የሩሲያ እና ዩክሬን ግጭት፡ ኒውክሌር ምን ዓይነት አደጋዎች ደቅኖብናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ፑቲን እሁድ ዕለት የአገሪቱ የኒውክሌር መከላከያ ኃይልን ጨምሮ ጦራቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዘዋል። ይህ ምን ማለት ይሆን?
ምዕራባውያን ተንታኞች ሃሳቡ ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም ይላሉ። የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ደግሞ ፑቲን የተጠቀሙት ቃላት ስለሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የማስጠንቀቂያ ደረጃ ካላቸው ግንዛቤ ጋር የሚስማማ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
አንዳንዶች ፑቲን ከዝቅተኛው የማስጠንቀቂያ ደረጃ (በቋሚነት ያለ የኒውክሌር የማስጠንቀቂያ ደረጃ መሆኑን ልብ ይሏል) ወደ ቀጣዩ "ከፍ ያለ" ("ወታደራዊ አደጋ" እና ከፍ ያለ "ሙሉ") እንዲሸጋገር አዘዋል ብለው ያስባሉ። ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እያንዳንዱ እርምጃ የጦር መሣሪያዎችን ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነትን ይጨምራል።
ብዙዎች ደግሞ እርምጃው ከምዕራቡ ዓለም የኒውክሌር አጸፋን እንደሚያመጣ ስለሚያውቁ ፑቲን በዋናነት ሕዝባዊ ምልክት አድርገው ብለው ተርጉመውታል። የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ ትዕዛዙ በዋነኛነት "ለመናገር" ያህል ነው ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።
ይህ ማለት ግን ምንም አይነት አደጋዎች የሉም ማለት አይደለም። በመሆኑም ሁኔታው በቅርበት መከታተል አስፈላጊ ነው።
ማስጠንቀቂያው አዲስ ነበር?
ባለፈው ሳምንት ፑቲን ሌሎች አገራት በሩሲያ ዕቅድ ጣልቃ ከገቡ "አይተውት የማያውቁትን" መዘዝ እንደሚከተላቸው አስጠንቅቀዋል። ይህ ደግሞ ሌለ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይህ ኔቶ በዩክሬን ጉዳይ በቀጥታ ወታደራዊ ተሳትፎ እንዳይኖረው የሚል ማስጠንቀቂያ ተደርጎ በሰፊው ተተርጉሟል።
ኔቶ ከሩሲያ ጋር ቀጥተኛ ግጭት ቢፈጥር ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ያውቃል። ስለዚህ ይህንን እንደማያደርግ ግልጽ ነው። የእሑዱ ማስጠንቀቂያ ግን ቀጥተኛ እና ይፋዊ ነበር።
አዲስ ማስጠንቀቂያ ለምን አስፈለገ?
ፑቲን እርምጃው "የኃይለኛ መግለጫዎች" ምላሽ ነው ብለዋል። ሰኞ ዕለት፣ ክሬምሊን መግለጫው የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን ጨምሮ የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ከኔቶ ጋር ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ግጭቶች መናገራቸውን ተከትሎ የመጣ ነው ብሏል።
የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት በበኩላቸው አዲሱ ማስጠንቀቂያ ፑቲን በዩክሬን ጉዳይ የተሳሳተ ስሌት በማድረጋቸው ነው ብለው ያምናሉ።
በዩክሬን የሚገጥማቸውን ተቃውሞ አሳንሰው ገምተውት ሊሆን ይችላል። ምዕራባውያንም ከማዕቀብ ጋር በተያያዘ የሚሰጡትን ጠንካራ ምላሽም አሳንሰው ገምተውታል። ይህም አዳዲስ አማራጮች እና ጠንካራ ንግግር እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
"ይህ የቁጣ፣ የብስጭት እና የመናደድ ምልክት ነው" ሲል አንድ በቅርቡ ጡረታ የወጡ የእንግሊዝ ጄኔራል ይናገራሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው ቋንቋው ፑቲን በዩክሬን ጦርነት አጥቂ ሳይሆኑ በዛቻ ራሳቸውን ለመከላከል የሚፈልጉ መሆኑን ለመግለጽ የጀመሩት ጥረት አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህ መልኩ ከታየ የኒውክሌር ማስጠንቀቂያው ተመሳሳይ መልዕክት ለሕዝባቸውም ማስተላለፊያ መንገድ ነው።
ሌላው ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ለዩክሬናውያን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት የያዙት ዕቅድ ፑቲንን ስላስጨነቀ ማስጠንቀቃቸው ነው ሊሆን ይችላል።
እንዲሁም የሚጣሉት ማዕቀቦች በአገራቸው አለመረጋጋት በመፍጠር መንግሥታቸውን ለመገልበጥ የተነደፉ ናቸው በማለት ያስባሉ። አጠቃላይ መልዕክቱ ግን ኔቶ በቀጥታ በግጭቱ የሚሳተፍ ከሆነ ጉዳዩ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ይመስላል።
አደጋዎቹ ምንድን ናቸው?
ምንም እንኳን የፑቲን ትዕዛዝ ለማስፈራሪያ ያህል እንጂ መሳሪያውን አሁን ለመጠቀም ፍላጎት ኖሮ ባይሆን እንኳን፣ አንዱ ሌላውን በተሳሳተ መንገድ ቢተረጉም ወይም ክስተቶች ከቁጥጥር ውጪ ቢሆኑ የተሳሳተ ስሌት ሊፈጠር ይችላል።
አሳሳቢው ነገር ፑቲን የተገለሉ እና ከግንኙነት ውጪ በመሆናቸው ጥቂት አማካሪዎቻቸው እውነቱን ሊነግሯቸው ፈቃደኞች መሆናቸው ነው። አንዳንዶች ውሳኔያቸው የተሳሳተ ነው ብለው ይፈራሉ።
አንዳንዶች ደግሞ በጣም ርቀው ከተጓዙ፣ በዕዙ ሰንሰለቱን ጠብቀው ወደ ታች በመውረድ ትዕዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ። የኑክሌር ግጭት የመኖር ዕድሉ በትንሹ ከፍ ቢልም ግን አሁንም ዝቅተኛ ነው።
የምዕራቡ ዓለም ምላሽ
የምዕራባውያን መንግሥታት እስካሁን ድረስ በንግግረ ደረጃም ሆነ በተግባር ግጭቱን እንዳይባባስ ጥንቃቄ አድርገዋል።
የአሜሪካ ጦር ኃይል ዴፍኮን የተባለ የራሱ የመከላከያ ዝግጁነት ማንቂያ ደረጃ አለው። የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ አሁን የኒውክሌር ማስጠንቀቂያ ደረጃውን "ለመቀየር ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም የኒውክሌር መሳሪያ የታጠቁ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ያሏት ሲሆን እስካሁን በአደባባይ ምንም አላለችም።
ዓላማው የሩሲያን መግለጫ እንደ ብዥታ መመልከት እና በቁም ነገር ወስዶ ውጥረቶችን ባለመጨመር ወይም እርምጃ ወስዶ የሩሲያን ምላሽ ላለማሳደግ ይመስላል።
ይህ የኒውክሌር ቀውስ አይደለም፤ መሆንም የለበትም ሲሉ የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
ሩሲያ ምን እየሠራች እንደሆነ ምዕራባውያን ያውቃሉ?
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሩሲያ ኒውክሌር መሣሪያ አቀማመጥ ዙሪያ እንግሊዝ እስካሁን ምንም ዓይነት ለውጥ አላየችም ብለዋል። ይህ በቅርበት እንደሚከታተሉት የደኅንነት ምንጮች አረጋግጠዋል።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሞስኮን የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመከታተል የሚያስችል ግዙፍ የስለላ ማሽን በምዕራቡ ዓለም ተፈጠሯል።
ለውጦች ለማየት ሳተላይቶች፣ የተጠላለፉ ግንኙነቶች መስመሮች እና ሌሎች መረጃዎች ይተነተናሉ። በዚህ ተመስርቶም ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በአብዛኛው ሁሉም ነገር እንዳለ ነው። ምዕራባውያን ምን ዓይነት ጉልህ የሆነ ለውጥ እንደሚኖር ለመረዳት የሩሲያን እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ። እስካሁን ግን ምንም ምልክት አልታየም።












