ሩሲያ እና ዩክሬን: ፑቲን ዩክሬንን እንዲወሩ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

ፑቲን ከውሾቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ብዙዎች ባልመጣ ያሉት ቀን መጥቷል። ዓለም በአንድ እግሯ ቆማለች። ኃያላኑ ምዕራባዊያን የሚያደርጉት የጠፋቸው ይመስላል።

ፑቲን እውን ያደርጉት ይሆን? ሲሉ ብዙዎች ሲጠይቁ ነበር።

ፑቲን አድርገውታል። የምዕራባዊያንን የማዕቀብ ዛቻ ወግድ ብለው፣ ክተት ካወጁ ሁለተኛ ቀናቸው ነው።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ወታደሮቻቸው ወደ ዩክሬን ዘልቀው እንዲገቡ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላለፉት ሐሙስ የካቲት 17/2014 ዓ.ም ነው።

የአለቃቸውን ትዕዛዝ በተጠንቀቅ ሲጠብቁ የነበሩት እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ምሥራቃዊቷ የዩክሬን ግዛት ዶንባስ ገስግሰዋል።

አሜሪካ ማዕቀብ ጥያለሁ ብትልም፤ አውሮፓውያን 'እኛ በቁም እያለን እንዴት ተደርጎ' ብለው ቢፎክሩም፤ ፑቲን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በዘመቻቸው ቀጥለዋል።

በቴሌቪዥን መስኮት ሚሊዮኖች በተከታተሉት ጠንከር ያለ ንግግራቸው በሩሲያ የሚደገፉ አማጺያንን እየተፋለሙ ያሉ የዩክሬን ወታደሮች መሳሪያቸውን በሰላም አስቀምጠው ወደቤታቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።

"እኔ ዩክሬንን የመቆጣጠር ዕቅድ የለኝም፤ ይህ ፀረ ናዚ፣ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል ፑቲን።

ነገር ግን አሉ ፑቲን. . . "ነገር ግን ማንም ቢሆን ሩሲያን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ከፈፀመ እኔን አያርገኝ፤ ቅጣቱ የከፋ ይሆናል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

"በእኛ ጉዳይ እጁን ሊያስገባ የሚሞክር ካለ፤ አገራችንን አደጋ ላይ ለመጣል ጉድጓድ የሚምስ ከተገኘ፤ ሕዝባችንን የሚገላምጥ ካየን፤ የሩሲያ ምላሽ ፈጣንና ተዘግኖ የማያልቅ ይሆናል። እውነቴን ነው፣ በሕይወት ዘመናችሁ አይታችሁ የማይታውቁት መከራ ይገጥማችኋል።"

የፑቲን ፍላጎት ምንድን ነው?

ፑቲን እኔ ዩክሬንን መቆጣጠር አልሻም ቢሉም ዩክሬን ግን ይህ አልተዋጠላትም።

የዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያ አገራችን ላይ የጦርነት ነጋሪት ጎስማለች ይላሉ።

''ሰላማዊ የሆኑ የዩክሬን ከተሞች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ዩክሬን እራሷን ትከላከላለች። ዓለም ፑቲንን ሊያስቆመው ይገባል" ሲሉ ትዊተር ገፃቸው ላይ ለጥፈዋል።

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የዩክሬን ከተሞች በፍንዳታ እየተናጡ ነው ሲሉ ዘግበዋል። ዋና ከተማዋ ኪዬቭ በሚገኘው ቦሪስፒል አየር ማረፊያ አካባቢ ተኩስ እንደነበር የተነገረ ሲሆን የሩሲያ ወታደሮች ወደ ከተማዋ ዳርቻ ተጠግተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና አጋሮቻቸው ሩሲያን በማዕቀብ አጥለቅለቀዋታል። ባይደን 'ገና ምን አይታችሁ የሩሲያን ምጣኔ ሃብት ሽባ አደርገዋለሁ' ሲሉም ዝተዋል።

''ፑቲን ቀድሞ የተዘጋጀበትን ጦርነት ለማካሄድ ቆርጧል። ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራው ከፍተኛ ነው። ዓለም ፑቲንን ተጠያቂ ታደርጋለች'' ሲሉም ተደምጠዋል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን።

ፑቲን ጦርነት ከማወጃቸው በፊት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ አውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል በመግለጽ ሩሲያውያን ይህንን እንዲቃወሙ አሳስበው ነበር።

ፑቲን ዓልሞ መተኮሻ መሳሪያ ላይ አነጣጥረው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለመሆኑ ፑቲን ከዩክሬን ምንድነው የሚፈልጉት?

ታላቋን ሩሲያን ዕውን የማድረግ ሕልም? ተስፋፊነት? ወይስ ምን?

የዚህ ጥያቄ መልስ እንደ ተጠያቂው ይወሰናል።

የምዕራብ አገር ተንታኞች የፑቲን ዋናው ፍርሃት ዩክሬን "መጥፎ የዲሞክራሲ ምሳሌ" በመሆኗ ነው ይላሉ።

ፑቲን ሕዝባቸውን የሚገዙበት የአስተዳደር ዘዬ 'ሰጥ ለጥ' የሚባለው ነው።

"ኦሊጋርክ" የሚባሉ ቢሊየነር የአገሬው ባለሀብቶች ከፑቲን ቃል ፍንክች አይሉም።

ጎረቤት ዩክሬን ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።

አንጻራዊ ነጻነት አለ። ሰፊ ዲሞክራሲ አለ። ይህ ቭላድሚር ፑቲንን የሚያስደስታቸው አይደለም የሚሉ አሉ።

ከምዕራባውያን ጋር ብዙም ማይስማሙት ፑቲን ዩክሬን ለአገራቸው ሰዎች 'መጥፎ' ምሳሌ እንድትሆን አይፈልጉም።

በዚህም ሕዝባቸው ከዕለታት አንድ ቀን ተነስቶ "የዩክሬን ዲሞክራሲ አጉርሰን" እንዳይላቸው ይፈራሉ፤ ፑቲን።

የኔቶ ስጋት

ሁለተኛው የወረራ ንሸጣቸው የ"ኔቶ" ጡንቻ መፈርጠም ነው።

ፑቲን በጣም የሚያበሳጫቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን አገሮች "ኔቶ" የሚባል የጦር ማኅበር ነው።

ይህ የወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅት 12 የአውሮፓ አገራት ናቸው የመሠረቱት። እነ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን አሜሪካም አሉበት። አሁን 30 ደርሰዋል።

ዩክሬን እዚህ ማኅበር ውስጥ አስገቡኝ በሚል ማመለከቻ አስገባች። ኔቶ እሺ ትንሽ ታገሺን አላት። ፑቲን ይህን ጊዜ ትዕግስታቸው ተንጠፈጠፈ። በንዴት ጦፉ።

ምክንያቱም የኔቶ አባል የሆነ አገር ጫፉ ከተነካ 30 አገራት ለዚያች አገር አግዘው ሠራዊታቸውን ያሰልፋሉ ወታደሮችና አውዳሜ የጦር መሳሪያቸውን ያሰፍራሉ።

ፑቲን ኔቶዎችን 'ተውኝ ልኑርበት'፣ 'ከምሥራቅ አውሮፓ ራቁልኝ' አሉ። ማንም አልሰማቸውም። አንጌላ ሜርከል ነበሩ የሚቀርቧቸው፤ እሳቸውም የሉም።

ፑቲን ቁጣቸውን የሚያበርድ ጠፋ።

መለማመጥ የሚያበዙት ምዕራቦች ምናልባት ከቁብም አልቆጠሯቸው ይሆናል።

ፑቲን ይሄኔ ልኬና አሳያችኋለሁ ብለው ተነሱ። ማንም አላመናቸውም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በጠራራ ፀሐይ ሉአላዊ አገርን ወረሩ ብሎ ማን ሊያምን ይችላል?

ምዕራባዊያን የመለማመጥ አባዜ አለባቸው። 'አፒዝመንት ፖሊሲ' ይሉታል። የ2ኛው የዓለም ጦርነትን ጦስ ያመጣው ይኸው ልምምጥ ነበር ይባላል። ያን ጊዜ ሒትለርን በቃህ ያሉት ቸርችል ነበሩ።

አሜሩካና የአውሮፓ ኃያል አገራት ቀኑን ባይለዩትም ፑቲን ዩክሬንን ሊወሩ እንደሆነ ሲያስጠነቅቁ ሳምንታት ተቆጥረው በመጨረሻም ሐሙስ ዕለት እውን ሆነ።

ለአሁን ከዩክሬን በስተቀር የሩሲያን ሠራዊት በጦርነቱ የገጠመ የለም። አስካሁን ምዕራባውያን ከባድ የሚባሉ ምጣኔ ሀብታዊ እቀባዎችን ከመጣል ባሻገር ወታደሮችን አሰማርተው ዩክሬንን ለመከላከል አልሞከሩም።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት እና ባለሥልጣናት አጋሮቻቸው ችላ እንዳሏቸው በመግለጽ አገራቸውን እራሳቸው እንደሚካከሉ እየገለጹ ነው። ጨምረውም ይህ የሩሲያ ወረራ ወዳጅና ጠላታችንን የምንለይበት ነው እያሉ ነው።

ዓለም ሕዝብ ደግሞ በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል በስጋት ውስጥ ሆኖ እየጠበቀ ነው።