ሩሲያ እና ዩክሬን: ለዩክሬን ለመዝመት 8 ሺህ ኪ.ሜ ያቆራረጠው ካናዳዊ ኮሜድያን

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንቶኒ ዎከር የሚታወቀው በዩንቨርስቲ ተማሪነቱ እና ኮሜድያንነቱ ነበር።
ከ100 ሺህ በሚበልጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹ የሚታወቁት የዶናልድ ትራምፕን ደጋፊዎች ያለ እረፍት ሲቀልድባቸው ነው።
በቅርቡ ደግሞ በሃገሩ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ ላይ ሲቀልድ ይታወቃል።
ካናዳዊው አሁን ፖላንድ እና ዩክሬን ድንበር ላይ ደርሷል። የዩክሬን ያቀረበችውን የበጎ ፍቃደኞች ጥሪን ተቀብለው የሚዘምቱ የውጭ ዜጎች ቁጥር እያደገ ነው። እሱም ለመዋጋት ዝግጁ ነኝ ይላል።
የ29 ዓመቱ ዊከር ከደቡብ ምስራቅ የፖላንድና የዩክሬን ድንበር አቅራቢያ እንደተናገረው ከሆነ ከሦስት ልጆቹ ኣገር ህልሙ በቶሮንቶ ህይወቱን ለመግፋት ነበር። ከቀናት በፊት ግን በቴሌቪዥን ያየው ጦርነት ሃሳቡን አስቀየረው።
"እኔና ባለቤቴ ከዩክሬን የሚወጡ ዜናዎች እየተከታተልን ነበር። አንድም ጥሩ ነገር አልነበረውም። ይህ የሆነው ካናዳ ቢሆን የሚረዳን ሰው እንፈልጋለን ስል አሰብኩኝ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በመጀመሪያ ለራሱ የሰጠው ምላሽ ጦርነትን በማታውቅ፣ የተረጋጋች፣ በአንጻራዊነትም በበለጸገች ሃገር ውስጥ በመወለዱ "ዕድለኛ" መሆኑን ማወቁ የበለጠ አሳሰበው።
"እኛ በፍፁም እንደዚህ ዓይነት ጥቃት አይደርስብንም። በዚህ በኩል ዕድለኛ ነን። ከዩክሬን ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም። ዩክሬናዊ አይደለሁም። እኔ ሰው ነኝ። ወደዚህ ለመምጣት ይህ በቂ ምክንያት ይመስለኛል" " ብሏል።
ዎከር ምንም የውትድርና ልምድ የለውም። እንደውም ከሦስት ዓመት በፊት የካናዳ ጦር ሃይልን ሊቀላል ሞክሎ በሄሞፊሊያ (የደም መርጋት) ህመም ምክንያት ጤናማ አይደለም ተብሎ ውድቅ እንደተደረገበት ተናግሯል።
በኋላም አናጺነት እና የጭነት መኪና ሹፌርነትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። በድንገተኛ ህክምና ቴክኒሻንነት የምስክር ወረቀት አግኝቷል። በዩክሬን ይህን ክህሎቱን ለመጠቀም ተስፋ አድርጓል። ከአንድ የካናዳ ዩኒቨርሲቲ ስለሳይበር ደህንነትን እና ሰርጎ ገብነትን ይማር ነበር።
ለጊዜው ዎከር የቀድሞ የካናዳ ወታደሮችን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካን ጨምሮ በበበርካታ የሚቆጠሩ የቀድሞ በጎ ፈቃደኞችን ለመጠበቅ በፖላንድ ድንበር ላይ ለጥቂት ቀናት ለመቆየት አቅዷል።
ሰኞ ዕለት ለዩክሬን ጦር ዕቃዎችን በመኪና በማድረስ እየረዳ እንደነበር ተናግሯል።
ወደ ጦር ግንባር ከመዝመቱ በፊት ምዕራብ ዩክሬን ወደምትገኘው የሊቪቭ ከተማ ለማምራት አቅዷል።
በፖላንድ እና በዩክሬን መካከል ያለው የድንበር ማቋረጫ ሃገሪቱን ለቀው ለመውጣት በሚሞክሩ ስደተኞች ተጥለቅልቋል።
"አንዳንዶች ወደፖላንድ ድንበር ለመሻገር አራት ቀን ተሰልፈው ጠብቀዋል። "ረሃብ እና ብርድ ተደማምሮ ለእነሱ ሁኔታው ጥሩ አይደለም" ብሏል
ዎከር ወደ ዩክሬን ለመሄድ መነሳቱን ካሳወቀ ጀምሮ እሱን መከተል የሚፈልጉ ሌሎች በጎ ፈቃደኞች መልዕክት አጥለቅልቀውት እንደነበር ተናግሯል።
በተለይ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዲሚትሮ ኩሌባን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ለውጭ ሃገር በጎ ፈቃደኞች ጥሪ ካደረጉ በኋላ የሚያገኘው መልዕክት ከፍተኛ ሆኗል።
ጥሪዎቹ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንደ ሬዲት እና ዲስኮርድ ባሉ የማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ መልዕክቶችን አነሳስተዋል።
የበጎ ፈቃደኞች ቁጥር በግልፅ አይታወቅም። በዩኬ የዩክሬን አምባሳደር የሆኑት ቫዲም ፕራስታይኮ "ብዙ ቁጥር ያላቸው" የውጭ ዜጎች ለዩክሬን "መዋጋት እንዲፈቀድላቸው እየጠየቁ ነው" ብለዋል ።
ዩክሬን ሁሉንም በጎ ፈቃደኞች እንደምታስታጥቅ ገልጻለች። ሆኖም በትክክል ማንን እንደሚፈልጉ ወይም እንዴት እንደሚሰለጥኑ፣ እንደሚደራጁ እና እንደሚሰማሩ የሚገልጸው ዝርዝር መረጃ ትንሽ ነው።
በግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ እሑድ ዕለት እንደተዘገበው ከሆነ የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሜላኒ ጆሊ ወደ ዩክሬን በበጎ ፍቃደኝነት እና ለመዝመት የሚወስኑ ካናዳዊያን ውሳኔው የግላቸው ነው ብለዋል። ይህን ያሉት የዩክሬን ተወላጆች የሆኑ ካናዳውያንን አስመልክተው ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስም ብሪታንያውያን ለመዝመት "የራሳቸውን ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ" ሲሉ ሰዎችን ተስፋ ላለማስቆረጥ ሞክረዋል።
ዎከር እነዚህን ጥረቶች ቢደግፍም በጎ ፈቃደኞች ስላለው ከፍተኛ ወጪ እና ከገቢ አለመኖር ጀምሮ እስከ ሩሲያ ወረራ ድረስ ባለው የውጊያ እውነታ ላይ ተጨባጭ መሆን እንዳለባቸው ያስጠነቅቃል።
ብዙ በጎ ፈቃደኞች ወጣት እና በጦርነት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ብሎ ያምናል። በበይነ መረብ ከበጎ ፈቃደኞች ውይይት እያደርጉ ያሉ የቀድሞ ወታደሮች ያልተማሩ እና ያልተዘጋጁ በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ሸክም ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
በጦርነት ላይ ያተኮረውን ታዋቂውን የቪዲዮ ጌም በመጥቀስ "ልክ እንደ 'ኮል 'ኦፍ ዲዩቲ' ይመስላል በሚል ወደዚህ መምጣት ከፈለጋችሁ አትምጡ። ቦምቦች እና ጥይቶች ይገድላሉ። ይህ የቪዲዮ ጨዋታ አይደለም" ብሏል።
በዩክሬን የሩሲያ ጦርን የመጋፈጥ እድል እንደሚያሳስበው ዎከር ሲጠየቅ ኪዬቭ በሚገኘው የህፃናት ካንሰር ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሕፃን በመድፍ ተመቶ መሞቱን መዘገቡ የፈጠረበት ድንጋጤ ቁርጠኛ እንዳደረገው ይገልጻል።
"ለዚህ ልጅ ለመበቀል የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። "ትክክለኛውን ነገር እየሠራሁ እንደሆነ ይሰማኛል" ብሏል።












