻም ሳይሆን ልጆቻቸው በእናታቸው በኩል የሩሲያ ዘር አላቸው። በመሆኑም "የልጆቼም አገር ነው፤ የከፋ ከመጣ እኔም ልዘምት እችላለሁ" ይላሉ አቶ ተፈራ።
በሩሲያ አሠራር አንድ ሰው ፓስፖርት ሲወስድ አብሮ የሚገባው ቃል አለ።
ይህም አገሪቷ የሆነ ፈተና በገጠማት ጊዜ ፓስፖርት የተቀበለው ሰው እንደ አገሩ ቆጥሮ የገጠማትን ችግር ለመከላከል የሚገባ ቃል ኪዳን ነው። ይህ ቃል ከተገባ በኋላም በየትምህርት ደረጃ የተለያየ ማዕረግ ያለው ካርድ ይሰጣል።
አቶ ተፈራም ይህንን ቃል ገብተዋል። "የከፋ ከመጣ ለአባት አገር ሩሲያ ልዘምት እችላለሁ" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ እና ሩሲያን የሚያመሳስላቸው ነገርም ብዙ ነው። የሕዝባቸው ጠባይ አንድ ነው። ከፍተኛ ወኔ አላቸው። 'የሩሲያ ሕዝብ ከወደደ ይወዳል፤ ከጠላም የገባበት ገብቶ ያጠፋል።' የኢትዮጵያም ሕዝብ በተመሳሳይ ቆራጥ ነው" ይላሉ።
እንደ ነዋሪው ግምት ከሆነ በሩሲያ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሳይጨምር በአሁኑ ጊዜ 200 ገደማ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ።
የተቀናቃኛቸው የምዕራባውያን ወታደራዊ ማኅበር ኔቶ በዩክሬን በኩል ወደ ድንበራቸው እየተጠጋ መምጣቱ ያሳሰባቸው ፑቲን ስጋታቸውን እየገለጹ እርምጃም እንደሚወስዱ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
አሁን የፑቲን እርምጃ እውን ሆኗል። የሩሲያ ሠራዊት በምሥራቃዊ የዩክሬን ክፍል ውስጥ በሚገኙ ግዛቶች በኩል ጦርነት ጀምሮ በመላዋ አገሪቱ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው።
ጦርነቱ በዩክሬን በተለይ በዋና ከተማዋ ኪዬቭ ውስጥ ከባድ ሽብር ፈጥሮ ዜጎች ስጋት ውስጥ ሲሆኑ፣ የተወሰኑት ደግሞ ድንበር ተሻግረው ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት 48 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ፖላንድ መሻገራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
በተቃራኒው አቶ ተፈራ እንደነገሩን በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ ምንም የተቀየረ ነገር የለም፤ ሕይወት እና መደበኛ እንቅስቃሴ በነበረበት እንደቀጠለ ነው።
ነገር ግን ጦርነቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ምዕራባውያን እየጣሉት ያለው ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ዕቀባ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሲሆን፣ የሚያስከትለው ጫና ሞስኮን ጨምሮ ሩሲያ ውስጥም የጦርነቱ ጫና መሰማቱ አይቀርም።












